ምርጫ 97፡ "የአዲስ አበባን ሕዝብ የከዳነው እኛ ነን ብዬ ነው የማስበው" ልደቱ አያሌው

የፎቶው ባለመብት, Carter Center
ምርጫ 97 ሲነሳ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የተቃዋሚው ቅንጅት ፓርቲ አመራሮች መካከል አቶ ልደቱ አያሌው አንዱ ናቸው። በወቅቱ ከነበሩት ፖለቲከኞች መካከል ወጣት የነበሩት አቶ ልደቱ በአንደበተ ርቱዕነታቸው እና በሚያንጸባርቁት አቋም በርካታ ደጋፊዎችን መፍራት ችለው ነበር።
የምርጫው ሂደት ተጨናግፎ በተቃዋሚዎች እና በመንግሥት መካከል ፍጥጫ መፈጠሩን ተከትሎ ከአብዛኞቹ የቅንጅት አጋሮቻቸው የተለየ አቋም ያንጸባርቁ የነበሩት አቶ ልደቱ ስማቸው በአሉታዊ መልኩ በስፋት ሲነሳ ነበር።
ከምርጫ 97 ባሻገር አሁን ድረስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሚጠቀሱ ፖለቲከኞች መካከል ጎልተው የሚታዩት አቶ ልደቱ ያንን ብዙዎችን ያነቃቃ ምርጫን እንዴት ያስታውሱታል? በወቅቱ ያለፉባቸውን ውጣውረዶች እና ቁጭታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ- ምርጫ 97፣ 20 ዓመት እንደሞላው ስታውቅ አስደነገጠህ?
ልደቱ- ምን ያህል እያረጀሁ መኾኑን የሚነግረኝ እርሱ ነው። ትናንት እንደኾነ አድርጌ ነው የማስበው። በ97 ምርጫ የነበሩት ሁኔታዎች አእምሮዬ ውስጥ በጣም በጣም ትኩስ ናቸው። ሃያ ዓመት እንዲህ ሁለት ቀን ይሆናል ወይ? እላለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ለካ አርጅቻለሁ እላለሁ። ዕድሜዬ 20 ዓመት መጨመሩን ሳስብ ማለት ነው።
ቢቢሲ- ዘለግ ያለ ነገር ለማይወድ፣ ምርጫ 97 ለማያውቅ የቲክቶክ ትውልድ፣ ያን ምርጫ በአንዲት ዐረፍተ ነገር እንዴት ትገልጸዋለህ?
ልደቱ - በጣም ተስፋ ሰጪ የኾኑ ሁኔታዎች በአጭር ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ጎልተው የታዩበት፤ ግን ደግሞ የተኮላሸበት፤ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ ሌላ 20 ዓመት ወደ ኋላ የወሰደ ምርጫ ነበር።
ቢቢሲ- የምርጫ 97 ውርስ ያከራክራል። 'ዕቃ ወደ ቀበሌ፤ ትግሬ ወደ መቀሌ' የምትል ትርክት ኋላ የትግራይ ሕዝብ ላይ ለደረሰው ስቃይ በሩን ገርበብ አድርጎ ከፍቷል የሚሉ አሉ። ኢህአዴግ ያኔ ለሕዝብ ያስተዋወቃት ''ኢንተርሃምዌይ'' የምትል መርዘኛ ቃል በኋላ የመጣውን የእርስ በርስ ፍጅት አዋልዳለች የሚሉም አሉ። 97 የተዘራ ዘር ነው በኋላ ውጤቱን ያየነው?
ልደቱ- የተባሉትን ነገሮች 97 አይደለም ያመጣቸው። 97 መቀጠል ሲገባው 97 መክሸፉ ነው እነዚህን ችግሮች ያመጣቸው። ስለዚህ ችግሩን የፈጠረው ያ ሃሳብ፣ ያ ሂደት ሳይሆን ያ ሂደት መቀጠል ሲገባው መኮላሸቱ ነው። የተኮላሸው በማን ነው በአገዛዙ እና ግልብ የሆነ አመለካከት በነበራቸው የቅንጅቱ አመራሮች። ስለዚህ 97 አይደለም ተጠያቂው። የ97 አለመቀጠል እና መክሸፍ ነው ለዚያ ሂደት ተጠያቂው።
ቢቢሲ- በኢትዮጵያ ታሪክ 101 የፓርላማ መቀመጫ ያገኘ የተቃዋሚ ፓርቲ አልነበረም። ምናልባት ያንን ዕድል አንተ በምትለው መልኩ በአግባቡ ማስቀጠል ቢቻል ኖሮ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ምን ትመስል ነበር?
