ዓለም የሚመገበውን የሩዝ መጠን መቀነስ አለበት?

ሩዝ ከምግብ በላይ ነው። ከግማሽ በላይ ለሚሆነው የዓለም ሕዝብ የባህሉ፣ የወጉ እና የኢኮኖሚ ኅልውናው ምልክት በመሆን የዕለት ተዕለት ኑሮው ዋና አካል ነው።

የፊሊፒንስ ዋና ከተማ በሆነችው ማኒላ የሚኖረው አድሪያን ቢያንካ ቪላኑዌቫ "ሩዝ የእያንዳንዱ የፊሊፒንስ ምግብ ፍጹም የልብ ትርታ ነው።ከዋና ምግብነት በላይ ነው፣ የባህል የማዕዘን ድንጋይ ነው።

"አብዛኞቹ ፊሊፒናውያን በቀን ሦስት ጊዜ ሩዝ ይበላሉ፤ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት። ጣፋጭ እንኳን የሚሰሩት ከሩዝ ነው። የምወደው ምናልባት የሚያጣብቀውን ሩዝ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም በፊሊፒንሳውያን ጣፋጭ ምግቦች ውስጥ የሚያጣብቀው ሩዝ ይካተታል።

ነገር ግን የአየር ንብረት ጫናዎች እየጨመሩ ሲመጡ አንድ አሳሳቢ ጥያቄ አብሮ ብቅ ብሏል። ምናልባት የምንመገበውን ሩዝ መጠን መቀነስ ይኖርብን ይሆን?

የዓለም ዋነኛ ምግብ

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በዓለም ላይ ከ 50,000 በላይ ሊበሉ የሚችሉ የእፅዋት ዝርያዎች ቢኖሩም 15 ሰብሎች ብቻ 90 በመቶውን የዓለም የምግብ ፍጆታ ያሸፍናሉ ሲል አስታውቋል።

ከእነዚህም መካከል የዓለም አርሶ አደሮች በዝናብ አብቅለው በፀሐይ አብስለው ከሚመግቡን መካከል ቀዳሚዎቹ ሩዝ፣ ስንዴ እና በቆሎ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

'ልመደው ልመደው ሆዴ፤ ተወዷል በቆሎ ስንዴ፣ ሩዙን ብላው በዘዴ' ያሉ የዓለማችን ሕዝቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

የዓለም አቀፍ የሩዝ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኢቫን ፒንቶ "ከ50 እስከ 56 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ሩዝን እንደ ዋና ምግቡ የሚመገብ ነው" ብለዋል።

በዚህ ስሌት መሠረት በየቀኑ ወደ አራት ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሩዝን በዋናነት ይመገባሉ ማለት ነው።

ሩዝ በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት በስፋት ይመረታል።

በአፍሪካ ያለው ተፈላጊነት እያደገ ሲሆን በአውሮፓ እና በላቲን አሜሪካም የተለያዩ ዝርያዎች ይመረታሉ። ነገር ግን ሩዝ በዓለም ገበታዎች ላይ በቀላሉ ቢነግስም ከፍተኛ ዋጋ ግን ያስከፍላል።

ውሃ የሚጠማው ሰብል

"ሩዝ በጣም ውሃ የሚጠማ ሰብል ነው" የሚሉት የስፔን የሩዝ አምራች ኢብሮ ፉድስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዣን ፊሊፕ ላቦርዴ ናቸው።

"አንድ ኪሎ ሩዝ ለማምረት ከ3,000 እስከ 5,000 ሊትር ውሃ ይፈጃል፣ ይህም ደግሞ በጣም ብዙ ነው።"

አብዛኛው ሩዝ የሚመረተው በጎርፍ በሚጥለቀለቁ ማሳዎች፣ በተለይም በደቡብ እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ነው።

