ትዳርን ሽሽት ወደ አውስትራሊያ ያመራችው ሳዑዲ አረቢያዊት ደብዛዋ መጥፋቱ ተነገረ

ሎሊታ

የፎቶው ባለመብት, Supplied

የምስሉ መግለጫ, ሎሊታ

ሎሊታ እአአ በ2022 ወደ አውስትራሊያ ለመሸሽ ተገደደችው ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ገና በለጋ ዕድሜዋ በብዙ ዓመታት ለሚበልጣት ትልቅ ሰው በመዳሯ ነበር።

የደረሰባት ተደጋጋሚ አካላዊ እና ፆታዊ ጥቃት ለሆስፒታል ዳርጓት እንደነበር ተናግራለች።

አውስትራሊያ ደረሳ አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላት አሁንም ጠፍታለች። አንድ ጓደኛዋ የሳዑዲ ሰዎች በጥቁር መኪና ከመኖሪያ ቤቷ ሲወስዷት ለመጨረሻ ጊዜ አይቻለሁ ብሎ ነበር።

በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ሎሊታ በግንቦት ወር 2023 ከሜልበርን ወደ ኳላ ላምፑር መብረሯን መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚያ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተወስዳ እንደታሰረች ጠበቃዋ ያምናል።

የሎሊታ ያለችበት ትክክለኛ ቦታ እና ደኅንነቷን ጨምሮ በሕይወት ስለመኖሯ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።

ሳዑዲ አረቢያ ጥላ የተሰደደች ሴት ርዕሰ ዜና ስትሆን ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

“ይህን ጉዳይ በተለየ ሁኔታ አሳማኝ የሚያደርገው ከጠፉ አንዳንድ የሳዑዲ ሴቶች ወይም ሞተው ከተገኙ ጋር ሲነጻጸር እኛ ምስክር አለን” ብለዋል ጠበቃዋ አሊሰን ባትሰን።

በካንቤራ የሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

የአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ በበኩሉ በሰኔ ወር ስለተከሰሰው አፈና “እንዳወቀ” እና በአገር ውስጥ እና በውጭ “አፋጣኝ ምርመራ ማድረግ መጀመሩን” ለቢቢሲ በሰጠው መግለጫ ተናግሯል።

የሎሊታ ጉዳይ በአውስትራሊያ ውስጥ እያደገ ያለው እና የሌሎች አገራት የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ዜጎቻቸውን የሚከታተሉበት፣ የሚያንገላቱበት ወይም የሚያጠቁበት አዝማሚያን የሚያሳይ ነው ይላሉ ተሟጋቾች።

መንግሥት የውጭ ጣልቃገብነት የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት መሆኑን በማወጅ እርምጃ እንደሚወስድም ቃል ገብቷል።

ባትሰን እና ሌሎች የመብት ተሟጋቾች ግን እንዴት ከጥቃት እንደምትሸሽ የተናገረች ሴት በጠራራ ፀሐይ ከቤቷ ልትወሰድ ትችላለች ሲሉ እየጠየቁ ነው።

እልም ብሎ መጥፋት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሎሊታ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜልበርን ያቀናችው በግንቦት ወር 2022 እንደነበር የበረራ መረጃዋ ያሳያል።

አብዛኛውን ጊዜ ራሷን ብትጠብቅም ብዙም ሳይቆይ በሳዑዲ አረቢያ ይኖር ከነበረ ሱዳናዊ ስደተኛ ጋር ጓደኝነት ፈጠረች።

አሊም [ትክክለኛ ስሙ አይደለም] እሱን በጥገኝነት ጉዳዩ ከረዳችው ባትሰን ጋር አስተዋወቃት።

የሰብዓዊ መብት ጠበቃው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሎሊታ ጋር በተደጋጋሚ ትነጋገር የነበረ ሲሆን “ይህ ጊዜዋ እንደሆነ” በመወሰን ሕይወቷን ለማስተካከል ግልጽ የሆነ ውሳኔ ነበራት በማለት ገልጸዋታል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ባትሰን ከሎሊታ “እንግዳ” የጽሑፍ መልዕክት ከደረሳት በኋላ ግንኙነታቸው በድንገት ተቋረጠ።

“ከሌላ ጊዜ በተለየ ሁኔታ መደበኛ ቋንቋ ተጠቅማ ነበር 'የቪዛዬ ነገር ከምን ደረሰ?’ ያለችው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

