ለበርካቶች የሙዚቃ ጉዞ መነሻ የሆነችው ዊትኒ ሂዩስተን እና ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ሥራዋ

ዊትኒ ሂዩስተን

ከ12 ዓመታት በፊት በየካቲት 2012 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ያረፈችው ዊትኒ ሂዩስተን፣ የበርካታ ትውልዶችን ሕይወት በሙዚቃ ሥራዎቿ ነክታለች።

ሥራዎቿ አሁንም በመላው ዓለም በሚገኙ ሚሊዮኖች እየተደመጡ ይደነቃሉ፤ በርካቶች ደግሞ ከሙዚቃ ብቃቷን ለመማር ድምጻቸውን በእርሷ ሥራዎች ይሞርዳሉ።

ዊትኒ ብቃቷን ለዓለም ያሳየችው በሙዚቃ ሥራዎቿ ብቻ ሳይሆን በፊልሙም በኩል የተዋጣላት ተዋናይት እንደሆነች አስመስክራለች።

በተለይ ብዙዎች የ90ዎቹ ትውልድ አባላት የማይዘነጉት ሥራ አላት። እንደ ቪሲዲ፣ ዲቪዲ፣ ኔትፍሊክስ ባልተወለዱበት ዘመን በዴክ- ቪኤችኤስ ካሴት ከሚታዩ ዝነኛ ፊልሞች አንዱ ነበር፤ ዘ ቦዲ ጋርድ።

በዚህ ፊልም ኬቨን ኮስትነር እና ዊትኒ ሂዩስተን ይተውኑበታል።

ዊትኒ በፊልሙ ላይ ሙዚቀኛ ሆና፣ ኬቨን ደግሞ የእርሷ የግል ጠባቂ ሆኖ የሚተረክ የፍቅር ታሪክ ነው።

ለዚህ ፊልም ማጀቢያ የተሠራው የዊትኒ ሂዩስተን “አይ ዊል ኦልዎይስ ላቭ ዩ” (I will Always Love you) የተሰኘው ሥራ ላለፉት 30 ዓመታት እንዳማረበት፣ እንደተወደደ አለ።

ባደረ ቁጥር እንደ ወይን ሲጣፍጥ ኖሯል።

ይህ ሙዚቃ የተጻፈው እና የተቀረጸው እንደፈረንጆቹ በ1973 ነበር።

ታዲያ ያኔ ለዊትኒ አልነበረም የተጻፈው።

ፀሐፊዋም ዊትኒ አልነበረችም።

ዶሊ ፓርተን ነበረች የጻፈችው።

ስትጽፈው ደግሞ ለዚህ ታላቅ ደረጃ ላበቃት የቅርብ ወዳጇ ፖርተር ዋግነር መታሰቢያ እንዲሆንላት ነበር።

ዊትኒ በድጋሚ ዘፍናው ዓለምን ካነቃነቀ በኋላ ዶሊ በሁለት ዓመት በፊት ስትናገር “እኔ ያን ጊዜ እንዲህ ተአምር የሆነ ሙዚቃ እንደጻፍኩ መቼ አውቄ፤ ዊትኒን በሰማሁ ቁጥር የስሜት ህዋሳቶቼ ይንቀለቀላሉ” ብላ ነበር።

ዳሚ ኢም የሙዚቃ አዋቂ ነው። ለቢቢሲ ሲናገር፣ “ዊትኒ ይህን ሙዚቃ በጥልቅ ስሜት ስለምትዘፍነው ዜማው አብሯት ከነፍሷ ጋር የተሰፋ ያህል ነው” ሲል አስተያየት ሰጥቷል።

ሌላው ለሙዚቃው መወደድ አንድ ምክንያት ተደርጎ የሚታሰበው የዊትኒ የድምጽ ቅላጼ እና እርግብግቢት ከፕሮዳክሽኑ ጋር መዋሃዱ ነው። ፕሮዳክሽኑ የዳቬድ ፎስተር ሲሆን፣ ዴቪድ ከሴሌንዲዮን እና አሪታ ፍራንከሊን ጋር ተመሳሳይ ስኬታማ ሥራን የሠራ ሰው መሆኑ ይታወሳል።

ዊትኒ ሂዩስተን
የምስሉ መግለጫ, ዊትኒ ሂዩስተን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዊትኒ ስቱዲዮ ገብታ ሙዚቃውን ስትሠራ ብዙውን ጊዜ ራሷን እስከመሳት ድረስ ሊያደርስ የሚችል የስሜት ከፍታ ውስጥ ትዘልቃለች ይላሉ አብረዋት የሠሩ ሙያተኞች።

“ወይም ዕጹብ ድንቅ ተዋናይት ናት፤ አልያም ደግሞ ስሜቷ የትወና አይደለም፤ የተፈጥሮ እንጂ” ይላል ይህ የሙዚቃ ሊቅ ለቢቢሲ።

በርኔት ይህን የዊትኒን ሙዚቃ፣ “በእኛ ትውልድ ውስጥ የማይደገም ታላቁ የድምጽ ደረጃ” ሲል ያወድሰዋል።

ትንሽ ወደ እርሷ ሙዚቃ የሚጠጉት የማሪያ ኬሪ “ሂሮ” እና የሴሌንዲዮን “ማይ ሃርት ዊል ጎ ኦን” ናቸው ብሎ ያምናል። 

ዊትኒ በዚህ ብቸኛ ሙዚቃዋ ሺህ ሙዚቀኞችን አፍርታለች። በአሜሪካ እና በእንግሊዝ እንዲሁም በተቀረው ዓለም የሚገኙ ወጣቶች ለውድድር የእርሷን ሙዚቃ ይዘው ይቀርቡ ነበር። ይህም በስሜት ስለሚዋጡ ነው።