ይህ ዘዴ ለሰብሉ መልካም ቢሆንም ነገር ግን አናይሮቢክ በመባል የሚታወቀውን ዝቅተኛ ኦክሲጅን ያለበት አካባቢ ይፈጥራል።

ዶ/ር ኢቫን ፒንቶ "ማሳዎች በጎርፍ ሲጥለቀለቁ… ብዙ ሚቴን የሚያመነጩ ረቂቅ ተሕዋስያን ይባዛሉ" ብለዋል።

የዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ ሚቴን የግሪንሀውስ ጋዝ ነው፤ለዓለም ሙቀት መጨመርም 30 በመቶ ተጠያቂ ነው ይላል ።

በሩዝ ላይ ምርምር የሚያካሄደው ተቋም እንደገመተው የሩዝ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚለቀቀው የግብርና ግሪንሃውስ ጋዝ 10 በመቶውን ይይዛል።

አረንጓዴ ስልቶች

መቀመጫውን ዩኬ ያደረገው የስፔን ኩባንያ፣ ቲልዳ "ኦልተርኔቲቭ ዌቲንግ ኤንድ ድራዪንግ (ኤደብሊውዲ)" በመባል የሚታወቀውን የውሃ ቆጣቢ ዘዴን ሲሞክር ቆይቷል።

ከመሬት በታች 15 ሴ.ሜ. የሆነ ቧንቧ ያስቀምጣል፤ ገበሬዎች ማሳቸውን ያለማቋረጥ በጎርፍ ከሚያጥለቀልቁ ይልቅ ውሃ በቧንቧው ውስጥ በማይኖርበት ጊዜ ብቻ ማሳቸውን በመስኖ ያጠጣሉ።

"በተለምዶ በእድገት ጊዜ ውስጥ 25 ዑደቶች አሉ" ይላሉ ላቦርዴ። "የኤደብሊው ዲ ቴክኒክን በመተግበር ወደ 20 መቀነስ ይችላል። ስለዚህ አምስት [የጎርፍ] ዑደቶችን በማቋረጥ የሚቴን ልቀትን መቀነስ ይችላሉ።"

በ2024 ቲልዳ ሙከራውን ከ50 ወደ 1,268 ገበሬዎች አሳድጓል። ውጤቱም አስደናቂ ነበር።

"የውሃውን አጠቃቀም በ27 በመቶ፣ ኤሌክትሪክን በ28 በመቶ እና ማዳበሪያን በ25 በመቶ መቀነስ እንችላለን" ይላሉ ላቦርዴ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የምርት መጠን በ7 በመቶ መጨመሩን ጠቁመዋል።

"ስለዚህ ገቢውን ከፍ ባለ ወጭ ማሳደግ ሳይሆን በዝቅተኛ ወጪ ገቢን ማሳደግ ነው" ብለዋል።

ላቦርዴ የሚቴን ልቀት በ45 በመቶ መቀነሱን አጽንኦት ሰጥተውታል፤ የጎርፍ ዑደቶች የበለጠ ከቀነሱ ይህ በ 70 በመቶ ሊቀንስ ይችላል ብለው ያምናሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ ጫና

ሩዝ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዓለማችን ሕዝቦችን ከፍተኛ ምርት በሚሰጡ ዝርያዎች እየታገዘ ይመግባል።

የአየር ንብረት ለውጥ ግን አሁን ምርቱን አደጋ ላይ ጥሏል።

ሩዝ አብቃይ አካባቢዎች ኃይለኛ ሙቀት፣ ድርቅ፣ ከባድ ዝናብ ወይም የጎርፍ መጥለቅለቅ እያጋጠማቸው ነው።

በሕንድ እአአ በ2024 በሩዝ ምርት ወቅት የሙቀት መጠኑ 53 ዲግሪ ሴልሺየስ ደርሷል። በባንግላዲሽ ተደጋጋሚ እና ኃይለኛ ጎርፍ ሰብሎችን እየጎዳ ነው።

