ቀጥታ, አሜሪካ የኢራንን የጭነት መርከብን መያዟን ተከትሎ ቴህራን በሁለተኛው ዙር ድርድር ለመሳተፍ ውሳኔ አለማሳለፏን ገለጸች

በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የዘጋችው አሜሪካ፤ በኢራን ባንዲራ የሚንቀሳቀስ የጭነት መርከብን መጥለፏን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ። ኢራን የአሜሪካ እርምጃ የተኩስ አቁም ጥሰት እንደሆነ የገለጸች ሲሆን “በትጥቅ የታገዘ የባሕር ላይ ውንብድና” ስትል ለጠራችው ለዚህ ድርጊት አጸፋውን እንደምትመልስ ዝታለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኢራኑ ፕሬዚዳንት 'ኢራን ለኃይል አትንበረከክም' አሉ

    የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን አገራቸው ከአሜሪካ ጋር በሁለተኛው ዙር ድርድር መሳተፏ ባልተረጋገጠበት ወቅት “ኢራናውያን ለኃይል አይንበረከኩም” አሉ።

    ኢራን በአሜሪካ መንግሥት ላይ "ጥልቅ ታሪካዊ አለመተማመን" እንዳላት የገለፁት ፕሬዚዳንቱ "የተገቡ ቃሎችን ማክበር"፤ “ትርጉም ላለውውይይት መሠረት መሆን አለበት” ብለዋል።

    ፔዜሽኪያን በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "ከአሜሪካ ባለሥልጣናት የሚመጡ ገንቢ ያልሆኑ እና የሚቃረኑ ምልክቶች መራራ መልእክት ያስተላልፋሉ፤ ኢራን እጇን እንድትሰጥ ይፈልጋሉ" ብለዋል።

  2. አሜሪካ በሆርሙዝ እገዳ ከጣለች ጊዜ ጀምሮ 27 መርከቦችን መከለከሏን አስታወቀች

    የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ ላይ እገዳውን ከጣለ ጊዜ ጀምሮ 27 መርከቦች ወደ ኢራን ወደብ እንዳይሄዱ ወይንም እንዲመለሱ ማድረጉን አስታወቀ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በኤክስ ገጹ ለይ ባሰፈረው ቪዲዮ ግዙፍ መርከቦች ክልከላው ወደታጠለበት የውሃ ክልል መግባታቸውን ሲነገራቸው ይደመጣል።

    በዚህ ወር መጀመርያ ላይ የአሜሪካ ባህር ኃይል ቴህራን ከነዳጅ ሽያጭ የምታገኘውን ትርፍ ለማስቆም በሚል ወደ ወደቦቿ የሚገቡም ሆነ ከወደቦቿ የሚወጡ መርከቦች ላይ እግድ እንደሚጥል አስታውቆ ነበር።

  3. የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ከእስራኤል ጋር የሚኖረው ድርድር ከአሜሪካ እና ኢራን ውይይት “የተለየ” መሆኑን ተናገሩ

    የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን ከእስራኤል ጋር የሚደረጉ ድርድሮች ከአሜሪካ እና ኢራን የሰላም ድርድር "የተለዩ” መሆናቸውን ገለጹ።

    አውን በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ሊባኖስ በቀጣይ በሚኖሩ ውይይቶች በአሜሪካ የቀድሞ የሊባኖስ አምባሳደር በነበሩት ሲሞን ካራም በሚመራ ልዑካን ቡድን እንደምትወከል ተናግረዋል።

    ከዚህ ቡድን ውጪ አገሪቱን የሚወክል ሌላ ተደራዳሪ እንደሌለ እንዲሁም በሌላ እንደማይተካ ጨምረው አብራርተዋል።

    የውይይቱ ዓላማዎች "ጥቃቶችን ማስቆም"፣ እስራኤል "በደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢዎች የምትፈጽመውን ወረራ" ማስቆም እንዲሁም የሊባኖስን ጦር "በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባለው የአገሪቱ ደቡባዊ ድንበር" ላይ ማሰማራት እንደሆነ ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሊባኖስን ጥያቄዎች "ሙሉ በሙሉ መረዳታቸውን" ገልጸዋል ያሉት አውን፣ እንዲሁም በቅርቡ የሚደረጉ ድርድሮችን በማመቻቸት ረገድ እገዛ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    በተጨማሪም “ሊባኖስን ማዳን እንደምንችል ተስፋ አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

    በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉ ቢገለጽም ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ወታደሮች ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ 10 ኪ.ሜ. ዘልቀው በመግባት እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

  4. በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉት ሁለት የተኩስ አቁሞች ምን ይመስላሉ?