ልደቱ - የቅንጅት አመራሮች በተጭበረበረም ሁኔታ ተርፎም ያገኙትን የፓርላማ ወንበር፣ የአዲስ አበባ መስተዳድርን ተረክበው፣ የፖለቲካ ትግሉን አጠናክረው፣ ቀጥለው ቢሆን ኖሮ፣ የአሁኑ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በረዥም ርቀት የተለየ ይሆን ነበር።
በተለይ ተቃዋሚ ኃይሎች፣ 97 ያገኘውን ውጤት እንደ ትልቅ ድል ቆጥረን፣ ለበለጠ ድል የሚያበቃን መደላድል ነው ብለን ተጠቅመንበት ቢሆን ኖሮ ከአምስት ዓመት በኋላ በተካሄደው ምርጫ ወይም በ2002 ምርጫ ኢህአዴግን አሸንፈን መንግሥት የምንሆንበት ዕድል ይኖር ነበር።
ያ ማለት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ አንድ መንግሥት ከሥልጣን ወርዶ ሌላ መንግሥት የሚተካበት ታሪካዊ ሁኔታ ይፈጠር ነበር።
ዲሞክራቲክ የሆነ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ማየት እንችል ነበር።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኅልውና ፈተና የእርስ በርስ ጦርነት አይኖርም ነበር።
በብዙ መመመዘኛ የተሻለች፣ የተረጋጋች ኢትዮጵያ፣ ለሌሎች አገሮች ምሳሌ የምትሆን ኢትዮጵያ ትሆን ነበር ብዬ ነው የማስበው።
ቢቢሲ - አሁን ያልከውን ገልብጠን እንየው። የቅንጅት ወደ አንድ መምጣት ባይደናቀፍ ኖሮ አሁን የምትላት ኢትዮጵያን ማምጣት ይቻል ነበር እኮ።
ልደቱ-አይ! አይ! አይቻልም።
ቢቢሲ- ለምን?
ልደቱ - አንዱ ትልቁ ችግር የነበረው በዚያ ጊዜ የነበረው የቅንጅት አመራሮች እንደዚያ ብለው ማሰባቸው ነው። በነገራችን ላይ መንግሥት ለመሆን የሚያስችል ዕድል አልነበረንም። ቅንጅት ምርጫውን ለማሸነፍ የሚያስችል ዕድል አልነበረውም። ምርጫውን እንዳሸነፈ እና በማጭበርበር እንደተቀማ ተደርጎ የሚቀርበው ራሱ በጣም ስህተት ነው።
እኔ የቅንጅት አመራር ነበርኩ በወቅቱ፤ አንድም የቅንጅት አመራር በመግለጫም ሆነ በቃለ መጠይቅ ምርጫውን አሸንፈናል ብሎ ተናግሮ አያውቅም። ነጻ ጋዜጦች የሚባሉት እና ሕብረተሰቡ ነው እንደዚያ የተረዳው።
በብዙ መንገድ ካየኸው ያንን ምርጫ ልናሸንፍበት የምንችለው ጉዳይ አልነበረም። ያገኘነው ውጤት በጣም ከፍተኛ ነበር። ያንን ውጤት ይዘን ነው ማስቀጠል የነበረብን። ያንን ሂደት አቁመን ፓርላማ አንገባም ብለን፣ አዲስ አበባን አንረከብም ብለን፣ በሌላ ሕዝባዊ አመጽ፣ በሌላ መንገድ መንግሥትን ለመገልበጥ መሞከር ግን ኪሳራ ነበር የሚሆነው። በዚያ መንገድ በመኬዱም ነው ኋላ የሆነው ነገር የሆነው። እና አይቻልም ነበር።