በሩዝ ላይ ምረምሮችን የሚያደርገው ኤእአርአርኤይ መፍትሄዎችን ለማግኘት ወደ ሰፊው የዕጽዋት ዘረ መል ባንክ በመሄድ 132,000 የሩዝ ዝርያዎችን መመልከት መርጧል። አንዱ ቁልፍ ግኝት የሩዝ ተክሎች እስከ 21 ቀናት ድረስ በውሃ ውስጥ እንዲቆዩ የሚያስችለው ዘረ መል ነው።

"እነዚህ ዝርያዎች በጎርፍ በተጥለቀለቁ አካባቢዎች፣ ጎርፉ እስኪቀንስ ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ። ይህ የሚሆነው ደግሞ ምርቱን ሳይጎዳው ነው" ይላሉ ፒንቶ።

እነዚህ ዝርያዎች ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ የባንግላዲሽ አካባቢዎች ተወዳጅነት እየጨመረ መጥተዋል ሲሉ ያክላሉ።

አማራጭ ምግቦች

አንዳንድ መንግስታት ሕዝባቸው ከሩዝ እንዲርቅ ለማበረታታት ሞክረዋል።

በባንግላዲሽ ከ15 ዓመታት በፊት የሩዝ ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ በዘመቻ ድንችን እንደ አማራጭ ለማስተዋወቅ ተሞክሯል።

የዳካ ነዋሪ የሆኑት ሻሪፍ ሻቢር "ድንች እንወዳለን… ግን ከሩዝ ይልቅ ከድንች የተሰራምግብ መመገብ ፈጽሞ የማይታሰብ ነበር።"

ቻይና በ2015 ድንችን እንደ አልሚ ምግብ በማስተዋወቅ ተመሳሳይ ዘመቻ ጀምራለች።

አገሪቱ በ1990ዎቹ የኣለማችን ግንባር ቀደም የድንች አምራች ሆናለች፤ እና በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች ሰዎች ድንችን እንደ ዋና ምግብ ይመገቡ ነበር። ሆኖም ዘመቻው የታሰበውን ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም።

በለንደን የኤስኦኤኤስ ዩኒቨርሲቲ አንትሮፖሎጂስት የሆኑት ጃኮብ ክላይን "በደቡብ ምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ ቻይና ድንች አልፎ አልፎ እንደ ዋና ምግብ ይበላል" ይላሉ።

ነገር ግን በብዙ አካባቢዎች ድንቹ ከድህነት ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።

"በቻይና ደቡብ ምዕራብ ያሉ ሰዎች ድንች እየበሉ እንዳደጉ ይነግሩኛል፤ ያ ደግሞ 'በድህነት ነው ያደግኩት' የሚሉበት አንዱ መንገድ ነው። ድንች ከመብላት ጋር የተያያዘ መገለል አለ" ይላሉ።

አስቸጋሪ ምርጫ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሩዝ በሰዎች ማዕድ ውስጥ ጠልቆ ገብቷል። ለማብሰል፣ ለማከማቸት፣ ለማጓጓዝ ቀላል ብቻ ሳይሆን ጣፋጭም ነው።

ዓለም በዓመት 520 ሚሊዮን ቶን ሩዝ ትበላለች።

በፊሊፒንስ አድሪያን ቢያንካ ቪላኑዌቫ መቀነስ ብትችልም መተው ከባድ እንደሆነ ሳትሸሽግ ተናግራለች።

"ሩዝ መብላት ባልፈልግም፣ ድግስ ተጠርቼ ስሄድ ወይም ሌላ ቤት በእንግድነት ስገኝ ሁልጊዜ ሩዝ ያቀርቡልኛል" ትላለች።

"ትንሽ ሩዝ የምመገብ ይመስለኛል፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ከገበታዬ አላወጣውም፤ ምክንያቱም የዕለት ተዕለት ሕይወታችን አካል ነው።"