    በአሁኑ ሰዓት በመካከለኛው ምሥራቅ ሁለት የተኩስ አቁሞች አሉ። አንዱ ሊባኖስ እና እስራኤል መካከል የተደረሰ ሲሆን ሌላው ደግሞ አሜሪካ ከኢራን ጋር የገባችው የተኩስ አቁም ነው።

    ኢራን እና አሜሪካ

    ለሁለት ሳምንት ያህል እንደሚቆይ የተገለጸው ይህ የተኩስ አቁም የሚያበቃው ረቡዕ ዕለት ነው።

    የዩናይትድ ስቴትስ ባህር ኃይል በኦማን ሰላጤ ላይ የኢራንን ባንዲራ በምታውለበልብ መርከብ ላይ ተኩስ ከፍቶ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ የኢራን ጦር አሜሪካን “በተኩስ አቁም ጥሰት” ወንጅሏታል።

    ዛሬ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢዝላማባድ በሁለቱ አገራት መካከል ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛ ዙር ውይይት እስካሁን ድረስ ስለመካሄዱ በእርግጠኝነት መናገር አልተቻለም።

    የአሜሪካ ልዑካን ቡድንን የሚመሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጄዲ ቫንስ ሲሆኑ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን በድርድሩ ላይ ለመሳተፍ “እቅድ የለንም” ብለዋል።

    ሊባኖስ እና እስራኤል

    በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን የጀመረው አርብ ዕለት ሲሆን ለአስር ቀን የሚቆይ ነው።

    ስምምነቱ የተደረሰው በሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን እና በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚነሲእትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መካከል ነው።

    ሁለቱ አገራት አሜሪካ ተጨማሪ የቀጥታ ድርድሮችን እንድታመቻች መጠየቃቸው ተገልጿል።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው ዝርዝር መረጃ ሊባኖስ ሄዝቦላህ እና ሌሎች ”ከመንግሥት ውጭ የሆኑ ታጣቂ ቡድኖች” በእስራኤል በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጽሙ ለማድረግ “ተጨባጭ እርምጃዎችን” መውሰድ አለባት።

    ሄዝቦላህ የተኩስ አቁሙን ለማክበር ፈቃደኛ መሆኑን የገለጸ ቢሆንም “የእስራኤል ወታደሮች እንዳይንቀሳቀሱ” የሚለው በስምምነቱ ውስጥ መካተት አለበት ሲል ጠይቋል።

  5. የኢራን ፕሬዝዳንት "ውጥረትን ለመቀነስ እያንዳንዱ የዲፕሎማሲ መንገድ ጥቅም ላይ መዋል አለበት" አሉ

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን "ጦርነት ለማንም አይጠቅምም፤ ምንም እንኳን ከሚደርሰው ማስፈራሪያ በተቃራኒ በጽናት ብንቆምም፣ እያንዳንዱ ምክንያታዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ውጥረትን ለመቀነስ ጥቅም ላይ መዋል አለበት" አሉ።

    ፔዜሽኪያን ዛሬ የአገራቸውን ፍትህ ሚኒስቴር በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢራናውያን "ስለ አገሪቱ እውነታዎች መረጃ ማግኘት አለባቸው" ያሉ ሲሆን "የተሳሳቱ መረጃዎችን ወይም ከእውነታው የራቁ ተስፋዎችን መስጠት ችግሮችን ለመፍታት እንዳንችል ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሕዝብን እምነትም ያሳጣል" ብለዋል።