ትልቁ ስህተት በምርጫ የተገኘውን ድምጽ በእጅ ይዞ እዚያ ላይ መጨመር እና ያንን ከማጠናከር ይልቅ በተለየ መንገድ በአቋራጭ በሕዝብ አመጽ ሥልጣን ለመያዝ ሙከራ መደረጉ፣ መታሰቡ ነው። እና እኔ ባልከው አልስማማም።

ቢቢሲ- እንደሰው መወደድን ትወዳለህ ብዬ አስባለሁ። የመወደድ ጫፍን ደግሞ ለአጭር ጊዜም ቢሆን አይተኽዋል፤ በተለይ በሚያዝያ 30 ሰልፍ ሰዎች የአንተን እጅ መንካት መባረክ እስኪመስል ድረስ 'ኢትዮጵያዊው ማንዴላ' እያለ ሕዝብ አሞካሽቶሃል። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ግን የጥላቻን አዘቅትንም ያየህ ይመስለኛል። በ20 ዓመታት ውስጥ አንዳንዴ ከራስህ ጋር ስታወራ 'ምነው የሕዝብን ስሜት በተከተልኩ'፣ ልክም ይኹን አይኹን 'ምነው ያኔ ከብዙኃኑ ጋር በቆምኩ'፣ 'ምነው ፓርላማ እንግባ ባላልኩ ኖሮ' የሚል ፀፀት ሽው ብሎብህ ያውቃል?
ልደቱ - . . . [ሳቅ] እንግዲህ ምናልባት ለዚህ የምሰጠው መልስ . . .
ቢቢሲ- ከ20 ዓመት በኋላ ንስሃ ነው ብዬ ነው።
ልደቱ - ገብቶኛል። ልንገርህ! ፖለቲካ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ብዙ ስህተቶች ሠርቼያለሁ ብዬ አምናለሁ። የማይሳሳት ድንጋይ ብቻ ነው፤ ሕይወት የሌለው ብቻ ነው። ይህንን ታሳቢ እናድርግ። የሚገርምህ ግን ፖለቲካ ውስጥ ከገባሁ በኋላ በሠራሁት ነገር የማልጸጸትበት ነገር ቢኖር 97 ላይ በወሰድኩት አቋም ነው።
ቢቢሲ - ለማመን እቸገራለሁ።
ልደቱ - ልትቸገር ትችላለህ። በፖለቲካ ሕይወቴ ሁለት ነገር ለምሳሌ ጥራ ብትለኝ 97 ምርጫ የወሰድኩት አቋም እና ባለፈው የብልጽግና አገዛዝ ከመጣ በኋላ ኢህአዴግን ለማፍረስ ጥረት ሲያደርግ፣ በትግራይ ጦርነት ለመጫር ጥረት ሲያደርግ መቃወሜ ነው። ሁለቱም በእኔ የፖለቲካ ሕይወት ትልቅ ትርጉም ያላቸው ናቸው። ያንን በማድረጌ ደግሞ በጣም ነው የምኮራው።
በተለይ ምርጫ 97 ሰው እንደተሳሳትኩ ያስባል። አሁን ያንተም የጥያቄ አቀራረብ እንደዚያ ነው የሚመስለው። እንደ ስህተት እንደሚያጸጽት ነገር አድርገህ ነው ያየኸው። እውነቱን ልንገርህ 'አብሶሉትሊ' [ፍጹም] ትክክል ነው የነበርኩት።
እኛ ያልነውን መንገድ ያኔ ቅንጅት ተከትሎ ቢሆን ኖሮ ከአምስት ዓመት በኋላ መንግሥት የመሆን ዕድል ነበረን። ኢትዮጵያ ዛሬ የኅልውና ጥያቄ ውስጥ አትገባም ነበር። ጽንፈኝነት ብሔርተኝነት የበለጠ እየተዳከመ ይሄድ ነበር። ያ ያልሆነው ከእኛ በተጻራሪ የሄደ አመራር ስለነበር ነው። ይህንን ደግሞ ቃል በቃል ያኔ ተናግሬዋለሁ። ጽሑፎቼ ላይ ታገኘዋለህ። ቃለ ምልልሶቼ ላይ ታገኘዋለህ።
ቢቢሲ -የኔ ጥያቄ ግን ስሜትህን የሚመለከት ነበር። ሁላችንም ቅጽበታዊ ስሜቶች አሉን፤ በ20 ዓመት ውስጥ ፀፀት አንዴም ሽው አላለብኝም ነው የምትለው?
