ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስምንት የእስራኤል ወታደሮች ሊባኖስ ውስጥ ከሄዝቦላህ ጋር በተደረገ ውጊያ ተገደሉ
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በተደረገ ውጊያ ስምንቱ ወታደሮቹ መገደላቸውን ገለጸ። አባላቱ የተገደሉት በታጣቂው የሄዝቦላህ ቡድን ላይ የምድር ዘመቻ ከጀመረ ወዲህ መሆኑን ጦሩ አስታውቋል።
በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በበኩሉ በጦርነቱ ወቅት የእስራኤልን ታንኮች ማውደሙን እና ጦሩን መመለስ የሚችል በቂ ኃይል እና የጦር መሣሪያዎች እንዳሉት ገልጿል።
የእስራኤል ጦር በሊባኖስ የድንበር መንደሮች ውስጥ “የአሸባሪ መሠረተ ልማት” የሚላቸውን ተቋማት ለማፍረስ ተጨማሪ እግረኛ እና የታጠቁ ወታደሮች ማሰማራቱን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤይሩት ማዕከላዊ ግዛት ባቹራ በምትባል አካባቢ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች ሲሞቱ 8 መቁሰላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ዒላማ የተደረገው ሕንጻ ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያለውን የጤና ጣቢያ የያዘ ሲሆን፣ ከሊባኖስ ፓርላማ እና ከተባበሩት መንግሥታት ክልላዊ ዋና መሥሪያ ቤት በተወሰኑ ሜትሮች ብቻ የሚርቅ ነው ተብሏል።
ይህ እስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ማዕከላዊ ቤይሩት አቅራቢያ ያደረሰችው ጥቃት ሲሆን ሌሎቹ ጥቃቶች ደግሞ በደቡባዊ የዳሂህ ዳርቻ ላይ ተፈጽመዋል።
የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ረቡዕ ማምሻውን እንዳስታወቀው ከሆነ በ24 ሰዓታት ውስጥ እስራኤል በአገሪቱ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 46 ሰዎች ሲገደሉ 85 ቆስለዋል ቢልም፣ ምን ያህሉ ሲቪሎች እና ምን ያህሉ ተዋጊዎች እንደሆኑ ግን አልለየም።
ለሁለት ሳምንታት በዘለቀው የእስራኤል ጥቃት ምክንያት የሄዝቦላህ አቅም ተዳክሟል። በጥቃቶቹ 1200 በላይ ሰዎች ሲገድሉ፣ ወደ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑት መፈናቀላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
በጋዛ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተለከትሎ የተጀመረውን ድንበር ዘለል ጦርነት ሙሉ ለሙሉ በማስቆም ዜጎቿን በድንበር አካባቢዎች ወደሚገኙ ቀዬአቸው ለመመለስ በማሰብ እስራኤል ወደ ማጥቃት መሸጋገሯን አስታውቃለች።
ሄዝቦላህ በሊባኖስ ውስጥ ትልቅ ሥልጣን ያለው የሺዓ እስላማዊ የፖለቲካ፣ ወታደራዊ እና ማኅበራዊ ድርጅት ነው። በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች አገራት በአሸባሪነት ተፈርጇል።
የእስራኤል ወታደሮች ወደ ሊባኖስ በገቡ በሁለተኛው ቀን ከሄዝቦላህ ተዋጊዎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ገጥመዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሆነ በበርካታ የደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢዎች በአውሮፕላኖች ድጋፍ የሚደረግላቸው ወታደሮች “አሸባሪዎችን በማስወገድ እና የሽብር መሠረተ ልማቶችን ከቅርብ ርቀት ላይ አፈራርሰዋል” ብሏል።
