ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በነዳጅ ዋጋ መናር ገበያው የደራለት የኤሌትሪክ መኪና አምራቹ ቢዋይዲ
በኢራን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ መጨመር በመላው ዓለም የኤሌትሪክ መኪኖች ያላቸውን ተፈላጊነት እየጨመረው ነው።
የቻይና መኪና አምራቾች ደግሞ ይህንን አጋጣሚ በሚገባ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
ቻይና በዓለማችን የኤሌትሪክ መኪናን በማምረት ቀዳሚ ስትሆን እስካሁን ድረስ ወደ አሜሪካ ገበያ እንድትገባ ባትደረግም በእስያ እና በሌሎች አካባቢዎች ባሉ ሻጮች በኩል በሚመጡ ትዕዛዞች ተጠቃሚ እየሆነች ነው።
ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም የኤሌትሪክ መኪናዎችን በመሸጥ ቴስላን የበለጠው ቢዋይዲ በሌሎች አገሮች የሚያደርጋቸውን ማስፋፊያዎች በሰፊው ቀጥሏል።
"ዛሬ ያለ አሜሪካ ገበያ ማትረፍ እና ስኬታማ መሆን ችለናል" ሲሉ የቢዋይዲ ምክትል ፕሬዝዳንት ስቴላ ሊ በቤይጂንግ አውቶ ሾው ላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአሜሪካ የሚገኙ ደንበኞችን ከመፈለግ ይልቅ ኩባንያው በሌሎች የዓለም ክፍሎች እንደ ብራዚል፣ ዩኬ እና አውሮፓ ያሉ ፍላጎቶችን ማሟላት ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ይናገራል።
ሊ "ደንበኞቻችን የነዳጅ ዋጋ በየቀኑ በጨመረ ቁጥር ያዳኑትን ገንዘብ ያስቡታል። የኤሌትሪክ መኪናዎች በየዕለቱ ገንዘብ መቆጠብ እንዲችሉ አድርጓቸዋል" ብለዋል።
"እውነቱን ለመናገር አሁን ከአቅማችን በላይ ነው። ፍላጎቱ ከአቅርቦታችን በላይ ነው።"
ቢዋይዲ "በከፍተኛ ፍጥነት ቻርጅ የሚደረጉ" ዘመናዊ መኪኖችን ለገበያ አቅርቧል። ሊ "ማርሽ ቀያሪ" ሲሉ የሚጠሯቸው እነዚህ አዳዲስ ምርቶች የኤሌትሪክ ምርቶች ላይ የሚነሱ ቻርጅ የማድረግ ፍጥነትን ጥያቄን ይፈታሉ ብለዋል።
በፍጥነት ቻርጅ ማድረግ በደቂቃዎች ውስት በመቶ ኪሎሜትሮች ፍጥነታቸው እንዲጨምር እንደሚያደርግ እና ይህ ለውጥ ሊ እንደሚሉት ከዚህ ወደም መኪኖቻቸውን ለመግዛት ያመነቱ ደንበኞችን ለማሳመን እንዲሁም ቢዋይዲ በሰፊው ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን እንደሚያስችለው ተናግረዋል።
አሁን በመላው ዓለም ካሉ የመኪና አውደ ርዕዮች ሁሉ ቀዳሚው የሆነው እና በዚህ ዓመት በቤይጂንግ በተካሄደው አውቶ ሾው ላይ ከ1400 በላይ መኪኖች በመቶዎች ከሚቆጠሩ የቻይና እና የሌላ አገር አምራቾች ለዕይታ ቀርበው ነበር።
ቢዋይዲ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመግባት የሚያደርገው ጥረት በየቀጠናው ካሉ የፖለቲካ ውጥረቶች ጋር መታገልን ይጠይቀዋል።
የቻይና የኤሌትሪክ መኪና አምራቾች በዓለም ገበያ ውስጥ ታሪፎችን እንዲሁም የተቆጣጣሪዎች መመሪያዎችን ይጋፈጣሉ።