ልደቱ- ስፔሲፊክ አድርገህ ነዋ የጠየቅከኝ። ገብቶሃል? 97 ዓ.ም. ተቀብዬ ቢሆን የሌሎቹን ሃሳብ ብለህ ስላነሳህ ነው የመለስኩልህ። አጠቃላይ ትግሉን በሚመለከት የሰው ልጅ ነኝ።
እዚህ ትግል ውስጥ ገብቼ ምን አተረፍኩ፤ ምን ውጤት አመጣሁ? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። ራሴን እንደተሸናፊ ነው የምቆጥረው። ይህንን ደግሞ በአደባባይ ገልጫለሁ። 32 ዓመት ታግዬ የወደቅኩ፣ የከሰርኩ ፖለቲከኛ ነኝ ብዬ በአደባባይ፣ ማንም ፖለቲከኛ እንደዚያ ብሎ አያውቅም ተናግሬያለሁ። ይህ ከምንድን ነው የሚመጣው ከቁጭት ከጸጸት ነው እኮ የሚመጣው።
32 ዓመት ስለ ሰላማዊ ትግል ሰብከህ ታግለህ መጨረሻ ላይ ጦረኞች፣ ብሔርተኞች የኢትዮጵያን የፖለቲካ አሸናፊ ሆነው ሲቆጣጠሩት ራስህን እንደ ወደቅክ እንደ ከሰርክ ትቆጥራለህ። ደግሞም ኪሳራ ነው። ይህ ስሜቴን አይጎዳውም ብልህ መዋሸት ነው የሚሆነው፤ ይጎዳዋል። ምናልባት በሌላ ነገር ብሰማራ ውጤታማ እሆን ነበር ብዬ ላስብ እችላለሁ። የሰው ልጅ ነኝ፤ አእምሮዬን የሚፈትኑ ነገሮች ይኖራሉ።
ቢቢሲ- ጥያቄዬ የ20 ዓመት ግምገማ አልነበረም። ያቺ ከሕዝብ ተለይተህ የቆምክባት ቅጽበትብዙ አስከፍልሃለችና አትጸጸትህም ወይ? ነው ጥያቄዬ
ልደቱ-እሱንማ መለስኩልህ። 'አብሶሉትሊ' ትክክል ነበርኩ። ያን በማድረጌ እኮራለሁ። እኛን አንደ ከሃዲ፣ እኛን እንደ ቅጥረኛ ቆጥሮናል ብዙ ሰው፤ ብዙ ታምተናል. . . ብዙ ተወርቶብናል...ግን...።
ቢቢሲ- ብዙ ተወርቶብናል ስትል. . . የትኞቹ ትዝ ይሉሃል? የትኞቹ ያስቁሃል? የትኞቹ ስሜትህን ይጎዱታል? ለምሳሌ ተንሸራታች ስልክ በአንተ ስም ተሰይሞ ነበር። ከአቦይ ስብሃት ጋር ሸራተን ነው የሚያሳልፈው ይባል ነበረ። ለዓመታት ከክህደት ጋር ስምህ ይነሳ ነበረ። የሚያስቅህ አለ? የሚጎዳህ አለ? ለምደኽዋል?
ልደቱ -መጀመሪያ አካባቢ ማስታወሻ ይዤ እመዘግብ ነበር። አሁን ሰልችቶኝ ትቸዋለሁ። አስታውሳለሁ ወደ 98 አሉባልታዎች እኔን በሚመለከት የተወሩ ነገሮች መዝግቤ ነበር። የሚገርምህ ከ98 አንዱም እውነት አልነበረም።
ቢቢሲ - ለምሳሌ የትኞቹ?