ጦሩ ስምንት ወታደሮቹ መገደላቸውን በኋላ ላይ አስታውቋል። አብዛኛዎቹ ደግሞ የስመ ገናናው ኢጎዝ እና የጎላኒ የጦር ክፍል ኮማንዶዎች ናቸው ተብሏል።
ስድስቱ በሄዝቦላህ ታጣቂዎች የደፈጣ ጥቃት መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ሁለቱ ደግሞ በሞርታር ተኩስ ተገድለዋል።
ሄዝቦላህ በበኩሉ ረቡዕ ዕለት በአንድ የድንበር መንደር በተደረገ ውጊያ ታጣቂዎቹ ፀረ-ታንክ ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል ኮማንዶዎች በመተኮስ በርካቶቹን መግደላቸን እና ማቁሰሉን ገልጿል።
በካፍር ኪላ ዳርቻ ላይ ደግሞ ወታደሮች በፈንጂ እና በጥይት ዒላማ መደረጋቸውን እንዲሁም በማሩን አል-ራስ አቅራቢያ ደግሞ ሦስት የእስራኤል ሜርካቫ ታንኮች በሚሳኤል መውደማቸውንም ገልጿል።
ሄዝቦላ በደቡባዊ ሊባኖስ ሰፊ የመሬት ውስጥ ለውስጥ ዋሻዎችን ጨምሮ በርካታ መሠረተ ልማቶችን ለዓመታት ገንብቷል። አካባቢውን ጠንቅቀው የሚያውቁ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችም አሉት።
ለተገደሉት ስምንት ወታደሮች ክብር የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “እኛን ለማጥፋት ከምትፈልገው የኢራን የክፋት መረብ ጋር በተደረገው ከባድ ጦርነት” ውስጥ ወድቀዋል ብለዋል።
“ይህ አይደገምም ምክንያቱም በአንድነት እንቆማለን። በፈጣሪ እርዳታም አብረን እናሸንፋለን” ሲሉ አክለዋል።
ባለፈው አርብ በቤይሩት የተገደሉትን የሄዝቦላህን መሪ ሐሳን ናስራላህን እና የኢራን ወታደራዊ ከፍተኛ አዛዥን ግድያ ለመበቀል ኢራን ማክሰኞ ምሽት ከ180 የሚበልጡ የባላስቲክ ሚሳዔሎችን ብታስወነጭፍም አብዛኞቹን መከላከል የቻለው አገሪቱ የአየር መከላከያ ሥርዓት ከአንድ ቀን በኋላም በድጋሚ በሥራ ተጠምዶ ውሏል።
ረቡዕ ዕለት ብቻ ከ240 በላይ ሮኬቶች ከደቡብ ሊባኖስ ወደ ሰሜን እስራኤል ተተኩሰዋል ሲል የእስራኤል ጦር ገልጿል።
በሊባኖስ የሚካሄደው የምድር ዘመቻ የሄዝቦላህን አቅም የሚያዳክም እና ተዋጊዎቹን ወደ ኋላ የሚገፋቸው ከመሆኑም በላይ ወደ 60 ሺህ የሚጠጉ እስራኤላውያን በድንበር አቅራቢያ ወደ ሚገኘው ቤታቸው እንዲመለሱ ያስችላቸዋል ሲሉ ኔታንያሁ አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የምታደርገውን የአጸፋ ጥቃት እንደማይደግፉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናግረዋል። ለኢራን ጥቃት በሚሰጠው ምላሽ ዙሪያ እስራኤል ምን እንደዳሰበች እንደሚወያዩ ተናግረዋል።
በቤይሩት የሄዝቦላህ ጠንካራ ምሽግ በሆነው ደቡባዊው ዳሂህ አካባቢ ከባድ የአየር ድብደባ ተፈጽሟል። የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ነዋሪዎች ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ካላቸው ሕንጻዎች አካባቢ ለቀው እንዲወጡ ቀደም ብሎ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