በተለይ ይህ ግዙፍ ገበያ ባለበት አሜሪካ ጠንከር ያለ ነው።
አሜሪካ የቻይና መንግሥትን ድጎማን እንዲሁም የዳታ ከለላ እና ብሔራዊ ደህንነትን በማንሳት ስጋቷን ትገልጻለች።
ነገር ግን ሊ በሌሎች አካባቢዎች ዩኬን ጨምሮ ተቀባይነት ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደም ተፎካካሪዎቻቸውን ለማሸነፍ በሚያደርጉት የዋጋ ቅነሳ ይታወቁ የነበሩት የቻይና ኩባንያዎች አሁን በቴክኖሎጂ በተለይ ደግሞ በባትሪ፣ ቻርጅ የማድረጊያ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም ሶፍትዌሮችን በመጨመር የፉክክር አድማሳቸውን አስፍተዋል።
የመኪና አምራች ኩባንያ ብቻ አይደለንም የሚሉት ሊ፣ የዓለማችን አንድ ሦስተኛን የስማርት ፎን ቁሳቁሶች እናመርታለን፣ በባትሪ ምረቶች፣ በሶላር ፓናል፣ በአውቶብሶች እና የጭነት መኪና ምርቶች ቀዳሚዎቹ ነን። ስለዚህ "ቢዋይዲ ሁሉ ነገር ነው" ይላሉ።
ሮቦቶች እና በራሪ መኪኖች
በቻይናው የመኪኖች አውደ ርዕይ ላይ በሌላ ኩባንየዓዎች የቀረቡት ፈጠራን ያሳዩ እና ከመኪና የተሻገሩ ነበሩ።
የቻይናው ዤ ፔንግ አዲስ ስድስት ሰው የሚጭኑ ኤስዩቪ የኤሌትሪክ መኪናዎችን ለዕይታ ያቀረበ ሲሆን፣ በቅርቡ ሂማኖይድ ሮቦቶችን አምርቶ ይፋ እንደሚያደግ፣ ወደፊት ደግሞ የሚበርሩ መኪኖችን ለመስራት ዕቅድ እንዳለው ይፋ አድርጓል።
ከዚህ ቀደም የቻይናን ገበያ ተቆጣጥረውት የነበሩት እንደ ቮክስዋገን፣ ቶዮታ እና ፎርድ ያሉ የሌላ አገር መኪና አምራቾች ፍጥነቱን ለመከተል ሲቸገሩ አንዳንዶቹም ከአገሪቱ ኩባንያዎች ጋር በትብብር ለመስራት ሲስማሙ ታይተዋል።
ቢኤምደብሊው ከባትሪ አምራቹ ሴኤቲኤል ጋር፣ ቮክስዋገን ከዤፒንግ እንዲሁም አውዲ የሁዋዌን የስርዓት ለመጠቀም መስማማታቸውን አስታውቀዋል።
በቻይና ውስጥ ፉክክር ከፍተኛ ሲሆን በደርዘን የሚቆጠሩ አምራቾች በከባድ የዋጋ ጦርነት እና ፈጣን የምርት ዑደቶች ውስጥ ተሳትፈዋል።
እንደ ቢዋይዲ ላሉ የገበያ አውራዎች እንኳን፣ የአገር ውስጥ ገበያ ተግዳሮቶችን ደቅኖባቸዋል።
የዋጋ ውድድር ከፍተኛ በመሆኑ ዋጋ እነዲቀንስ እና ትርፍ እንዲያሽቆለቁል ሲያደርግ በዚየው ልክ ሽያጭ ደግሞ እያደገ አይደለም።
የቢአይዲ የአገር ውስጥ ሽያጭ ለሰባት ተከታታይ ወራት እየቀነሰ መጥቷል፣ በተቃራኒው በአውሮፓ በዚህ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ በ156 በመቶ ጨምሯል።
ሊ እንዳሉት ውድድር የሚፈጥረው ጫና አንደናእዶች አንዲዋሃዱ አልያም እንዲከስሙ ማድረጉ የማይቀር ነው።
"ታሪክ ሁሉም አካል እንደማይዘልቅ ይጠቁማል" የሚሉት ኃላፊዋ በ90ዎቹ የጃፓን የመኪና አምራቾች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እና በቅርቡ ደግሞ የደቡብ ኮሪያ ስሪቶች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የተከሰተ መሆኑን ይጠቅሳሉ።