የሎሊታ የደኅንነት ቪዛ ጥያቄ አቅርባ ነበር። ይህ ቪዛ በአገራቸው የአደጋ ስጋት ላለባቸው የሚሰጥ ሲሆን፣ ጥያቄዋ ከዚህ ቀደም ውድቅ ተደርጎ ነበር። ባትሰን ውሳኔውን በመቃወም በይግባኝዋን እየረዳችት ነበር። ሁለቱ ደጋግመው ስለሚነጋገሩ ሎሊታ ደረሰበትን ደረጃ ታውቃለች ትላለች።

“ሎሊታን ከወሰዱት ሰዎች የመጣ መልዕክት ነው ብዬ አምናለሁ” ብላለች ባትሰን። ሎሊታ ቋሚ ቪዛ እንዳላት ለማወቅ እየሞከሩ እንደሆነ ታስባለች። ይህን ያደረጉትም በሳዑዲ አረቢያ ያለው የአውስትራሊያ ቆንስላ እርዳታ የማግኘት መብት ይሰጣት እንደሆነ ለማወቅ ነው።

ከዚያም ምንም ነገር ሳይፈጠር ዝምታ ሆነ። ሳምንታት ወራትን ሲተኩ ባትሰን "አንድ ነገር እንደተፈጠረ" ተሰምቷታል።

አሊንም ማግኘት አልቻለችም። ሁለቱ መደበኛ ግንኙነት ስለነበራቸው ይህም ያልተለመደ ነበር።

መጨረሻ ላይ ስልኩን አንስቶ የፈራችውን ነገር ነገራት።

ሎሊታ ስትወሰድ እንዳየ ተናግሮ፤ ክስተቱ ለቤተሰቡ እንዳይተርፍ በመፍራት በዝምታ መደበቁን ነገራት።

ከሎሊታ ጋር ያደረገውን የመጨረሻ ንግግር ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሊወስዷት ካቀዱ ወንዶች ጥበቃ እንዲደረግላት የሚመለከት እንደነበርም ገልጿል።

አስገድደው ልብሶቿን እንድትሸክፍባቸው ያደረጉባቸውን ቦርሳዎች ፎቶም ልካለታለች።

የሎሊታ ሻንጣዎች

የፎቶው ባለመብት, Supplied

የምስሉ መግለጫ, የሎሊታ ሻንጣዎች

አሊ በፍጥነት ወደ አፓርታማዋ ቢያመራም ግን አንድ አረብኛ ተናጋሪ ሰው እንዳስፈራራው ለባትሰን ነገራት። ሰውየው ካንቤራ ከሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ ብሎ ያምናል።

ዘዴውን በመቀየር ጓደኛውን አነጋግሮ ወደ አየር ማረፊያ በመሄድ ሁለቱም “ውዝግብ እንዲፈጥሩ” በማድረግ የደኅንነት ሠራተኞችን ትኩረት ለመሳብ አሰበ።

ሎሊታን ግን በአየር ማረፊያው አላይዋትም።

“መወሰዷን ለማረጋገጥ አንድ ዓመት ፈጅቶብኛል” ስትል ባትሰን ተናግራለች።

ጠበቃዋ የተከሰተውን ነገር ለማወቅ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁኔታውን እየተከታተለች ነው።

“እሷ ስለመፍራቷ የምትናገርበት የስልክ ልውውጦች እና መልዕክቶች አሉን። በዚህ ፍራቻ የተነሳ ቤት በተደጋጋሚ እንደምትቀይርም መረጃ አለን” ትላለች።

በቅርቡም አንድ ቤተ ዘመድ ምስክርነት ሰጥቷል። “እስከሚያውቁት ድረስ ሎሊታ በሳዑዲ እስር ቤት ወይም ማቆያ ውስጥ ትገኛለች” ብላለች ባትሰን።

ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን

በታሪኩ ውስጥ ግልጽ የሆኑ ክፍተቶች አሉ። እንደባትሰን ከሆነ በማያሻማ መልኩ የሚታወቀው ግን ሎሊታ በትውልድ አገሯ ውስጥ “ምንም አስተማማኝ አማራጮች የላትም” የሚለው ነው።

ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን እአአ በ2017 የሳዑዲ አረቢያ ገዥ ከሆኑ በኋላ አንዳንድ በሴቶች ላይ የተጣሉ እገዳዎችን በማላላት ግዛቱን ለማዘመን ጥረት አድርገዋል።

በሳዑዲ ሁሉም ሴቶች ከእስር ቤት ለመውጣት ወንዶችን ፊርማ ይፈልጋሉ። በዚህ ሕግ መሠረት የሎሊታ ጉዳይ የሚወሰነው በሸሸችው ባለቤቷ ላይ ነው።