ልደቱ - የትኞቹን ልበልህ (ፈገግታ). . . ለምሳሌ ቅድም አንተ ያነሳሀው አቦይ ስብሃት ጋር ተገናኝቶ ነበር የሚባለው። ውሸት ነው። አቦይ ስብሃትን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘኋቸው ምርጫ 97 ከተካሄደ ሁለት ሦስት ዓመት በኋላ ኤርፖርት ነው።
በሕይወቴ አንድም ቀን ሸራተን አድሬ አላውቅም፤ እስካሁን ድረስ። ከምርጫውም በፊት ከምርጫውም በኋላ። እኔ 98 አሉባልታ መዝግቤ አንዱም እውነት አልነበረም።
ቢቢሲ- ስሜትህን አይጎዳውም እንደዚህ ዓይነት ነገር? አታዝንም?
ልደቱ- . . . የማዝነው በእኔ በደረሰው ጉዳይ ላይ አይደለም። እኔ ትግል ውስጥ ገብቻለሁ። እንኳንስ ስምህ ሕይወትህ ሊጠፋ ይችላል። እኔ ራሴን ገድዬ ነው እዚህ ትግል ውስጥ የቆየሁት። ነገ ከነገ ወዲያ ባሉት ቀናቶች ልሞት እችላለሁ። ልገደል እችላለሁ። ሕይቴን ላጣ እችላለሁ፤ ስምህ ይመለሳል፤ ችግር ለውም።
ቢቢሲ - በወቅቱ ግን እነዚህ ተምሳሌቶች ስሜትህን ይጎዱት ነበር? ከስልክ ጋር፣ ከክህደት ጋር፣ ከብዙ ነገር ጋር ሲገናኝ እንደ ሰው እነዚህ ስሜቶች እንዴት ላይሰሙህ ይችላሉ?
ልደቱ - አየህ ችግሩ ምን መሰለህ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዘመን ያስቸገረን ፖለቲከኛ 2010 ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ነው የኢትዮጵያን ፖለቲካ መከታተል የጀመረው። እና ከእነዚህ ሰዎች ጋራ ፖለቲካ አውርቶ መግባባት በጣም አስቸጋሪ ነው።
ሁለተኛ 97 ዓ.ም. የምርጫው ወቅት ማለት ነው የገጠመን አንዱ ችግር እርሱ ነበር። ፖለቲካ መከታተል ብዙ ሰው የጀመረው ምርጫ 97 ላይ ነው። በጣም የምርጫው ነገር ትኩረት ሳበ፣ ክርክሮች ነበሩ። በዚያ ምክንያት ኅብረተሰቡ ተሳበ። የመንግሥት ለውጥ ሊመጣ ነው ብሎ አመነ።
የፖለቲካ ትኩሳቱ ሕብረተሰቡን ፖለቲካ እንዲከታተል አደረገው። ብዙ ሰው ፖለቲካ መከታተል የጀመረው እዚያ ላይ ነው። እኔ ግን ፖለቲካ ውስጥ የነበርኩት ከዚያ በፊት 12 ዓመት ነው። በዚያ ሂደት ውስጥ ብዙ አሉባልታ ተወርቶብኛል።
ገና የመአህድ የወጣቶች ክንፍ ሊቀመንበር ሆኜ ከተመረጥኩበት ጊዜ ጀምሮ በጣም ከፍተኛ የሆነ አሉባልታ ሲወራብኝ ነበረ። ትግሉ ውስጥ ገብቼ የመጀመሪያዎቹ ሁለት፣ ሦስት ዓመታት አንድ ነገር አሉባልታ ሲወራብኝ እንቅልፍ አጥቼ ነበር የማድረው። እናደድ ነበር።
ምርጫ 97 የመጣው ከፍተኛ ደረጃ ከደረስኩ በኋላ ነው። እኔን የሚሰማኝ ሕብረተሰቡ እንደሚያስበው አይደለም።
ቢቢሲ - 97 ላይ በወሰድከው አቋም የተናደደ ፀጉር አስተካካይ አልቆርጥም አላለህም፤ አስተናጋጅ አልታዘዝም አላለህም? ጋራዥ መኪናህን አልሰራም አላለህ?
