ኤክስ ሐሰተኛ መረጃን ከማሰራጨት ጋር በተያያዘ ውዝግብ ብራዚል ውስጥ ታገደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቀድሞው ስሙ ትዊተር እየተባለ የሚታወቀው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ኤክስ፣ አዲስ የብራዚል ተወካዩን እንዲያሳውቅ የአገሪቷ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ ባለማክበሩ ታገደ።
ዳኛ አሌክሳንደር ዲ ሞሬስ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ ሁሉንም የፍርድ ቤቱን ትዕዛዛት እስከሚያከብር እና ያለበትን ቅጣት እስከሚከፍል ድረስ ሙሉ በሙሉ ታግዶ እንዲቆይ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ውዝግቡ የጀመረው ባለፈው ሚያዚያ ወር ዳኛው ሐሰተኛ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ነበሩ የተባሉ በርካታ የኤክስ ገጾች እንዲታገዱ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ተከትሎ ነው።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎም የኤክስ ባለቤት ኤሎን መስክ “የመናገር ነጻነት የዲሞክራሲ መሰረት ነው፤ በብራዚል ሕዝብ ያልተመረጡት ዳኛ ለፖለቲካ ጥቅም ሲሉ ይህንን መብት እያፈኑ ነው።” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ በአገሪቷ ውስጥ ከሚገኙ 200 ሚሊዮን ሕዝቦች መካከል 10 በመቶ ያህል ተጠቃሚ እንዳለው የሚገመት ሲሆን፣ቅዳሜ ጠዋት ላይ አንዳንድ የኤክስ ተጠቃሚዎች ማኅበራዊ መድረኩን መጠቀም እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ኤክስ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የብራዚል ተወካዩ ፣ድርጅቱ ‘ሳንሱር’ ያለውን እና በአገሪቱ ሕገ ወጥ መሆኑን የገለጸውን ትዕዛዝ ካላከበረች እንደምትታሰር ዛቻ ከደረሰባት በኋላ ቢሮውን መዝጋቱን አስታውቆ ነበር።
ዳኛ ሞሬስም ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የተከሰሱና አብዛኞቹ የቀድሞው የቀኝ ክንፍ ፕሬዚደንት ጄር ቦልሶናሮ ደጋፊዎች የሆኑ የኤክስ ገጾች ምርመራ እየተደረገባቸው ስለሆነ እንዲዘጉ ትዕዛዝ የሰጡ ሲሆን፣ እነዚህ ገጾች እንደገና የሚከፈቱ ከሆነ የድርጅቱ ሕጋዊ ተወካይ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ኤክስ ይህንን ትዕዛዝ ባለማክበሩ ቅጣት እንደሚጣልበት ዳኛው የገለጹ ሲሆን፣ ኩባንያውና መስክ ግን ዳኛውን ‘ግራ ክንፍ’ ናቸው በማለት የብራዚል የመንግሥት ተቺዎችን ተቀላቅለዋል።
በቢሊየነሩ ላይ መሰል ክስ ሲቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የኤክስ ቁጥጥርን በተመለከተ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ የነበረ ሲሆን ከዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር ጋርም የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር።
ማኅበራዊ መድረኩን የማገድ ትዕዛዙን የሚያስፈፅመው የብራዚል ቴሌኮሚዩኒኬሽን ኤጀንሲ ኃላፊም ‘ ትዕዛዙን ለመፈፀም ዝግጁ መሆናቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ዳኛ ሞሬስ እንደ አፕል እና ጉግል ያሉ ድርጅቶች ከመተግበሪያቸው ማከማቻ [ስቶር] ላይ ኤክስን እንዲያስወግዱ እና ከአይኦኤስ እና አንድሮይድ ሥርዓት ላይ እንዲያስወግዱ የ5 ቀን ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል።
ዳኛው ጨምረውም ኤክስን ለመጠቀም ቪፒኤን የሚጠቀሙ ሰዎች እና ድርጅቶች 6.7 ሺህ ፓውንድ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
እንደ ዳኛው ትዕዛዝ ከሆነ እገዳው ኤክስ በአገሪቷ አዲስ ሕጋዊ ተወካይ እስከሚሰይም እና የብራዚል ሕግን በመጣስ የተላለፈበትን ቅጣት እስከሚከፍል ድረስ ተግባራዊ ይሆናል።
ኤክስ ቀደም ብሎ ካጋራቸው ጽሑፎች መካከል በአንዱ ግን ይህንን እንደማይፈፅም ገልጿል።
“ በቅርቡ ዳኛ አሌክሳንደር፣የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን ‘ ሳንሱር’ ለማድረግ ሲሉ ያወጡትን ሕገ ወጥ ትዕዛዛቸውን ባለማክበራችን ኤክስ በብራዚል እንዲዘጋ ያዛሉ ብለን እንጠብቃለን” ብሎ ነበር።
“ ዋናው መሠረታዊ ጉዳይ ዳኛ ዲ ሞሬስ የብራዚልን ሕግ እንድንጥስ ነው የሚፈልጉት። እኛ ደግሞ እንደሱ ማድረግ አንፈልግም” ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀደም ብሎ የአገሪቷ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ተከትሎ የመስክ የሳተላይት ኢንተርኔት ድርጅት - ስታርሊንክ የባንክ አካውንት በብራዚል እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል።
ስታርሊንክ በኤክስ ገጹ በሰጠው መልስ ትዕዛዙ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲል ተቃውሞታል።
ዳኛ ሞሬስ በአገሪቷ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ለመገደብ ከወሰኑ በኋላ እውቅናን አግኝተዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከተሎ የቀድሞው ፕሬዝደንቱ ቦልሶናሮን እና ደጋፊዎቻቸው የነበራቸውን ሚና እየመረመሩ ነው።
ባለፈው ዓመትም ቴሌግራም የተወሰኑ ገጾችን እዲዘጋ ለማድረግ ባለመተባበሩ በጊዜያዊነት ታግዶ ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 እና በ2016 የሜታ የመልዕክት መለዋወጫ ዋትስአፕ ፖሊስ የጠየቀውን የደንበኞቹን መረጃ አሳልፌ አልሰጥም በማለቱ በጊዜያዊነት ታግዶ እንደነበር ይታወሳል።












