አስፐርቴም የተሰኘው የለስላሳ መጠጦች ማጣፈጫ ካንሰር ያመጣል? የዓለም ጤና ድርጅት ምን ይላል?

አስፐርቴም የተሰኘው በርካታ መጠጦች ውስጥ የሚገኝ ማጣፈጫ “ካንሰር ሊያመጣ ይችላል” ቢባልም የዓለም ጤና ድርጅት እስካሁን ምክሩን አልቀየረም።

የዓለም ጤና ድርጅት ሙያተኞች በሁለት ቡድን ተከፍለው በሺህ የሚቆጠሩ ጥናቶችን ሲመረምሩ ቆይተዋል።

“ካንሰር ሊያመጣ ይችላል” የሚል መረጃ ቢወጣም እስካሁን ያለው መረጃ አሳማኝ አይደለም ማለት ነው።

በርካታ ሰዎች አደጋ ያመጣል ከሚባለው መጠን በታች አስፐርቴም ቢወስዱም፣ ድርጅቱ በርከት አድርገው የሚወስዱ ሰዎች ጥንቃቄ እንዳይለያቸው አስጠንቅቋል።

አስፐርቴም ከስኳር ነፃ በሚባሉ ምግቦች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በአነስተኛ ካሎሪ ከስኳር 200 እጥፍ የሆነ ጥፍጥና መስጠት ይችላል።

ይህን ማጣፈጫ ከሚጠቀሙ ታዋቂ ምርቶች መካከል ዳየት ኮካ፣ ስኳር የሌለው ኮካ እና ፔፕሲ ማክስ ይገኙበታል።

ነገር ግን አስፐርቴም ከማስቲካ ጀምሮ እስከ ጥርስ ሳሙና እና እርጎ ድረስ ባሉ ምርቶች ውስጥ ይገኛል።

በ1980ዎቹ ለገበያ የቀረበው ይህ ኬሚካል በስፋት ጥቅም ላይ ቢውልም አሁን አከራካሪ ምርት ነው።

በዓለም ጤና ድርጅት የኒውትሪሽንና ምግብ ደኅንነት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ፍራንቼስኮ ብራንካ ጤናማው ምርጫ ስኳር ወይስ ማጣፈጫ ተብለው ተጠይቀው፣“ምርጫ ቀርቦ ኮላ በማጣፈጫ ይሁን አሊያም በስኳር ቢባልማ እኔ ሦስተኛ ምርጫ ኖሮ ውሃ ብጠጣ እመርጣለሁ። አሊያም ማጣፈጫ የገባባቸው ምርቶች በገደብ መጠቀም ይገባል።” ብለዋል።

ዶክተሩ እንደሚሉት ጥናቶቹ ሲመረመሩ አስፐርቴም ለጤና ጠቃሚ ላይሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ነገር ግን አንዳንዴ የምንጠጣው ከስኳር ነጻ የሆነውና የካሎሪ መጠኑ ዝቅተኛ የሆነው ዳየት ኮካ ሳይሆን ሊያሳስበን የሚገባው በጣም በተደጋጋሚ የምንጠቀም ከሆነ ነው ይላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት አካል የሆነው ዓለም አቀፉ የካንሰር ጥናት ኤጀንሲ አስፐርቴም “ካንሰር ሊያመጣ የሚችል ነው” የሚል መደመደሚያ ላይ ደርሷል።

ይህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው ማጣፈጫው የጉበት ካንሰር ሊያመጣ ይችላል የሚሉ ሦስት ጥናቶችን መሠረት አድርጎ ነው።

ነገር ግን ይህን ለማረጋገጥ ጠንከር ያለ ሳይንሳዊ ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል።

የካንሰር ጥናት ኤጀንሲው ሠራተኛ የሆኑት ዶክተር ሜሪ ሹባወር-ቤሪጋን “አሁን ያለው ማስረጃ ጥራት ያለውና ጠንካራ ነው ማለት ከባድ ነው” ይላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ይህ ማጣፈጫ “ለካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል” ቢልም በፈረንጆቹ 1981 የወጣን ምክር እስካሁን አልቀየረም።

ይህ ማለት በቀን በአንድ ኪሎ ግራም የሰውነት ክብደት 40 ሚሊግራም ነው መውሰድ የሚመከረው።

ይህን አድርጉ ማለት አይደለም። ከዚህ በላይ እንዳታደርጉ እንጂ የሚል ነው የጤና ድርጅቱ ምክር። ነገር ግን የምንለካው በሰውነት ክብደታችን ከሆነ ሕፃናት ሊጎዱ ይችላሉ።

ዶክተር ብራንካ ጣፋጭ መጠጥ ሕፃናት ባሉበት ለእራት ማቅረብ ቢቀርብን የሚል ምክር ይለግሳሉ።

አክለው ማጣፈጫዎች ክብደት ይቀንሳሉ የሚባለው በፍፁም ሐሰት ነው ይላሉ።

በጠቅላላው ምክራቸው ከስኳርም ሆነ ከማጣፈጫ ራሳችን በተቻለ መጠን ገለል እናድርግ ነው።