ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የመጨረሻውን ሙሌት ማጠናቀቋን ገለፀች
ኢትዮጵያ የመጨረሻውን የሕዳሴ ግድብ ሙሌት “በተሰካ ሁኔታ” ማካሄዷን ገለፀች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በይፋዊ የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው ላይ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ “አራተኛውንን እና የመጨረሻውን ሙሌት በተሳካ ሁኔታ” ማካሄዷን ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡን ለመገደብ በገንዘብ በዕውቀት፣ በጉልበት እና በጸሎት የተሳተፉትን ሁሉ በዚሁ መልዕክታቸው ላይ አመስግነዋል።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረች አስራ ሁለት ዓመታት ያህል አስቆጥራለች።
ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ግዙፍ ግድብን በውሃ መሙላት ከመጀመሯ በፊት አስገዳጅ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት በማለት ሲወተውቱ ቢቆዩም፣ ኢትዮጵያ ሳትቀበለው ለአራት ዙር ግድቡ ውሃ እንዲይዝ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በግድቡ ዙሪያ እየተጀመረ ሲቋረጥ የቆየ ድርድር ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ ሱዳን እና ግብፅ የግድቡን የውሃ ሙሌት እና ቀጣይ ሥራን በተመለከተ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ መካከል ሲደረግ የነበረው እና ለሁለት ዓመት ያህል ተቋርጦ የቆየው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በካይሮ ተካሂዶ ያለውጤት ተበትኗል።
ይህ ውይይት በመስከረም በኢትዮጵያ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
የግድቡ ግንባታ 11ኛ ዓመት ላይ፣ባለፈው ዓመት የካቲት 13፣ 2014 ዓ.ም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።
ግድቡ 145 ሜትር ከፍታና ወደ ጎን ደግሞ 1 ሺህ 780 ሜትር ርዝመት አለው።
ግድቡ የሚይዘውን 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሙሉ በሙሉ ሲይዝም ውሃው የሚተኛበት ስፍራ ርዝመት 246 ኪሎ ሜትር እነደሚደርስ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ግብፃውያን ግድቡ አገራቸው ከአባይ ወንዝ የምታገኘውን የውሃ መጠንን በመቀነስ ጉዳት ያስከትልባታል የሚል መከራከርያ ያቀርባሉ።
ኢትዮጵያ ግን የአባይ ውሃን የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት እንዳለት በመግለጽ፣ ግድቡ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን የውሃ አቅርቦት በማይጎዳ ሁኔታ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማመንጨት እንደምታውለው ትገልጻለች።
ግንባታው ከተጀመረ ከአስር ዓመት በላይ የሆነው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ 90 በመቶው መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለጎረቤት አገራት ኃይል ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ላለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ የውሃ ሙሌቱ ሲካሄድ የነበረው ግድብ ባለፈው ዓመት በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ መጀመሯን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ከግብፅ እና ከሱዳን በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማት ሲሆን፣ የግድቡ ጉዳይም ከአፍሪካ ኅብረት ባሻገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ሦስቱ አገራት በግድቡ ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት በአፍሪካ ኅብረት እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ንግግር ቢያደርጉም ሁሉንም ከሚያግባባ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቆይተዋል።
ተጠናቆ ሥራውን ሲጀምር በአፍሪካ ግዙፉ እንደሆነ የሚነገርለት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አገሪቱ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ከራሷ በማውጣት እያከናወነች ነው።