ልደቱ - ከአኗኗሬ አንድም ነገር አልቀየርኩም። ጫማዬን እንኳን ሳይቀር መንገድ ላይ ቁጭ ብዬ የማስጠርግበት ቦታ ላይ ነው የማስጠርገው። ለምሳሌ ባንክ ስሄድ ብዙ ጊዜ መኪናዬን ቢሮ አቁሜ በእግሬ ነው የምሄደው። ከ97 ምርጫ በኋላም በእግሬ ነው የምሄደው። መንገድ ላይ ሰዎች ሲያዩኝ ሰዎች ሲያዩኝ ይደነግጣሉ።
ምክንያቱም ስለ እኔ የሚወራው ሌላ ነገር ነው። ጥይት በማይበሳው መኪና እንደሚሄድ፣አምስት ስድስት አጃቢ እንደሚያጅበኝ ተደርጎ ነበር የሚወራው። ድንገት መንገድ ላይ በእግሬ እየሄድኩ ሲያዩኝ ይደነግጣሉ። ዞር ዞር ብለው አጃቢ ያለኝ መስሏቸው ለማየት ይሞክራሉ። አሮጌ መኪናዬን ይዤ መብራት ላይ ቆሜ ጎን ለጎን ያዩኛል። ይደነግጣሉ። እነርሱ ትልቅ ጥቁር መስታወት ያለው ኮብራ ነው የሚጠብቁት። እና ከነበረኝ ሕይወት የተለየ ሕይወት አድርጌ አላውቅም። የገጠመኝም በዚያ ደረጃ የለም። የሚወራው እና እውታው ሌላ ነው።
ቢቢሲ- ስለዚህ ምንም አልደረሰብኝ ነው መልሱ።
ልደቱ - ይልቅ ከባዱ ነገር ምን መሰለህ፤ ለምሳሌ እህቶቼ ታክሲ ውስጥ ሆነው ወይንም የሆነ ቦታ ሲገኙ ስለ እኔ ይወራል። እና የሚሰሙት ነገር አስፈሪ የሆነ ዘግናኝ የሆነ ነገር ነው። ለምሳሌ የልደቱ እናት ቤተክርስቲያን ሄዳ ተደበደበች ተብሎ ይነገራል። ከእኔ አልፎ ቤተሰቤን የሚነካ ነገር ማለት ነው።. . . ይኼ በጣም ያሳዝነኛል። ለምንድን ነው የሚያሳዝነኝ እኔ አምኜበት ነው ፖለቲካ ውስጥ የገባሁት፣ እኔን በሚመለከት ቢያወሩ ችግር የለብኝም እቋቋመዋለሁ። ከእኔ ጋር ዘመድ ለመሆን ወስነው ያልተወለዱ ሰዎች ግን ለምን የዚህ ተጠቂ ይሆናሉ። እኔ ግን በግሌ ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል ልደቱ በግሌ የሚደንቀኝ ነገር የለም።
ቢቢሲ - በ20 ዓመት ውስጥ ስለ ፖለቲካ ምን ተማርክ? ፖለቲካ የግድ የመርኅ ሳይንስ አለመሆኑን? ፖለቲካ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ መሆኑን? ፖለቲካ አንዳንዴ ትልቅ ግብ ለማሳካት ትንንሽ ግን አስፈላጊ የሆኑ ስህተቶች (ክህደቶችንም ቢሆን) መፈጸም የሚፈልግ መሆኑን? ምንድን ነው ያስተማረህ ሀያ ዓመት?
ልደቱ - በፖለቲካ አንዳንድ ጊዜ እንደዚያ ለማድረግ የምትገደድበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። እኔን በተመለከተ ግን የሚነሱት ሁለት ነገሮች ናቸው። አንዱ የ97 ጉዳይ ነው።
ሌላው ከዶ/ር ዐቢይ ጋር የተያያዘ ነው። የዶ/ር ዐቢይ አገዛዝ መጣ። እኔ ከተወሰኑ ወራት በኋላ መጥቼ የትም አያደርሰንም አያሻግረንም አልኩ። ትልቅ ጫጫታ ነው የነበረው። እንዴት እንዲህ ትላለህ? ቀንተህ ነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፍራሽ ሆነህ ነው። ሌላ ተልዕኮ ኖሮህ ነው ያላለኝ አልነበረም።
ዝም ብዬ ብደግፍ ኖሮ ከዚያ በኋላ አራትም ዓመት፣ አምስትም ዓመት፣ ሰባትም ዓመት አብረው ከተጓዙት ጋራ ልመሳሰል ብዬ ልደግፍ ብል ኖሮ ምን ውጤት ይመጣ ነበር?