    "ስኬቶቹም ሆኑ ተግዳሮቶቹ ለሕዝብ በሐቅ መነገር አለባቸው" ሲሉ ፔዜሽኪያን ተናግረዋል።

    ቀደም ሲል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቴህራን በሚቀጥለው ዙር ውይይት ላይ ለመገኘት "ምንም ዓይነት እቅድ እንደሌለ" ተናግረው ነበር።

  6. ፓኪስታን፣ ቴህራን እና ዋሺንግተን ለሚያደርጉት ቀጣይ ዙር ድርድር “የጸጥታ ሁኔታው መጠናከሩን” አስታወቀች

    የፓኪስታን የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ሞሺን ናቅቪ ከኢራን አምባሳደር ሬዛ አሚሪ ሞጋህዳም ጋር ተገናኝተው በኢዝላማባድ በሚደረገው ሁለተኛ ዙር ድርድር ዝግጅቱ ዙሪያ መወያየታቸውን እና ገለጻ እንደተደረገላቸው አስታወቁ።

    ኢራን በድርድሩ ላይ መሳተፏን ባታረጋግጥም ናቅቪ ግን ለድርድሩ ዝግጅቱ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

    ወደ ኢዝላማባድ ለሚመጣው ልዑክ “የጸጥታ ሁኔታዎች መጠናከራቸውን” እንዲሁም ለኢራን አምባሳደር ገለጻ እንደተደረገላቸው የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

    ሚኒስትሩ አክለውም በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገው ድርድር በቀጣናው ለሚኖር ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው ብለዋል።

    እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የኢራን አምባሳደር ፓኪስታን ውጥረቱን ለማርገብ እየተጫወተችው ያለውን “በጎ እና ገንቢ ሚና” አድንቀዋል።

  7. የደቡባዊ ሊባኖስ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ያገኙት ፍርስራሽ መሆኑን የተመድ ኃላፊ ተናገሩ

    ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሊባኖስ እና እስራኤል ተኩስ አቁም ለማድረግ ከተስማሙ በኋላ “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው” የደቡባዊ ሊባኖስ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው ቢመለሱም፤ መንደራቸው ሲደርሱ ያገኙት “ፍርስራሽ” መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ቶም ፍሌቸር ተናገሩ።

    ፍሌቸር ከቢቢሲ ‘ቱዴይ’ የራዲዮ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ሸቀጦችን እናጓጉዝባቸው ከነበሩ ስድስት ድልድዮች ውስጥ አምስቱ ወድመዋል፤ ስለዚህ አሁን እርዳታ ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ብቻ ሳይሆን ሲቪል ሰዎች [ወደ ቤታቸው] ለመመለስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል” ብለዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት ምግብ፣ መድኃኒት እና ብርድ ልብሶችን የጫኑ ሁለት ተሽከርካሪዎችን በሳምንቱ መጨረሻ ወደ አካባቢዎቹ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

    ተኩስ አቁም ከመደረጉ አስቀድሞ እስራኤል በሊታኒ ወንዝ ላይ የተዘረጉት እና ደቡባዊ ሊባኖስን ከቀሪው አገሪቱ ክፍል ጋር የሚያገናኙ ድልድዮች ላይ ለሳምንታት ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።

    እስራኤል ድልድዮቹን የመታችው የሄዝቦላህ ኃይሎችን እና እንቅስቃሴያቸውን ዒላማ በማድረግ መሆኑን ትናገራለች።

  8. ቻይና የኢራን መርከብ በአሜሪካ መያዙ “እንዳሳሰባት” ገለጸች

    የኢራንን ባንዲራ የሚያውለበልበው ቱስካ የጭነት መርከብ በአሜሪካ መያዙን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጥሪ አቀረቡ።

    ቃል አቀባዩ ጉኦ ጂያኩን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የአሜሪካ ኃይሎች መርከቡን “በኃይል መጥለፋቸው” ቻይናን “እንዳሳሰባት” መናገራቸውን የዜና ወኪሉ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