ብዙዎቹ ሙዚቃን እንዲወዱ ያደረጋቸውም ይኸው የዊትኒ ዘመን አይሽሬ ሥራ ነው።

ችግሩ ታዲያ ወጣቶች በውድድር ወቅት ዊትኒን ለመሆን ሲሞክሩ በአጭሩ ተሰብረው ይቀራሉ። ይህ የሚሆነው ትላለች የቢቢሲ የባህል ጉዳዮች ዘጋቢ ካሪ ግራንት፣ “ይህ የሚሆነው ዊትኒን ማስመሰል በአእምሮ ቀላል ቢሆነም በድምጽ ግን ከባድ ስለሆነ ነው።”

ዴቪድ ግራንት ሌላው የሙዚቃ ባለሙያ ነው። የዊትኒ በዓለም ሙዚቃ ላይ ያኖረችው ተጽእኖ የማይስተባበል ነው ይላል።

“ምክንያቱም ደግሞ ኋላ ላይ ለብዙ ሴት ዘፋኞች አርአያ ሆናለች። እሷን አይተው ነው ብዙ ሴቶች ሙዚቃን የጀመሩት።”

ዊትኒ የፖፕ፣ የሶል እና የአር ኤንድ ቢ ሙዚቃን አሳምራ ተጫውታለች። ምናልባት በብዙ የሙዚቃ ረድፎች መንገጫገጭ የማታሳየው ሙዚቃን ከቤተክርስቲያን ዝማሬ ስለጀመረች እና በልጅነቷ በቂ መሠረት ይዛ ስለተነሳች ይሆናል ይላሉ ተንታኞች።

የዊትኒ “አይ ዊል ኦልዌይስ ላቭ ዩ’ በታሪክ ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበ ሙዚቃ ነው። ነገር ግን ይህን ሙዚቃ ከመልቀቋ ቀደም ብሎም ዊትኒ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ተጎናጽፋ ነበር።

ከ1985 እስከ 1987 ብቻ ሌሎች ሰባት ሙዚቃዎቿ በቢልቦርድ ሰንጠረዥ አንደኛ የሆኑላት ነበሩ። ከእነዚህም መካከል “አይ ዋና ዳንስ ዊዝ ሰምባዲ” (I Wanna Dance with Somebody) እና “ኦል ማይ ላቭ ፎር ዩ” (All My Love for You) ይጠቀሳሉ።

የሙዚቃ ተንታኞች እንደሚሉት በአር ኤንድ ቢ ዘርፍ ዊትኒ በቀደደችው ፈር እነ ማሪያ ኬሪ፣ ክሪስቲና አጉሊየራ፣ ቢዮንሴ እና ጄኔፈር ሐድሰን ገብተዋል። ገበያውን የከፈተችላቸው ዊትኒ ናት ይላሉ።

ሌላው የዊትኒ አስደናቂ ስኬት በአንድ የሙዚቃ ስልት ብቻ አለመወሰኗ ነው። ፖፕ፣ ሶል፣ ሮክ እና አር ኤንድ ቢ ላይ ተሳክቶላታል።

ዊትኒ ሂዩስተን
የምስሉ መግለጫ, ዊትኒ ሂዩስተን

ዊትኒ በአሳዛኝ ሁኔታ ከዛሬ 12 ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ የካቲት 2012 ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ ቢዮንሴ እንዲህ ብላ ነበር።

“እኔ ሁልጊዜም ምኞቴ ዊትኒን መሆን ነበር። የእርሷን ድምጽ የመሰለ ከወዴት ይገኛል? እንከን የማይወጣለት ቅላጼ፤ የሚሻክር ግን ደግሞ ለስላሳ ድምጽ።”

ብዙ ሴት ዝነኛ ዘፋኞች የዊትኒን ሞት ተከትሎ “እሷን በማየት ነው ለዚህ የበቃነው፤ ንግሥታችን ነበረች” ሲሉ ጽፈዋል።

ሌዲ ጋጋ ግራሚ ሽልማንት ስትቀበል በቅድሚያ ያመሰገነችው ዊትኒን ነበር። “እሷን ቀድሜ የማመሰግነው “ቦርን ዚስ ዌይ” (Born This Way) የሚለውን ሙዚቃ ስጽፈው ዊትኒ ስትዘፍነው በማሰብ ነበር የተሳካልኝ፤ እኔ እዘፍነዋለሁ ብዬ ባስብ እንደዚያ አልጽፈውም ነበር፤ ያ ዓይነት መተማመን በራሴ ላይ አልነበረም” ብላለች።

ዊትኒ ከሞተች 12 ዓመት ሆናት። ይህ ጥዑም ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዋ ደግሞ 30 ዓመት አለፈው። ይሁንና አሁንም ይህ ተዓምረኛ ሙዚቃዋ እንደ ኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ዝንተ ዓለም ይታወሳል።