ኢህአዴግን እናፍርስ ሲባል፣ ህወሓትን ለመምታት ጥረት ሲደረግ፣ አያዋጣም ይህ ነገር፣ ወደ ጦርነት ነው የሚወስደን ብዬ ተከራክሬያለሁ። ያንን ባለደርግ እና ትግራይ ውስጥ የነበረውን ጦርነት የሻዕቢያን ጭፍጨፋ ሁላ ደግፌ እንደሌሎቹ ብቆም ምን አስተዋጽኦ አደርግ ነበር?
ስለዚህ የወሰድኳቸው አቋሞች ስትራቴጂክ የሆኑ ናቸው። ተገቢ የሆኑ ናቸው፤ ከዚያ በመለስ ግን በፖለቲካ ቅድም ያልከው ዓይነት ሁኔታ ሊገጥም ይችላል። ያን ደግሞ እውነቱን ልንገርህ ከማንም በላይ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። አስፈላጊ ሲሆን ላደርገው እችላለሁ። ግን ያ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ቅንጦት ነው። እንደዚያ ዓይነት ሜይን ስትሪም የምትለው ፖለቲካ በአውሮፓ በአሜሪካ በምርጫ ፉክክር የምታደርገው ፖለቲካ አይደለም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው።
የኅልውና ፈተና ነው። ሐቁንም ይዘን መሻገር አልቻልንም። እንኳንስ እንደዚያ ዓይነት ፖለቲካ እያራመድን። ዋና የፖቲካችን ችግር እኮ አድር ባይ መሆን ነው። ፖፕሊስት መሆን ነው። ሕዝበኝነት ነው።
ቢቢሲ - ፕሮፌሰር መስፍን 'የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙትልኝ እንጂ ልሙትልህ የማይል ነው' ይሉ ነበር። አንተ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ትገልጸዋለህ?
ልደቱ - በአጭሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ ራሱ ያለው ግምት የተሳሳተ ነው። ራሱን እንደ በቃ ሕዝብ፣ ራሱን እንደ አዋቂ ሕዝብ፣ እንደ ጥሩ ሕዝብ አድርጎ ነው የሚቆጥረው። እውነታው ግን ይህ አይደለም። በተለይ ከፖለቲካ አንጻር አያይዘን ስናየው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የለውጥ ኃይል አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገዛዝ የተመቸ፣ ለጭቆና የተመቸ ሕዘብ ነው።
ለዚህም ነው በእንዲህ ዓይነት ደካማ እና አምባገነን መንግሥታት እየተመራ የቀጠለው።
ቢቢሲ - ከምርጫ 97 በኋላ የአዲስ አበባ ሕዝብ አንድ የመታው የፖለቲካ መጋኛ አለ? የአዲስ አበባን ሕዝብ እንዴት ትገልጸዋለህ?
ልደቱ- የአዲስ አበባን ሕዝብ እኛ ነን የከዳነው ብዬ ነው የማስበው። የአዲስ አበባ ሕዝብ በምርጫ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ እኛን አምኖ ሌሊት ተነስቶ መርጦናል። እንኳንስ እኛን የሚደግፈው የአገዛዙ አባል ናቸው የሚባሉ ሳይቀሩ ናቸው አዲስ አበባ ላይ የመረጡን። ያንን የሰጡንን ድምጽ ነው ሜዳ ላይ የበተንነው።
አስተዳድረኝ ብሎ የአዲስ አበባ ሕዝብ ድምፁን፣ ካርዱን ሰጥቶን አንረከብም፤ አንገባም ብለን ነው የወሰንነው። እኛ ነን መጀመሪያ የካድነው።
ተስፋ መቁረጥ የለበትም። በሰላማዊ ትግል ጥርሱን ነክሶ መቀጠል ነበረበት። ግን ምን ሆነ ሕብረተሰቡ ተስፋ ቆረጠ። በቃ ከዚህ በኋላ ሰላማዊ ትግል አያስፈልግም ብሎ ወደ ጽንፈኛ ፖለቲካ አንጋጦ ማየት ጀመረ። ለዚያ ዋነኛ ተጠያቂው እኛ ነን፤ የፖለቲካ አመራሩ ነው ባይ ነኝ።
ቢቢሲ - ግን 97 የአዲስ አበባ ሕዝብን ፈሪ አድርጎታል እንዴ?
