አንድ ውሻ በዝንጀሮ ፈንጣጣ መያዙን የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ ውሻ ከባለቤቱቶቹ በተላለፈ የዝጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ መጠቃቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
ይህ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የበሽታው ስርጭት ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ ራሳቸውን ከቤት እንስሳቶቻቸውም ጭምር ማግለል እንዳለባቸው የሚያሳይ እንደሆነም የጤና ሃላፊዎቹ አስታውቀዋል።
ሌሎች እንስሳትን የመበከል አደጋን ለመቀነስ ቆሻሻን በጥንቃቄ ማስወገድ እንደሚያስፈልግ የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል።
ውሾች በሽታውን ወደ ሌሎች ውሾች ወይም ወደ ሰዎች ያስተላልፉ እንደሆነ የሚያረጋግጥ መረጃ እስካሁን እንደሌለም ባለሞያዎች ገልጸዋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በቆዳ-ለቆዳ ንክኪ እና ሰዎች ጨርቆችን ጨምሮ አልጋ ወይም ፎጣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር በጋራ ሲጠቀሙ የሚተላለፍ በሽታ ነው።
በአሁኑጊዜ በዓለም ዙሪያ ወደ 35,000 የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን አብዛኛዎቹ በአውሮፓ፣ በሰሜን እናበደቡብ አሜሪካ ይገኛሉ ። እስካሁን ከበሽታው ጋር በተያያዘ 12 ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት ተደርጓል።
የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ሃምሌ ወር ውስጥ ነበር የዝንጀሮ ፈንጣጣን አለማቀፍ የጤና አደጋ ሲል ያወጀው።
የመጀመሪያው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ከሰው ወደ ውሻ የተላለፈው በፓሪስ ከተማ ሁለት አንድ ላይ በሚኖሩ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ወንዶች ቤት ውስጥ ነው። ግለሰቦቹ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምልክቶች ማሳየት ከጀመሩ ከ 12 ቀናት በኋላ ነበር በውሻቸው ላይም ምልክቶችን ማየት የጀመሩት።
ባለሞያዎች ያደረጉት የዘረመል ትንታኔ እንደሚያሳየው ውሻውን ያጠቃው ቫይረስ ግለሰቦቹን ካጠቃው ጋር ቫይረስ ጋር ተመሳሳይ ነው።
የውሻው ባለቤቶችም ውሻው አብሯቸው ሲተኛ እንደነበር ተናግረዋል።
በአለም የጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምላሽ ሰጪ ቡድን ውስጥ የቴክኒካል ስራዎች መሪ የሆኑት ዶ/ር ሮሳምንድ ሉዊስ “ይህ ከዚህ በፊት ሪፖርት ያልተደረገ ብሎም ለመጀመሪያ ግዜ የመዘገበ ወደ ውሻ ያጋጠመ ስርጭት ነው ብለን እናምናለን’’ ብለዋል።
በተቋሙ የድንገተኛ የጤና አደጋዎች ሀላፊ የሆኑት ዶ/ር ማይክ ራያን “ጉዳዩ ያልተጠበቀ አይደለም” ብለዋል።
ነገር ግን በሽታው ከአንድ ዝርያ ወደ ሌላው መዘዋወሩ እጅግ እንደሚያሳስባቸውም ተናግረዋል። አክለውም አንድ በሸታ ወደ አዲስ የእንስሳ ከተላለፈ በኋላ እንደሚላመድ ብሎም እና በውስጡም ወደ አዲስ ዝርያ እንዲለወጥ እድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
“ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመ ስርጭት ነው። ስለሆነም ውሾች ሊበከሉ ይችላሉ ማለት ነው። ነገር ግን ውሻው ሌሎች ውሾችን ሊበክል ይችላል ወይም ወደ ሰዎች ያስተላልፋል ማለት አይደለም’’ ሲሉ የአለም የጤና ድርጅት የዓለም አቀፍ ተላላፊ በሽታዎች ስጋት ዝግጁነት ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ሲልቪ ብሪያንድ ተናግረዋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመከላከል በመላው አለም ያለው የክትባት አቅርቦት እስካሁን ድረስ ውስን ነው።
ባለፈው ሳምንት ብቻ በበሽታው ተይዘው ሪፖርት የተደረጉ ሰዎች ቁጥር በ 20 በመቶ ጭሯል። ይህም ከሳምንት በፊት ከነበረው በ20 በመቶ ብልጫ አለው።
እስካሁን አብዛኛው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሲታይ ወንድ የተመሳሳይ ጾታ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።












