የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አውሮፕላን ወደ ሚያርፍበት የአየር ኃይል ሰፈር በተላከ ጥቅል በርካቶች ታመሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አውሮፕላን ኤርፎርስ ዋን ወደ ሚቆምበት የአየር ኃይል ጦር ሠፈር የተላከ "አጠራጣሪ ጥቅል" ከተከፈተ በኋላ በርካታ ሰዎች መታመማቸው ተገለፀ።
በዋሺንግተን ዲሲ አቅራቢያ በሜሪላንድ የሚገኘው የጥምር ኃይሉ አንድሩ ጦር ሠፈር (ጄቢኤ) ቃል አቀባይ ጥቅሉ የተከፈተበትን ሕንጻ ሠራተኞች ለቅቀው እንዲወጡ መደረጉን እና የታመሙት የሕክምና ክትትል ከተደረገላቸው በኋላ እንደተሻላቸው ተናግረዋል።
ሲኤንኤን ወደ ጦር ሠፈሩ የተላከው ጥቅል ምንነቱ ያልታወቀ ነጭ ዱቄት የያዘ እንደነበር ስማቸውን ያልተገለጸ እና በጉዳዩ ላይ የሚደረገውን ምርመራ በቅርበት የሚከታተሉ ያላቸውን ግለሰብ ጠቅሶ ዘግቧል።
የአየር ኃይል ጦር ሠፈሩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አውሮፕላን እና ሠራተኞቹ የሚቀመጡበት ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ ፕሬዝዳንቱ ወደ ተለያዩ አገራት ጉዞ ሲያደርጉ የሚነሱት ከዚህ የአየር ኃይል የጦር ሠፈር ነው።
የጄቢኤ ቃል አቀባይ ምንነቱ ያልታወቀው ጥቅል የተከፈተበት እና ከእርሱ ጋር የተገናኘ ሌላ ሕንጻ "ለጥንቃቄ" በሚል ሠራተኞች ለቅቀው እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል።
አክለውም "ወደ አካባቢው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የተሰማሩ ሲሆን፣ ስጋት የሚሆን ምንም ነገር እንደሌለ በማሳወቃቸው መደበኛ ሥራ ተጀመሯል። ምርመራም እየተካሄደ ነው" ብለዋል።
ሲኤንኤን እስካሁን ድረስ በተደረጉ ምርመራዎች ምን ዓይነት አደጋ የሚያስከትል ነገር አልተገኘም ብሏል።
በጥቅሉ ውስጥ የነበረውን ዱቄት ምንነት ለማወቅ በአደገኛ ንጥረነገሮች ዙሪያ የሚሠራ ቡድን የመጀመሪያ ምርመራ ማድረጉን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ነገር ግን በቡድኑ የተደረገው የምርመራ ውጤት በጥቅሉ ውስጥ ያለው ይዘት በሰው ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነገር እንዳልሆነ አመልክቷል። የሚደረጉ ተጨማሪ ምርመራዎች ግን አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው።
መርማሪዎች ከጥቅሉ ጋር አብሮ የመጣ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ጽሑፍን እየፈተሹ መሆኑ ተገልጿል።
የታሸገውን ጥቅል የከፈቱ ሰዎች ያጋጠማቸው ሕመም ምንነት እና ምን ያህል ጉዳት እንዳጋጠማቸው እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ወታደራዊው አየር ማረፊያ የሚገኘው ከዋሽንግተን አቅራቢያ በመሆኑ የተነሳ የአገሪቱ ፕሬዝዳንቶች አውሮፕላን የሆነው ኤር ፎርስ ዋን የሚነሳው እና የሚያርፈው ከዚያ ነው።
ይህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ግዙፍ አውሮፕላን የመነሻ ማዕከል የሆነው የአየር ማረፊያ የአንድሩ አየር ኃይል ሠፈርን እና የባሕር ኃይል የአየር ምድብን በማዋሃድ በአውሮፓውያኑ 2009 ነበር አንድሩ የአየር ኃይል ሰፈር በሚል የተዋቀረው።
ይህ የአሜሪካ አየር ኃይል እና ባሕር ኃይል የጥምር ማዕከል የሆነው አንድሩ ጦር ሰፈር ስያሜውን ያገኘው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አውሮፓው ውስጥ የአሜሪካን ጦር ኃይሎች አዛዥ ከነበሩት ከሌተናንት ጄነራል ፍራንክ ማክስዌል አንድሩ ነው።