ልደቱ - አዎ፣ ለምን መሰለህ አንደኛ በምርጫው ወቅት በተፈጠሩት ግርግሮች 193 ሰዎች ሞተዋል። አሁን በጦርነት ከሚሞተው ሕዝብ ጋር ስታነጻጽረው ኢምንት ነው። ያኔ ዓለምን ያንጫጫ ግድያ ነው የነበረው። 193 ሰው አዲስ አበባ ሞቷል። ግን ዋናው ነገር ምንድን ነው ሰዉ በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ ቅንጅት መንግሥት ሊሆን ነው ብሎ አሰበ። ያ እንዳልሆነ ሲያውቅ በሰላማዊ ትግል ተስፋ ቆረጠ። ምርጫውን ማሸነፍ የማንችል መሆናችንን እውነቱን እያወቅን ለሕብረተሰቡ መንገር ነበረብን።
ቢቢሲ- የአዲስ አበባን ሕዝብ በፖለቲካ ባህሪ ደረጃ የሚለየው ነገር አለ ብለህ ታስባለህ?
ልደቱ - አዎ የከተማ ሥነ ልቦና ለኢትዮጵያዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ የቀረበ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሁልጊዜ እኔ ምን እላለሁ 20 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተማ ነው የሚኖረው። እነዚህ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ላላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና ማኅበራዊ መሠረት ናቸው። 97 የታየው ይህ ነው።
አብዛኛው ቅንጅት ያሸነፈው በከተሞች ነው። በከተማ ያለ ሕብረተሰብ ሥነ ልቦናው የኢትዮጵያዊነት ነው። አሁንም ቢሆን፣ በእርግጥ እየቀነሰ መጥቷል። የብሔርተኝነቱ ፖለቲካ የከተማውንም ሕዝብ እየበከለው መጥቷል።
ያኔ 100 በመቶ ነው የተመረጠው። አንድ ሰው ነው ከኢህአዴግ አሸንፎ የገባው። ያም ደግሞ ያሸነፈው በሥነ ምግባር ምክንያት አንድ ሰው አስቀድመን እንዲወጣ ስላደረግን ነው። እንጂ አሸንፎ አይደለም። መቶ በመቶ ነው ያሸነፍነው። ዛሬ ምርጫ ቢካሄድ መቶ በመቶ ላናሸንፍ እንችላለን። ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ቢደረግ ምንም ጥርጥር የለኝም 70 በመቶ 80 በመቶ እንደምናሸንፍ።
አሁንም ማኅበራዊ መሠረታችን ነው። የአዲስ አበባ ሕዝብ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ነገ ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ ቢካሄድ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ያላቸውን ፓርቲዎች ነው የሚመርጠው። በ97 መጠን ባይሆንም ማለቴ ነው።
ቢቢሲ - 97ን መለስ ብለን ስናስታውስ ምንድን ነው የምንማረው?
ልደቱ - 97 እጃችን ውስጥ ገብቶ ያመለጠን ትልቅ ዕድል ነው። ከዚያ በኋላ የሄድንበት የፖለቲካ ሂደት የቁልቁለት ነው፤ የውድቀት ሂደት ነው። ወደዚያ ሂደት መመለስ አለብን ብሎ ሰዉ ማሰላሰል [ሪፍሌክት] ማድረግ ያለበት ይመስለኛል። አዋጪው መንገድ አሁንም 20 ዓመት ወደኋላ ብንሄድም ወደዚያ መመለስ ነው። ከዚህ አንጻር ሕብረተሰቡ ትንሽ ቢያስብበት ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።
ቢቢሲ - ከፖለቲካ ራስህን ገለል የማድረግ ሐሳብ ውልብ ብሎብህ ያውቃል? መቼ ነው ጡረታ የምትወጣው?
ልደቱ - መቼም ከፖለቲካ ጡረታ የመውጣት ሐሳብ የለኝም። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ፖለቲካ ውስጥ እቆያለሁ።