በሄዝቦላህ አስተባባሪነት ረቡዕ ጠዋት የቢቢሲ ቡድን ውድመት በደረሰበት አካባቢ የሚዲያ ጉብኝት አድርጓል።
በአንድ ወቅት ሞቅ ደመቅ ይል የነበረው ዳሂህ የተባለው ሰፈር አሁን የሙት መንደር መስሏል። ሱቆች ተዘግተዋል፤ መንገዶች ጭር ብለዋል፤ አብዛኛዎቹም ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል።
በጉብኝት ከተደረገባቸው ቦታዎች አንዱ ሰኞ ዕለት ጥቃት የደረሰበት የሲራት ቲቪ ዋና መሥሪያ ቤት ነው። ሙሉ ለሙሉ ከመውደሙም በላይ በአቅራቢያው ያሉ ሕንፃዎች የደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት የጥቃቱን ክብደት ያመለክታል።
ከፍርስራሹ የሚወጣ ጭስ ከመታየቱም በላይ በአየር ላይ ከባድ ጠረን ነበር። በጉብኝቱ ወቅትም የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች ሰማይ ላይ ሲበሩ ድምጻቸው ይሰማ ነበር።
የሐሳን ናስረላህ ፎቶ የታተመባቸው በርካታ ፖስተሮች በየቦታው ተሰቅለዋል። “አንድም ባንዲራችን አይወድቅም” የሚል ጽሑፍም በአንደኛው ፖስተር ላይ በጉልህ ይነበባል።
እስራኤል ዒላማ ያደረገችው ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉትን ሳይሆን የሲቪል ሕንፃዎችን ነው ብሏል ሄዝቦላህ። እስራኤል ደግሞ ቡድኑ በመኖሪያ አካባቢዎች የጦር መሳሪያዎችን እና ጥይቶችን ይደብቃል ስትል ትከሳለች።
የአሜሪካ እና የእስራኤል ባለሥልጣናት ግማሹ የሄዝቦላህ የጦር መሳሪያ ወድሟል፤ አመራሩም ፈርሷል ብለው ያምናሉ።
የሄዝቦላህ ቃል አቀባይ መሐመድ አፊፍ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም።
“ቡድኑ በፍጥነት ጥንካሬውን እያገኘ ነው ማለት እችላለሁ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። “የቡድኑ አመራር፣ የትዕዛዝ እና የቁጥጥር መዋቅሩ እንዲሁም ደግሞ የሮኬቶች አቅርቦቱ በሙሉ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው” ብለዋል።
“ፈጣሪ ከፈቀደ ጠላት የሆነችው የእስራኤል ጦር ወደ ሊባኖስ ሲሻር ሽንፈትን እናከናንበዋል” ሲሉ አክለዋል።
ከዳሂህ በተጨማሪ የሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ ከሚባሉት ደቡብ እና ምሥራቃዊ የቤካ ሸለቆ በርካታ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
የቤይሩት ሰማዕታት አደባባይ በርካታ መሄጃ የሌላቸው ቤተሰቦች መሰባሰቢያ ሆኗል።
አንዳንድ ድንኳኖች ግድግዳዎች ላይ ቢዘረጉም ብዙዎቹ ግን በአቅራቢያው በሚገኘው መሐመድ አል-አሚን መስጊድ ደረጃዎች ላይ መሬት ላይ ፍራሾች አንጥፈው እየተኙ ነው።
የ55 ዓመቱ መሐመድ ከአምስት ቀናት በፊት ከባለቤታቸው፣ ከልጃቸው እና ከሰባት የልጅ ልጆቻቸው ጋር በስፍራው ደርሰዋል። ወደ መጠለያ ካምፕ ለመግባት ቢሞክሩም ግን ቦታ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
“የምንሄድበት ቦታ የለንም” ብለዋል። የሚመገቡትን አላጡም። ዳይፐር፣ ወተት እና መድኃኒት አለማግኘታቸው ግን ለችግር ዳርጓቸዋል።
የ26 ዓመቱ መሐመድ ደግሞ ከሦስት ልጆቹ ጋር ከስፍራው ደርሷል።
በዳሂህ መንደር ይሠራ የነበር ቢሆንም ሁሉም ሱቆች በመዘጋታቸው ሥራ አጥቻለሁ ብሏል። “ምንም ሥራ የለም” ሲል አክሏል።