በቻይና የኮቪድ ወረርሽኝ የመጀመሪያ የእንቅስቃሴ ገደቦችን የዘገበችው ጦማሪ ልትፈታ ነው

ቭሎገሯ ዣን ዣንግ

የፎቶው ባለመብት, YouTube

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መነሻ የሆነችውን ውሃን ከተማ ሁኔታ በመዘገቧ በእስር ላይ የነበረች ቻይናዊቷ ጦማሪ የአራት ዓመት ፍርዷን በማጠናቀቅ ሰኞ እንድትፈታ ቀጠሮ ተይዞላት እንደነበር ደጋፊዎቿ ተናገሩ።

ዝሃን ዣንግ ስለመፈታቷ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ባለስልጣናቱ ዣንግ ስላለችበት ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ ላይሰጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የ40 ዓመቷ የቀድሞ የህግ ባለሙያ በኮቪድ-19 ዘገባቸው ምክንያት ከቻይና ባለስልጣናት ችግር ከገጠማቸው በርካታ ተሟጋቾች አንዷ ናት።

የተወሰኑት ሲታሰሩ ሌሎቹ ደግሞ ጠፍተዋል።

በኋላም “ሁከት በማነሳሳት እና ችግርን በመፍጠር” ጥፋተኛ ሆና ተገኝታለች።

ይህ ክስ በርካታ የቻይና ተሟጋቾች የሚከሰሱበት ወንጀል ነው።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዣንግ የተከሰሰችበት ትክክል እንዳልሆነ ሲናገሩ ቆይተዋል።

ጤንነቷ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ እንድትፈታም ሲሟገቱ ነበር።

ዣንግ ከእስር ከተፈታች በኋላም "ከፍተኛ ስጋት ሊደቀንባት" እንደሚችል የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ቡድን ባልደረባ አሌክሳንድራ ቢኤላኮውስካ ይናገራሉ።

“ቻይና ውስጥ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞች የእስር ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ በቁም እስር ወይም በክትትል ውስጥ ይቆያሉ” ሲሉ ያስረዳሉ።

"በእውነቱ ከሆነ ምንም አዲስ ነገር የሚኖር አይመስለኝም። ምናልባትም በሚስጥራዊ ቦታ ይዘዋት ሊቆዩ ይችላሉ ወይም ለተወሰነ ጊዜ ከዕይታ ያርቋታል" በማለት ገልጸዋል

ዣንግ እንድትፈታ ብዙዎች ጠይቀዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዣንግ ጠበቆች አንዷ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ብትፈታም “የግል ነጻነቷ አሁንም እንደሚገደብ እና ከወላጆቿ ጋር በሻንጋይ እንደምትኖር ተናግረዋል።

ዣንግ የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተበት 2020 ወቅት ከሻንጋይ ተነስታ ወደ ዉሃን በማቅናት በበጎዳናዎች እና በሆስፒታሎች ያየችውን ነገር በመዘገብ ትታወቃለች።

የቀጥታ ስርጭቶቿ እና ቪዲዮዎቿ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊው ይታዩ ነበር። በዚህም ምክንያት ከባለስልጣናት ተደጋጋሚ ዛቻ ቢደርስባትም ዘገባዋን አላቆመችም ነበር።

በቀጥታ ከተለቀቁት ቪዲዮዎቿ በአንደኛው "ቀረጻውን አቁሚ ካልሆነ ታበሳጭኛለሽ” ሲል የሚያስጠነቅቃትን ባለስልጣን ስትቀርጽ ታይታለች።

"ምናልባት ዓመጸኛ ነፍስ ነው ያለኝ ... እውነቱን እየዘገብኩ ነው። ለምን እውነቱን ማሳየት አልችልም?" ስትል በአንድ ቃለ ምልልስ ተናግራለች።

"ይህች ሀገር ወደ ኋላ መመለስ ስለሌለባት የማደርገውን አላቆምም።” ብላም ነበር።

ይህ ከመታሰሯ በፊት የሰጠችው የመጨረሻ ቃለ ምልልስ ነው ተብሎ ይታሰባል።

ዣንግ በአውሮፓውያኑ ግንቦት 14 ቀን 2020 ደብዛዋ እንደጠፋ ከመዘገቡ በፊት ከ100 በላይ ቪዲዮዎችን በዩቲዩብ ቻናል፣ ዊቻት እና ትዊተር ላይ ለጥፋለች።

ባለስልጣናት በሻንጋይ ፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋሏን በቀጣዩ ቀን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ዓመት ህዳር ወር ላይ ክስ ተመስርቶባት በቀጣዩ ወር ተፈርዶባታል።

ዣንግ በመጀመሪያዎቹ የእስር ወራቷ የረሃብ አድማ ብታደርግም በግዳጅ በቱቦ እንድትመገብ መደረጉን ጠበቃዋ ተናግረዋል።

እስከ ሐምሌ 2023 ድረስም በከፊል ረሃብ አድማ ላይ ቆይታለች። ክብደቷም ከመታሰሯ በፊት ከነበረበት በግማሽ ቀንሶ ወደ 37 ኪሎ ግራም አሽቆልቁሏል።

በከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በጨጓራ እና በዝቅተኛ የነጭ የደም ሴል ችግር እየተሰቃየች ነበር ተብሏል።

“በዉሃን ከተማ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ለህብረተሰቡ ለማሳወቅ ህይወቷን በድፍረት አደጋ ላይ የጣለችው ጋዜጠኛ ዣንግ ዣን ህክምና ካላገኘች ህይወቷ ሊያልፍ ይችላል” ሲል ድንበር የለሹ የጋዜጠኖች ቡድን ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

በቻይና ህግ ባለሙያ የሆኑት ጀሮም ኮኸን በበኩላቸው ዣንግን በተመለከተ ወሳኙ ነገር ከእስር ከተፈታች በኋላ የሚሆነው ጉዳይ ነው።

"አብዛኞቹ ከእስር የተለቀቁት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መደበኛ ባልሆነ ጫና ጸጥ እንዲሉ ይደረጋል። አንዳንዶች ከአገር በመውጣት በቻይና ስለተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት በማድረግ ስኬታማ ቢሆኑም እነዚህ ጥቂት ብቻ ናቸው" ብለዋል ፕሮፌሰር ኮኸን።

የዣንግ ጠበቃ በበኩላቸው እስር ላይ እያለች ፖሊስ ቤተሰቧን ደጋግሞ በመጎብኝት ጉዳዩን ከሌሎች አካላት ጋር እንዳይወያዩ ትእዛዝ ሰጥተዋቸዋል ብለዋል።