    ሌላኛው የዜና ወኪል አሶሺዬትድ ፕሬስ ያወጣው ዘገባ ደግሞ ቃል አቀባዩ፤ “ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች ኃላፊነት የተሞላበት አቋም እንደሚይዙ፣ በተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚያገዙ፣ ውጥረቶችን ከመጨመር ወይም ቅራኔዎችን ከማባባስ እንደሚቆጠቡ ተስፋ እናደርጋለን” ማለታቸውን ያመለክታል።

    “የሆርሙዝ ወሽመጥ ዓለም አቀፍ የውሃ መስመር ነው፤ ያለ ምንም እንቅፋት ክፍት ሆኖ መቆየቱንም ማረጋገጥ የቀጠናው አገራት እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ጥቅም ነው” ሲሉም አክለዋል።

    የቻይን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የጣለችውን እገዳ “ኃላፊነት የጎደለው እና አደገኛ” ሲል ጠርቶ ነበር።

    ከኢራን ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው የነዳጅ ምርት ውስጥ 90 በመቶ ገደማውን የምትገዛው ቻይና እንደሆነች ይገመታል። ተንታኞች፤ አሜሪካ ወደ ወደቦቹ የሚደረግ ጉዞ ላይ እገዳ የጣለችው ቻይና ኢራን ላይ ጫና እንድታሳድር ለማድረግ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት እየሰጡ ነው።

  9. “ትራምፕ ግዙፍ የጦር ወንጀል እንደሚፈጽሙ እየዛቱ ነው” - የሂውማን ራይትስ ዎች የቀድሞ ኃላፊ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቅ ሁለተኛ ዙር ድርድር ልዑካቸውን መላካቸውን በገለጹበት የትናንቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው፤ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ የኢራንን የኃይል ማመንጫዎች እና ድልድዮች እንደሚመቱ በድጋሚ ዝተዋል።

    የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች የቀድሞ ኃላፊ የሆኑት ኬኔት ሮዝ፤ ይህ የፕሬዝዳንቱ ዛቻ እንደ የጦር ወንጀል ሊቆጠር እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    “ትራምፕ ግዙፍ የጦር ወንጀል እንደሚፈጽሙ እየዛቱ ነው” ያሉት የቀድሞ ኃላፊው፤ የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈጸም በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ መሆኑን አስረድተዋል።

    ትራምፕ “ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕጎችን እንደማይከተል ሊናገር ይችላል፤ የአሜሪካ መንግሥት እና የተቀረው ዓለም ግን ይከተሉታል። የሰብአዊነት ሕግ እንደ ኃይል ማመንጫዎች እና ድልድዮች ያሉ የሲቪል ቁሶችን ዒላማ ማድረግን ይከለክላል” ብለዋል።

    እንደ ሮዝ ገለጻ ትራምፕ ድልድዮቹ እና የኃይል ማመንጫዎቹ በወታደሮችም ጥቅም ላይ ስለሚውሉ “ሁለት አይነት ጥቅም ያላቸው ቁሶች ናቸው” የሚል መከራከሪያ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ይህ ግን ክርክሩን ለመቋጨት በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

    “የሰብአዊነት ሕግ በሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳይ ተመጣጣኝ ካልሆነ ወታደራዊ ዒላማዎች ጭምር እንዳይተኮስባቸው ይጠይቃል” ሲሉ አብራርተዋል።

    በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ዋልትዝ ግን እርምጃው የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል መባሉን “ውሸት፣ ሐሰት እና ከመስመር የወጣ ሀሳብ” ሲሉ ተቃውመውታል።

    ድልድይ እና የኃይል ማመንጫዎቹ የሚንቀሳቀሱት በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በመሆኑ “ሕጋዊ ወታደራዊ ዒላማ” እንደሆኑ በመጥቀስ ተከራክረዋል።

  10. ኢራን በሁለተኛውን ዙር ድርድር ለመሳተፍ ውሳኔ አለማሳለፏን ገለጸች

    በአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የሚመራው ተደራዳሪ ቡድን ለሁለተኛ ዙር ንግግር ወደ ፓኪስታን ቢጓዝም ኢራን እስካሁን ድረስ በድርድርሩ ለመሳተፍ ውሳኔ እንዳላስተላለፈች የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናገሩ።

