በዘመናት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ የሚደፋው አስደናቂው ዘውድ

ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም. እኩለ ቀን ላይ ታሪካዊው የቅዱስ ኤድዋርድ ዘውድ ለዘመናት በዘለቀው የንግሥና ሥነ ሥርዓት መሠረት፣ በንጉሥ ቻርለስ ሳልሳዊ ጭንቅላት ላይ ይደረጋል። ነገር ግን አዲሱ ንጉሥ ዘውዱን ከአንድ ሰዓት ላነሰ ጊዜ ብቻ ከመድፋታቸው ባሻገር ፈጽሞ ድጋሚ አያደርጉትም።

አስኪ የዚህን ልዩ ዘውድ ገጽታ እና ያለውን ሚና ቀረብ ብለን እንመልከት።

ምንም እንኳን ቻርለስ የእናታቸውን ሞት ተከትሎ ወዲያውኑ ንጉሥ ቢሆኑም፣ ከጥንት ጀምሮ በዘለቀው ልምድ መሠረት ይፋዊው የንግሥና ሥነ ሥርዓታቸው የሚፈጸምበት ዕለት የሥልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።

ይህ አጋጣሚም በሥርዓተ ንግሥና ዕለት ብቻ የሚወጣውን፣ በዋጋ የማይተመነውን የቅዱስ ኤድዋርድ ዘውድን ለመመልከት በዘመናት ውስጥ የሚከሰት ዕድልን ይፈጥራል።

ከ22 ካራት ወርቅ የተሰራው እና የ360 ዓመት ዕድሜ ያለው ዘውድ 30 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ሲኖረው 2.23 ኪሎ ግራም ክብደት አለው።

ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት ዘውዱን ደፍተው የሚያሳይ ምስል

ይህንን ዘውድ ለመጨረሻ ጊዜ የደፉት ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት ሲሆኑ፣ ወቅቱም በ1953 (እአአ) ነበር። ላለፉት 70 ዓመታትም ዘውዱ ከሚቀመጥበት የለንደን ማማ የወጣው ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ነበር።

የንግሥቲቱን ንግሥና በሚመለከት ለተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም ቀረጻ ከዓመታት በኋላ ዘውዱ በወጣበት ጊዜ፣ ንግሥት ኤልዛቤት "አሁንም ከባድ ነው?" ብለው በማንሳት ክብደቱ እንዳለ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በጣም ከባድ ነው

ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት

ዘውዱ 444 በሚሆኑ በተለያዩ የጌጥ ማዕድናት እና በከበሩ ድንጋዮች የተንቆጠቆጠ ነው። ሰማያዊ እና አረንጓዴ የሚመስል ቀለሞችም አሉት። እንዲሁም ወርቅን ጨምሮ በሌሎች ውድ ማዕድናት የተዋበ ነው።

ቀደም ሲል በዘውዱ ላይ ያሉት የከበሩ ድንጋዮች የሚነሱ የነበሩ ሲሆን፣ በንግሥና ሥነ ሥርዓት ወቅት በዘውዱ ላይ እንዲቀመጡ ተደርገው የተዘጋጁ ነበሩ።

ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ግን የከበሩት ድንጋዮቹ በዘላቂነት ከዘውዱ ላይ እንዳይነሱ ተደርገው እንዲያያዙ ተደርገዋል።

ዳግማዊ ቻርለስ ከአዲስ ዘውድ እና ንጉሣዊ አርማ ጋር

ዘውዱ በ1661 (እአአ) ለዳግማዊ ቻርለስ ተብሎ ነበር የተሰራው። የዘውዱ ስያሜም ከቀደምት የአንግሎ-ሳክሶን ንጉሥ እና ቅዱስ ከሚባለው ኤድዋርድ የመጣ ነው። ንጉሡ በ11ኛው ክፍለ ዘመን ዘውድ ደፍቶ የሚያሳይ ምስል አለ።

የኤድዋርድ ዘውድ ንጉሡ ከሞተ በኋላ እጅግ የከበረ ቅርስ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል። ከዚያም በኋላ ከ1220 (እአአ) ከተካሄደው ከንጉሥ ሄንሪ ሳልሳዊ የንግሥና ሥነ ሥርዓት አንስቶ በነበሩት ተከታታይ ነገሥታት ጥቅም ላይ ውሏል።

