በየመን በረሃ እየተካሄደ ያለው ዓለም አቀፍ መዘዝ ያለው ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, BBC/Lee Durant
በመካከለኛው ምሥራቅ ደቡብ ምዕራብ ማዕዘን ላይ በምትገኘው የመን ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ዓለም አቀፍ አንደምታ ያለው ነው።
በአገሪቱ ለረዥም ጊዜ የተንሰራፋው የእርስ በርስ ጦርነት ችላ ሊባል የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ይነገራል።
ይህ ግጭት ከቴህራን እስከ ሪያድ የሚዘረጋው ሰፊ ቀጣናዊ ግጭት አካል ሲሆን፣ ባለፈው ቅዳሜና እሑድ የሁቲ ሚሳዔሎች የሳዑዲ አረቢያን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች በመምታት የሰዎች ሞትና የንብረት ጉዳት አድርሰዋል።
የሁቲዎች ጥቃት ከአስር ዓመታት በላይ ወዲህ በሳዑዲ መሬት ላይ ከተፈፀሙት ጥቃቶች ሁሉ ከፍተኛውን ሞት ያስከተለ ሲሆን፣ በቀጣናው ውስጥ የድንጋጤ ማዕበል ፈጥሯል፤ የሳዑዲን የደኅንነት ሁኔታም ጥያቄ ውስጥ ከትቷል።
ለዓለም አቀፍ የባሕር መጓጓዣ መስመር ስጋት ሆነው የቆዩት የሁቲ ታጣቂዎች፣ ለሳዑዲ አረቢያ ደግሞ ይበልጥ ስጋት ሆነዋል።
በሌላ በኩል፣ የሳዑዲ አረቢያ ቀጣናዊ ተቀናቃኝ የሆነችው ደጋፊያቸው ኢራን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጫናዋ እንዲበረታ እንደ መሣሪያ እያገለገሏለት ነው።
የየመን መንግሥትን ከሚደግፉ ኃይሎች የአንዱ ወታደራዊ አዛዥ የሆኑት ተውፊቅ አል ሃቡን በይዞታቸው የሚገኝ አካባቢን የቢቢሲዋን ዘጋቢ ኦርላ ጌሪንን አስጎብኝተዋታል።
በጉብኝታቸው ወቅት ከእግራቸው ሥር የነበሩ የብረት ስብርባሪዎችን አሳይዋት። ተመትቶ የወደቀ የሁቲ ድሮን ክፍሎች ሲሆኑ፣ ድሮኑ ሲ4 (C4) የተባለ ፈንጂ ተሸክሞ እንደነበር ነግረዋታል።
አል ሃቡን የደቡብ ኃይሎች አባል ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን እና በሳዑዲ አረቢያ ድጋፍ የሚደረግለትን የየመን መንግሥት ደግፈው የሚዋጉ እጅግ የላላ ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ጥምረት አካል ናቸው።
በሳዑዲ የአየር ጥቃት ተደግፈው የሚያደርጉት ውጊያ ግን ሁቲዎችን ሊያስቆም አልቻለም።
ሁቲዎች የየመንን መንግሥት አባርረው የአገሪቱን ዋና ከተማ ሰነዓን እአአ በ2014 ከተቆጣጠሩ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል።
ሰነዓን ከተቆጣጠሩ ከአንድ ዓመት በኋላ በሳዑዲ የሚመራ የአረብ አገራት ጥምረት ለዓመታት የዘለቀ የአየር ድብደባ ቢያደርግባቸውም ውጤት ማምጣት አልተቻለውም።

የፎቶው ባለመብት, BBC/Lee Durant
የደቡብ ኃይሎች አዛዡ አል ሃቡን እንደሚሉት፣ 500 ያህል የሁቲ ተዋጊዎች ከፍተኛ ስፍራዎች ላይ ተቀምጠው ቀይ ባሕርን እና የአደን ባሕረ ሰላጤን የሚያገናኘውን ስትራቴጂካዊ የባሕር መስመር ባብ ኤል ማንዳብን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በተለይ ከሳዑዲ ነዳጅ ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ ወሳኝ የሆነውን ይህን ጠባብ የውሃ መተላለፊያ ሁቲዎች መስከረም ወር ላይ ባደረጉት ፈጣን ግስጋሴ ተቆጣጥረው ነበር።
አዛዡ ለቢቢሲዋ ጋዜጠኛ እንደተናገሩት የመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች 85 በመቶ ያህሉን የባብ ኤል ማንዳብ አካባቢ መልሰው ተቆጣጥረዋል።
በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ አንዳንድ ይዞታዎቻቸውን ለቀዋል መባሉን ያስተባበሉት ሁቲዎች የባብ ኤል ማንዳቡን በተመለከተ ግን እስካሁን ምንም አላሉም።
ያም ሆነ ይህ የአገሪቱ መንግሥት ሙሉ ቁጥጥር እስኪኖረው ድረስ በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦትና በዋጋው ላይ የሚኖረው ጫና ይቀጥላል።
ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) እንደሚለው፣ የየመኑ ግጭት መስከረም ወር ላይ ከተባባሰ ወዲህ 200,000 ያህል ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል።
ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ በአረቡ ዓለም ከሚገኙት አገራት በኢኮኖሚ ደካማ በሆነችው አገር መሆኑ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል።
የቢቢሲ ጋዜጠኛዋ የተመለከተቻቸው ሆስፒታሎች ከአቅማቸው በላይ ጫና ተሸክመዋል፤ ሐኪሞች ከውግያ ግንባሮች የሚመጡ የቆሰሉ የመንግሥት ደጋፊ ተዋጊዎችን ለማከም ቀንና ሌሊት ያለማቋረጥ እየሠሩ ነው።
እአአ በ2022 የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ለጥቂት ዓመታት አንጻራዊ መረጋጋት አስገኝቶ ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ ሁቲዎች ኃይላቸው ይበልጥ እየተጠናከረ መሄዱን ቅዳሜና እሑድ በፈፀሙት ጥቃት አሳይተዋል።
አማጺያኑ ታጣቂዎች አብዛኛው የየመን ሕዝብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ላይ ቁጥጥር ያላቸው እንደመሆናቸው፣ አዲስ የሽምግልና ጥረት ከተጀመረ በድርድሩ ላይ ጠንካራ እና ከባድ ቅድመ ሁኔታዎችን ሊያቀርቡ ይችላሉ።




