    ቃል አቀባዩ ኢስማኢል ባጋኢ “እስካሁን ድረስ… ለቀጣይ ዙር ድርድር ምንም እቅድ የለንም፤ ይህንን በተመለከተም የተላለፈ ውሳኔ የለም” ማለታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ያወጣው የንግግራቸው ትርጉም ያሳያል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጄዲ ቫንስ የሚመራው ተደራዳሪ ልዑክ ሰኞ ምሽት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ድርድር ወደ ፓኪስታን መጓዙን አስታውቀዋል። የትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና አማቻቸው ጃሬድ ኩሽነርም በድርድሩ ይሳተፋሉ።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ትናንት ባወጣው ዘገባ “በቀጠለው [የአሜሪካ] የባሕር ጉዞ እገዳ፣ የተኩስ አቁም ጥሰት እና በአሜሪካ ዛቻ የተሞላበት ትርክት” ምክንያት ቴህራን በንግግሩ እንደማትሳተፍ ገልጾ ነበር።

    የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ በበኩላቸው “አሜሪካ ለዲፕሎማሲ እና ለድርድር ዝግጁ ነኝ ብትልም፤ በተግባር ግን በምንም መልኩ የዲፕሎማሲ ሂደቱን የመከተል ሀሳብን በቁም ነገር መያዟን መሆኗን የሚያሳዩ ድርጊቶችን እየፈጸመች አይደለም” ብለዋል።

    የኢራንን ብሔራዊ ጥቅሞች ከማስጠበቅ ጋር በተያያዘ አገሪቱ አመራር በቀነ ገደቦች እንደማያምን መናገራቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል። ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር የኢራንን የኒውክሌር ክምችት ከአገሪቱ ማስወጣት አማራጭ ሆኖ እንደማያውቅም አስረድተዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ባደረጉት እና ያለ ውጤት በተበተነው የመጀመሪያ ዙር ንግግር ካላግባቧቸው ጉዳዮች አንዱ የቴህራን የኒውክሌር ፕሮግራም ነው።

  11. እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጻ የደቡብ ሊባኖስ ነዋሪዎችን አስጠነቀቀች

    የእስራኤል ጦር የደቡባዊ ሊባኖስ ነዋሪዎች ተለይተው ከተቀመጡ የአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል መስመሮች እንዳያልፉ እና ለሊታኒ ወንዝ አቅራቢያ ወደሆኑ ስፍራዎች እንዳይጠጉ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።

    እስራኤል እና ሊባኖስ የተስማሙበት የ10 ቀናት ተኩስ አቁም ካለፈው ሳምንት አንስቶ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። ይህ ስምምነት ቢደረግም የእስራኤል ጦር ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በሚታየው “የሄዝቦላህ ድርጅት የቀጠለ የሽብርተኞች እንቅስቃሴ“ ምክንያት አካባቢውን ለቅቆ እንደማይወጣ አስታውቋል።

    አሁን ደግሞ ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ መንደሮችን ዘርዝሮ ነዋሪዎች ወደ እነዚህ አካባቢዎች እንዳይመለሱ ወይም እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል።

    ትናንት ምሽት በደቡባዊ ሊባኖስ ክፋርኬላ የተባለ አካባቢ የሚገኝ የሄዝቦላህ ሮኬት ማስወፍጨፊያ ላይ ጥቃት መፈጸሙንም አስታውቋል።

    የእስራኤልን ነዋሪዎችን በሄዝቦላህ ከሚተኩሳቸው ሮኬቶች ለመጠበቅ ሲል ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ “የደኅንነት ዞን” ማቋቋሙንም አስታውቋል።

    ከዚህ ቀደም የእስራኤል ጦር ከተቆጣጠራቸው የሊባኖስ ስፍራዎች ለቅቆ እንደማይወጣ፣ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እንደማይፈቅድ እና መንደሮችን እንደሚያወድም ገልጾ ነበር።