ነገር ግን ከቀዳማዊ ቻርለስ ግድያ በኋላ ዘውዱ እና ሌሎች የዘውዳዊው ሥርዓት አርማዎች በ1600ዎቹ በኦሊቨር ክሮምዌል የምክር ቤት አባላት አማካይነት ቀልጠው እንዲጠፉ ተደርገዋል።

የክሮምዌል ሞትን ተከትሎ፣ ንጉሣዊው ሥርዓት በተለየ ሁኔታ ተመልሷል። ዳግማዊ ንጉሥ ቻርለስ የቅዱስ ኤድዋርድ ዘውድን ጨምሮ አዳዲስ የዘውዱ ሥርዓት ጌጣጌጦችን፣ እንዲሁም ንጉሥ ቻርለስ ከላይ በምስሉ ላይ አድርጎት የሚታየው አዲስ መንግሥታዊ ዘውድ እንዲዘጋጅ አድርጓል።

ነገር ግን የኤድዋርድ ዘውድ በጣም ጥቂት ጌጦች ብቻ ነበሩት። ዳግማዊ ቻርለስ ያሰራው ዘውድ ግን አልማዞች እንዲሁም ከግለሰቦች እና ከአንጥረኞች የተገዙ ባለቀለም የከበሩ ድንጋዮች አሉት ይላሉ የዘውድ ጌጣጌጦች የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት አና ኬይ።

ዘውዱ በክፈፉ ዙሪያ አራት መስቀል እና ቅርጾች እንዲሁም ግማሽ ክብ ቅርጽ ያላቸው ጌጦች አሉት።

የግማሽ ክብ ቅርጾቹ በትናንሽ የወርቅ ጌጦች እንዲሸፈኑ ተደርገዋል።

በዘውዱ አናት ላይ በተንጠልጣይ ዶቃዎች ያጌጠ መስቀል እና የንጉሡን ሥልጣን የሚወክል ሉል አለው።

ምንም እንኳን ዘውዱ የተሰራው በ1661 ቢሆንም፣ አሁን ንጉሥ ቻርለስ ዙፋኑን ሲረከቡ ሰባተኛው ንጉሥ ሆነው ነው የቅዱስ ኤድዋርድ ዘውድን የሚደፉት።

ይህ ዘውድ ዘወትር ጥቅም ላይ ስለማይውል፣ በተደጋጋሚ ከሚለወጠው እና ነገሥታቱ በፓርላማ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሚያደርጉት ዘውድ በተለየ ለረጅም ዘመናት አገልግሎት መስጠት ችሏል።

አሁን ንጉሥ ቻርለስ ሳልሳዊ በቅዱስ ኤድዋርድ ዘውድ ሲነግሡ ሰባተኛው ይሆናሉ

የዳግማዊ ቻርለስ ተተኪዎች የሆኑት ዳግማዊ ጄምስ እና ሳልሳዊ ዊሊያም ሁለቱም ንግሥናቸውን የተቀበሉት በቅዱስ ኤድዋርድ ዘውድ ነው። ዘመን ሲለወጥ የንጉሣውያኑ ፍላጎት እና ምርጫ በመቀያየሩ ከ200 ዓመታት በላይ በንግሥና ሥነ ሥርዓት ላይ ጥቅም ላይ ሳይውል ቆይቷል። ነገር ግን በተለያዩ ንጉሣዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ለዕይታ ሲቀርብ ነበር።

ንጉሥ ኤድዋርድ ሰባተኛ በ1902 ዘውዱን በማድረግ ንግሥናውን ለመቀበል አቅደው በተለየ ሁኔታ አሳድሰውት ነበረ። ነገር ግን ከንግሥና ሥነ ሥርዓቱ በፊት በመታመማቸው ሌላ ቀለል ያለ ዘውድ እንዲደፉ ተደርጓል።

ንጉሥ ኤድዋርድ ሰባተኛን የተከተሉት ጆርጅ አምስተኛ የታደሰውን እና በማይነሱ የተለያዩ ጌጣጌጦች በተንቆጠቆጠው ዘውድ ንግሥናቸውን ተቀብለዋል።

የታደሰው ዘውድ በመጀመሪያው ላይ ያልነበሩ አዳዲስ ውድ ጌጦች እንደተካተቱበት የከበሩ ማዕድናት ባለሙያው ኪም ሪክስ ይናገራሉ። የተጨመሩበት ጌጣጌጦችም በንጉሣውያኑ ዘንድ የሚታወቁ እና የሚወደዱ ናቸው።

