ታይላንድ ከምዕራብ አፍሪካ መጣ የተባለውን ዓሳ ከምድሯ ለማጥፋት ዘመቻ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, Thai News Pix
ታይላንድ ውስጥ ከታዩ “እጅግ ወራሪ ፍጡራን” አደገኛው ነው የተባለውን ዓሳ ለማጥፋት ዘመቻ መጀመሩን የታይላንድ ባለሥልጣናት ገልፀዋል።
ይህን ዘመቻ ተከትሎ በርካታ ታይላንዳዊያን ወደ ሐይቆች ገብተው ዓሳውን ማሳደድ የጀመሩ ሲሆን ሳይንቲስቶች ደግሞ የዘረ-መል ማሻሻያ ማድረግ ጀምረዋል።
ሆኖም አካባቢን ይበክላል የተባለው ብላክቺን ቴላፒያ የተባለው ዓሳ አሁንም መስፋፋቱን ቀጥሎ በ17 ግዛቶች ተዳርሷል።
የሀገሪቱ ፓርላማ እያስደረገ ባለው ጥናት እንዴት ሊስፋፋ እንደቻለ ለማጣራት ሙከራ እያደረገ ሲሆን የባንግኮክ ተወካይ ናታቻ “የተበከለ አካባቢ ለቀጣዩ ትውልድ አናስተላልፍም” ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ይህ ከምዕራብ አፍሪካ መጣ የተባለው ዓሳ እንዴት በታይላንድ ሊስፋፋ ቻለ? ዓሳውን ማጥፋትስ ይቻላል?
ታይላንድ ብላክቺን ቲላፒያ በተሰኘው ዓሳ ወረራ ሲፈፀምባት ይህ የመጀመሪያው ባይሆን በቅርቡ የተከሰተው ግን ከዚህ ቀደም ከታዩት የላቀ ነው።
የፓርላማ አባሉ ናታቻ እንደሚሉት ይህን ወረርሽኝ ለማስቆም 10 ቢሊዮን የታይ ባት አሊያም 293 ሚሊዮን ዶላር ሊጠይቅ ይችላል።
አሁን ትልቅ ችግር የሆነው ብላክቺን ቲላፒያ ለታይላንድ የውሀ ውስጥ ሕይወት እጅግ አስፈላጊ የሚባሉ ትናንሽ ዓሳዎች፣ ሽሪምፕ እና ስኔይል ላርቭ የተባሉ የውሀ ውስጥ እንስሳትን እያሳደደ መብላቱ ነው።
ላለፉት ወራት የታይላንድ መንግሥት ዜጎች ብላክቺን ቲላፒያን እንዲያጠምዱ እያበረታታ ሲሆን ዓሳው ወደ ወንዞች እና ትናንሽ ኩሬዎችም መዝለቅ ጀምሯል።
ዓሳውን ጨዋማ እና ንፁህ በሚባሉ ሐይቆች እና ወንዞች ውስጥ መኖርና መስፋፋት ይችላል።
የታይላንድ መንግሥት ይህን ዓሳ ለሚያጠምዱ ሰዎች ገንዘብ ለመስጠት ቃል የገባ ሲሆን በአንድ ኪሎ ግራም 15 ባት አሊያም 0.42 ዶላር ይከፈላቸዋል።
ይህን ተከትሎ የባንግኮክ ከተማ ነዋሪዎች ቦቴያቸውን አጥልቀው ወደ ከተማዋ ወንዞች ዘልቀው በመግባት ዓሳውን ማጥመድ ተያይዘውታል።
በዚህ ያልተገቱት ባለሥልጣናት ብላክቺን ቲላፒያ የተባለውን ዓሳ አሳደው የሚበሉት ኤዢያን ሲባስ እና ሎንግ-ዊስከርድ ካትፊሽ የተባሉትን ዓሳዎች መልቀቅ ጀምረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Thai News Pix
ነገር ግን ይህ ዓሳ በጣም በፍጥነት የሚባዛ ሲሆን ሴት ዓሳዎች በአንድ ጊዜ 500 መቶ ጨቅላ ዓሳዎች መጣል ትችላለች።
የሀገሪቱ ሳይንቲስቶች በዘረ-መል የተሻሻለ እና ዘር መተካት የማይችል ብላክቺን ቲላፒያን ቤተ-ሙከራ ውስጥ አዳቅለው በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት መገባደጃ ለመልቀቅ አስበዋል።
ነገር ግን የሕዝብ እንደራሴው ናታቻ የታይ መንግሥት ከዚህም በላይ ማድረግ ይገባዋል ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ይህ ከሌሎች ዓሳዎች ለመለየት የማይቸግረው ዓሳ እንዴት ወደ ታይላንድ ሊመጣ እንደቻለ በግልፅ ባይታወቅም ከ14 ዓመታት በፊት አንድ የምግብ አምራች ኩባንያ አምጥቶት ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ።
ቻሮን ፖክፋንድ ፉድ የተባለው ኩባንያ የእንስሳት መኖ አምራች ሲሆን የሽሪምፕ እና የእንስሳት ተዋፅዖ ምመረቻ አለው። ኩባንያ በ2010 ከጋና 2 ሺህ ዓሳዎችን አስመጥቶ የነበረ ሲሆን ሁሉም ዓሳዎች ሞተው በስርዓቱ ተቀብረዋል ይላል።
ነገር ግን ከሁለት ዓመት በኋላ በታይላንድ የብላክቺን ቲላፒያ ወረርሽኝ ተከሰተ። ወረርሽኙ ከተከሰተባቸው ሥፍራዎች መካከል አንዱ የኩባንያው ቤተ-ሙከራ የሚገኝበት አካባቢ አንዱ እንደሆነ ፒቢኤስ የተባለው ሚድያ ዘግቧል።
ቢሆንም ኩባንያው የሚቀርብበት ክስ በማስተባበል ለወረርሽኙ ተጠያቂ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል።
አንዳንድ መላ ምቶች ደግሞ የዓሳው ዝርያ ወደ ታይላንድ በድብቅ ገብቶ ሊሆን ይችላል ይላሉ። አሁን ጥያቄው ታይላንድ ይህን ዓሳው ከምድሯ ማጥፋት ትችላለች ወይ የሚለው ነው?