    ካለፈው ሳምንት አንስቶ ተፈጻሚ በሆነው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ሊባኖስ ሄዝቦላህ እና ሌሎች “መንግሥታዊ ያልሆኑ የታጠቁ ቡድኖች” በእስራኤል ዒላማዎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጽሙ መከላከል የሚያስችል “ትርጉም ያለው እርምጃ” የመውሰድ ኃላፊነት ተጥሎባታል።

  12. ኢስላማባድ የሰላም ንግግር ለማድረግ እየተሰናዳች ነው፤ ኢራን በድርድሩ ትሳተፍ ይሆን?

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ሁለተኛ ዙር ንግግር ዛሬ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ እንደሚጀመር እየተነገረ ነው።

    ባለፈው ሚያዚያ 3/2018 ዓ.ም. የሁለቱ አገራት የሰላም ንግግር የተካሄደበት ሴርና ሆቴል እንግዶች የዛሬውን ንግግር ለማስተናገድ ሲባል ሆቴሉን ለቅቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።

    ፖሊስ የውጭ አገር ልዑኮችን ለመቀበል የኢስላማባድ ቁልፍ መንገዶችን መዝጋቱን አስታውቋል።

    ዶናልድ ትራምፕ በጄዲ ቫንስ የሚመራው እንዲሁ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነርን ጨምሮ ሌሎች “ተወካዮቻቸውን” የያዘው ልዑክ ሠኞ ምሽት ኢስላማባድ እንደሚደርስ ተናግረዋል።

    ሆኖም ግን ኢራን በንግግሩ እንደምትሳተፍ እስካሁን በይፋ አላረጋገጠችም። የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው እግድ በመቀጠሉ የቴህራን ባለሥልጣናት በንግግሩ እንደማይሰተፉ ዘግቧል።

    ለሁለት ሳምንት የተደረሰው የአሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት የፊታችን ረቡዕ ያበቃል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስምምነት የማይደረስ ከሆነ ኢራንን እንደሚያወድሙ አሁንም ዝተዋል።

  13. ኢራን በአሜሪካ መርከብ ላይ በድሮን ጥቃት መፈፀሟ ተዘገበ

    አሜሪካን የኢራንን ጭነት የሚያጓጉዝ መርከብን በቁጥጥር ስር ማዋሏን ተከትሎ፤ ቴህራን በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር መርከቦች ላይ የድሮን ጥቃቶችን መፈጸሟን ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም ዜና ወኪል ዘገበ።

    አሜሪካ ትናንት የኢራን ባንዲራን አንግቦ እየተጓዘ የነበረ የጭነት መርከብን ጠልፋ በቁጥጥር ስር ማዋሏን ካስታወቀች በኋላ ኢራን አጸፋውን እንደምትመልስ ዝታ ነበር።

    አሁን በአሜሪካ ጦር መርከብ ላይ ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት የደረሰ ጉዳት ስለመሆኑ እስካሁን መረጃ አልወጣም።

    የኢራን ጦር ኃይሎችን የሚያስተባብረው የተልዕኮ ማዘዣ ጣቢያ የሆነው ኻታም አል-አንቢያ የአሜሪካ ባሕር ኃይል በወሰደው እርምጃ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መጣሱን እና የአሜሪካ ጦር ላይ የአፀፋ እርምጃ እንደሚወስድ ገልፆ ነበር።

  14. ትራምፕ የኢራን መርከብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ካሳወቁ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ባንዲራ የሚያውለበልብ መርከብ በዋሽንግተን ቁጥጥር ስር መዋን ካሳወቁ በኋላ ሠኞ ጠዋት የዓለም ነዳጅ ገበያ ጭማሪ አሳየ።

    ይህ የሆነው ቅዳሜ ዕለት ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለንግድ መርከቦች እንደምትዘጋ በድጋሚ ካሳወቀች እና ወደ ወሽመጡ የሚጠጉ መርከቦችን ዒላማ እንደምታደርግ ካሳወቀች በኋላ ነው።

    ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በ4.74 በመቶ በመጨመር 94 ዶላር ገብቷል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በጥምረት ኢራን ላይ ጥቃት ከፈፀሙ እና ቴህራን 20 በመቶ የዓለም ነዳጅ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ መጓጓዣን በመዝጋቷ ምክንያት የኃይል ገበያው ከፍተኛ ውጣ ውረዶችን አይቷል።

  15. አሜሪካ የኢራንን የጭነት መርከብን መያዟን አስታወቀች፤ ኢራን አጸፋውን እንደምትመልስ ዝታለች

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የዘጋችው አሜሪካ፤ በኢራን ባንዲራ የሚንቀሳቀስ የጭነት መርከብን መጥለፏን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ በሶሻል ትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው እንዳስታወቁት ‘ቱስካ’ የተሰኘው መርከብ የተያዘው ጉዞውን እንዲያቆም በአሜሪካ ባሕር ኃይል የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ባለማክበሩ ነው።

    ኢራን የአሜሪካ እርምጃ የተኩስ አቁም ጥሰት እንደሆነ የገለጸች ሲሆን “በትጥቅ የታገዘ የባሕር ላይ ውንብድና” ስትል ለጠራችው ለዚህ ድርጊት አጸፋውን እንደምትመልስ ዝታለች።

    እርምጃው እንደተወሰደ የተገለጸው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከኢራን ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለመቋጨት ፓኪስታን ውስጥ በሚካሄደው ሁለተኛ ዙር ድርድር ላይ የአሜሪካን ልዑክ እንደሚመሩ ዋይት ሀውስ ካረጋገጠ በኋላ ነው።

    እስካሁን ኢራን በድርድሩ የመሳተፏን ነገር አላረጋገጠችም። የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት የአገሪቱ ባለሥልጣናት የአሜሪካ እገዳ በተጣለበት ሁኔታ ድርድር ውስጥ አንሳተፍም የሚል አቋም ይዘዋል።

    ትራምፕ መርከቡ መጠለፉን ባስታወቁበት ልጥፋቸው፤ “ዛሬ የኢራንን ባንዲራ ያነገበ፣ 900 ጫማ የሚጠጋ ቁመት ያለው እና ክብደቱ ከአውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ጋር የሚቀራረብ ቱስካ ተሰኘ መርከብ የጣልነውን የባሕር እግድ ለማለፍ ሞክሯል፤ ጥሩ አልሄደላቸውም” ሲሉ ጽፈዋል።

    አሜሪካ መርከቡ እንዲቆም ማስጠንቀቂያ ብትሰጥም እንዳልተቀበለው ገልጸዋል። “ስለዚህ ባሕር ኃይላችን ኢንጅን የሚገኝበት ክፍል ላይ በመምታት አቁሟቸዋል” ሲሉ የተወሰደውን እርምጃ ተናግረዋል።

    “ቱስካ ከዚህ ቀደም በነበረው የሕገ ወጥ ተግባር እንቅስቃሴ ምክንያት በአሜሪካ ግምጃ ቤት ማዕቀብ ተጥሎበታል። መርከቡ ላይ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር አለን፤ የተጫነውንም ነገር እያየን ነው” ብለዋል።

    የኢራን ጦር ዋና መስሪያ ቤት ኻታም አል አንቢያ ቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ አሜሪካ “ከኢራን የንግድ መርከቦች አንዱ በኦማን ባሕር ላይ እያለ ተኩስ በመክፈት፣ የጉዞ ስርዓቱን በማጥፋት እና መርከቡ ላይ በመውጣት የተኩስ አቁም ጥሰት ፈጽማለች” ብለዋል።

    ይህንን ያደረገችው ወታደሮቿን በማሰማራት እንደሆነ ጠቅሷል። “ኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጦር ኃይሎች በቅርቡ ምላሽ ይሰጣሉ፤ ለዚህ በአሜሪካ ባሕር ኃይል ተፈጸመ በትጥቅ የታገዘ የባሕር ላይ ውንብድና ድርጊት አጸፋውን ይመልሳሉ” ሲሉም ዝተዋል።