ባትሰን እንደምትለው ይህ ብቻ የአውስትራሊያ ባለሥልጣናት “በፍቃደኝነት ወደ ሳዑዲ አረቢያ የምትመለስበት ምንም መንገድ የለም” በማለት ለማመን በቂያቸው ሊሆን ይገባ ነበር።

“ስጋቱ እውነታነት አለው”

ሎሊታ አውስትራሊያ በደረሰችበት ወቅት አገሪቱ ውስጥ ሌሎች ሁለት የሳዑዲ ሴቶች ምሥጢራዊ በሆነ መልኩ ሞተው ተገኝተዋል።

የእህትማማቾቹ የአስራ እና የአማል አልሴህሊ አስከሬን በ2022 በምዕራብ ሲድኒ ቤታቸው ውስጥ ተገኝቷል።

እህትማማቾቹ እንዴት እንደሞቱ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም። ፖሊስ ግን ጉዳዩን “አጠራጣሪ” እና “ያልተለመደ” ሲል ገልጾታል።

በ2017 ጥገኝነት ለመጠየቅ ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አውስትራሊያ የተጓዙት አስራ እና አማል በፍርሃት ይኖሩ ነበር ሲሉ ምስክሮች ከሚያሳዩት ባህሪ ተነስተው ተናግረዋል።

የሳዑዲ ሴቶች ጥገኝነት ለመጠየቅ ወደ ተለያዩ አገራት ማቅናታቸው ወይም በግዳጅ ስለመወሰዳቸው የሚወጡ ዘገባዎች አዲስ አይደሉም።

በ 2018 በአሜሪካ ጥገኝነት ከጠየቁ በኋላ በሃድሰን ታስረው የተገኙት የታላ ፋሬ እና የሮታና ፋሬ ጉዳይ ትልቁ ማሳያ ነው። በ2017 ደግሞ ወደ አውስትራሊያ ለመሸሽ ስትሞክር በማኒላ አየር ማረፊያ በአጎቶቿ እንደተጠለፈች የምትናገረው ዲና አሊ ላስሎምም ሌላኛዋ ናት።

የአውስትራሊያ የስለላ ሃላፊ ማይክ በርገስ

የፎቶው ባለመብት, ASIO

የምስሉ መግለጫ, የአውስትራሊያ የስለላ ሃላፊ ማይክ በርገስ

ባለፉት ዓመታት ከቻይና፣ ከኢራን፣ ከሕንድ፣ ከካምቦዲያ እና ከሩዋንዳ ጋር ትስስር ያላቸው በርካታ አውስትራሊያውያን በየመንግሥታቸው ወኪሎች ክትትል፣ ትንኮሳ ወይም ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርት አድርገዋል።

የአውስትራሊያ የስለላ ኃላፊ በበኩላቸው “ከመቼውም ጊዜ በላይ” ብዙ ሰዎች በአገሪቱ ውስጥ “በስለላ እና በውጭ ጣልቃገብነት ምክንያት ዒላማ” እየተደረጉ ነው።

“አውስትራሊያውያን ያለው ሥጋት እውነት መሆኑን ማወቅ አለባቸው። ሥጋቱ አሁን ነው። ስጋቱ ከሚገመተው በላይ ጥልቅ እና ሰፊ ነው” ሲሉ ማይክ በርገስ በየካቲት ወር ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የአገሪቱ ፓርላማ የብሔራዊ የውጭ ጣልቃ ገብነት ሕግ ግምገማ “በአተገባበሩ ላይ ጉልህ ጉድለቶች” ያሉት እና “የታሰበውን አላማ ማሳካት አልቻለም” ብሏል።

በምላሹም መንግሥት የዲያስፖራ ማኅበረሰቦች አጠራጣሪ ባህሪያትን ለመለየት እና ሪፖርት ለማድረግ የሚረዳ የድጋፍ አሠራር መዘርጋትን እና ቋሚ የውጭ ጣልቃ ገብነት ግብረ ኃይልን ጨምሮ ማሻሻያዎችን አስተዋውቋል።

“እነዚህ ውስብስብ ችግሮች ናቸው። ከኤጀንሲዎቻችን ጋር ያለማቋረጥ… ተጋላጭ ሰዎችን ለመጠበቅ እየሠራን ነው” ሲሉ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ክሌር ኦኔይል መግለጫ ሰጥተዋል።

ለውጦቹ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ ለመገምገም ግን በጣም ገና ነው።