ጆርጅ ስድስተኛም ዘውዱን የደፉ ሲሆን፣ ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤትም ንግሥናውን ሲረከቡ ዘውዱን በማድረግ የመጨረሻዋ ናቸው።

እዚህ ላይ እንደሚታየው የዘውዱ የፊት እና የኋላ ገጽታ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው።

በጠርዙ ዙሪያ ያለው ክፈፍም በመሳፍንቶች እና በመኳንቶች ዘንድ የሥልጣን ማሳያ ተደርጋ የምትወሰደው ኤርሚን የተባለችው እንስሳ ፀጉር የተለበጠ ነው።

የዚህን ዘውድ የፊትለፊት ክፍል ለመግለጽ ቀላሉ መንገድ ባሉት በቀለም ያሸበረቁ የከበሩ ድንጋዮቹ አማካይነት ነው። ቀደም ባለው ዘመን የፊቱን እና የኋላውን ለመለየት ትንሽ ግራ ያጋባ ነበር።

የንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ንግሥና በዓል

ከዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት አባት ጆርጅ አምስተኛ የንግሥና በዓል ቀደም ብሎ የዘውዱን የፊት እና ኋላ ገጽታ ለመለየት ቀይ ክር ታስሮበት ነበር። ነገር ግን ከንግሥና ሥነ ሥርዓቱ በፊት ሳይታወቅ ክሩ በመነሳቱ ለመለየት አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።

ኋላ ላይ ንጉሡ እንደጻፉት፡ "ዘውዱን በትክክለኛ መንገድ መድፋቴን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ አድርጌ ነበር። ነገር ግን ንግሥናውን የሚያስፈጽሙት የቤተክርስቲያን ኃላፊ እና ጳጳሱ ዘውዱን ሲቀባበሉት ስለነበረ የፊተኛው ክፍል የትኛው ይሁን አይሁን አላወቅሁም ነበር።"

ይህ ዘውድ ብዙም ለሕዝብ ዕይታ ባይቀርብም፣ ነገር ግን በስፋት ይታወቃል።

የብሪታኒያ ፓስፖርት ምስል

የዘውዱ ምስል በተለያየ ቅርጽ እና ገጽታ በብሪታኒያ ፓስፖርት ወይም በአገሪቱ የፖስታ አገልግሎት እንዲሁም በሌሎች ስፍራዎች ላይ አርማ ሆኖ ይገኛል።

ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት የቅዱስ ኤድዋርድ ዘውድ የዘውዳዊው ሥርዓት መለያ እንዲሆን አድርገዋል። የአዲሱ ንጉሥ ቻርለስ ዘውድ በጥንት ዘመን ከነበረው ጋር እንደሚመሳሰል ቢነገርም ልዩነት ግን አለው።

የዚህ የቅዱስ ኤድዋርድ ዘውድ በንጉሣዊው ሥርዓት የንግሥና ሥነ ሥርዓት ላይ ያለው አስፈላጊነት ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል።

ይህንን ዘውድ የተለየ የሚያደርገው ደግሞ የዘውዳዊው ሥርዓት ጥንካሬን እና ዘመናት ተሻጋሪነትን የሚወክል መሆኑ ነው።

ትሬሲ ቦርማን፣ የታሪክ ተመራማሪ እና ደራሲ

“በ11ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ኤድዋርድ የተዋወቀው ይህ ዘውድ፣ ዘውዳዊው ሥርዓት ጥንታዊ ተቋም መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ለዚህም ነው እስካሁን ድረስ ዘልቆ ለመቆየት የቻለው” ይላሉ በብሪታኒያ ዘውዳዊ ሥርዓት ዙሪያ ታሪካዊ መጽሐፍ የጻፉት ትሬሲ ቦርማን።

ይህ በዘመናት ውስጥ አንድ ጊዜ ከሚከናወኑት ሥነ ሥርዓቶች መካከል አንዱ የሆነው እና በመጪው ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም. የሚካሄደው የዳግማዊ ንጉሥ ቻርለስ የንግሥ ሥነ ሥርዓት፣ ሕዝቡ ዘውዱን ለማየት ዕድል ይፈጥራል።

ከዚያም በኋላ የቅዱስ ኤድዋርድ ዘውድ ቀጣይ ንጉሥ እስኪመጣ ድረስ ወደ ሚቀመጥበት ወደ ለንደን ማማ ተመልሶ ይገባል።