በሚቺጋን በሚገኝ ቤተክርስትያን ላይ በተፈፀመ ጥቃት አራት ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty
በአሜሪካ ሚቺጋን ግዛት በምትገኝ ቤተክርስትያን አንድ ታጣቂ ተኩስ በመክፈት እና በሕንጻው ላይ እሳት በመለኮስ በፈፀመው ጥቃት ቢያንስ አራት ሰዎች ሲገደሉ ስምንት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ ገለጸ።
ባለሥልጣናት እንዳሉት በዲትሪዮት ከተማ ሰሜን ምዕራብ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ግራንድ ብላንክ ከተማ በምትገኝ ሞርሞን ቤተክርስትያን ላይ ጥቃቱ የተፈፀመው በመቶዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን የእሁድ የአምልኮ ሥነ ሥርዓትን እየታደሙ በነበረበት ወቅት ነው።
ተጠርጣሪው በሚቺጋን በርተን ነዋሪ የሆነው የ40 ዓመቱ ቶማስ ጃኮብ ሳንፎርድ እንደሆነ የተለየ ሲሆን፣ ጥቃቱን ከፈፀመ በኋላ በቤተክርስትያኗ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ በፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ አልፏል።
ባለሥልጣናት "የታሰበበት የጥቃት ድርጊት" ያሉት ክስተት ላይ ምርመራ እያደረጉ ሲሆን የጥቃቱ ዓላማ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
የግራንድ ብላንክ ታውንሽፕ ፖሊስ አዛዥ ዊሊያን ሪንይ እሁድ እለት በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ሁለት ግለሰቦች የተተኮሰባቸው ጥይት ባደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።
በኋላ ላይም ሁለት ሰዎች ሞተው መገኘታቸውን እና ሌሎች ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው አዛዡ ገልጸዋል።
ሪንይ እንዳሉት እሁድ እለት ከሰዓት 9፡25 ላይ ታጣቂው በተሽከርካሪ ላይ ሆኖ ወደ ሕንፃው ሲገባ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቤተክርስትያኗ ውስጥ በአምልኮ ሥነ ሥርዓት ላይ ነበሩ።
ከዚያም ጥቃት አድራሹ ተኩስ በመክፈት በቤተክርስትያኗ ውስጥ በነበሩት ግለሰቦች ላይ የተኩስ ሩምታ መክፈቱን አዛዡ ተናግረዋል።
ፖሊስ ወዲያውኑ ምላሽ ሰጥቷል ያሉት አዛዡ፣ ፖሊሶች ከግለሰቡ ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን እና በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ግለሰቡ መገደሉን ገልጸዋል።ሳንፎርድ የተገደለው ተኩስ በከፈተ በስምንት ደቂቃዎች ውስጥ ነው።
" እሳቱ መቼ፣ የት እና እንዴት እንደተጀመረ ለመለየት እየሞከርን ነው" ብለዋል አዛዡ።
ሆኖም ተጠርጣሪው እሳቱን ለማስነሳት ተቀጣጣይ ፈሳሽ ምን አልባትም ጋዛ ሳይጠቀም እንዳልቀረ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
የፖሊስ አዛዡ ሪይን ጥቃቱ በሚፈፀምበት ወቅት ሕጻናትን በመደበቅ ምዕመናኑ የፈፀሙትን ጀግነነትን አድንቀዋል።
መርማሪዎች የተጠርጣሪውን የግል ንብረቶች እየፈለጉ ሲሆን የጥቃቱ አላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ የእጅ ስልኩ ላይ ያሉ መረጃዎችን እየመረመሩ ነው።
ሳንፎርድ የቀድሞ የባሕር ኃይል አባል እንደሆነ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በዲትሮይት በሚገኘው ቢሮ የኤፍቢአይ ልዩ ወኪል ተወካይ ሩበን ኮልማን እንዳሉት ከሆነ ምርመራውን የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ ኤፍቢአይ እየመራው ሲሆን የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጭ ቡድን፣ የቦምብ ቴክኒሽያን እና ሌሎች በሥፍራው ተሰማርተዋል።
የሚቺጋን ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ ኪም ቪትርም የፖሊስ መኮንኖች በሌሎች በርካታ ቦታዎች ያሉ የቦምብ ፍንዳታዎች ስጋት ምላሽ እየሰጡ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
" ምላሽ ሰጥተናል። ሥፍራዎቹንም አጽድተናል" ብለዋል ቃል አቀባይዋ።
የሞርሞን ቤተክርስትያን በሰጠችው መግለጫም አንድ የታጠቀ ግለሰብ በአምልኮ ሥነ ሥርዓት ላይ ተኩስ መክፈቱን እና በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጣለች።
" ለሰላም እና በዚህ ሁሉ ውስጥ ላለፉትም ሁሉ ምህረት እንዲልክላቸው እንጸልያለን" ብላለች ቤተክርስትያኗ በመግለጫዋ።
የግራንድ ብላንክ ታውንሽፕ ፖሊስ በምርመራው ላይ ድጋፍ ለመስጠት 100 የኤፍቢአይ ወኪሎች ተሰማርተዋል ብሏል።
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕም የተፈፀመውን ጥቃት በተመለከተ ገለጻ እንደተደረገላቸው ገልጸው፣ የፌደራል ምርመራውን ኤፍቢአይ እንደሚመራው አረጋግጠዋል።
ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ክስተቱን " በአሜሪካ በክርስትያኖች ላይ ኢላማ ተደርጎ የተፈፀመ ሌላ ጥቃት" ብላውታል።
የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲም በኤክስ ገጻቸው ላይ በቤተክርስትያኗ ላይ ስለተፈፀመው አሰቃቂ ተኩስ እና የእሳት ቃጠሎ መረጃ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
" በአምልኮ ሥፍራ ላይ እንዲህ ዓይነት ጥቃት መፈፀሙ ልብ የሚሰብር እና የሚያሳዝን ነው በዚህ አሳዛኝ ክስተት ለተጎጂዎች አብረን እንጸልይ" ብለዋል ቦንዲ።
የሚቺጋን ገዥ ግሪችብ ዊትምርም " በየትኛውም ቦታ በተለይ በአምልኮ ሥፍራ የሚፈፀም ጥቃት ተቀባይነት የለውም" በማለት ድርጊቱን ያወገዙ ሲሆን ሁኔታውን እየተከታተሉ እንደሆነ ገልጸዋል።
የቀድሞው የኡታህ ሴናተር እና ታዋቂ ፖለቲከኛ ሚት ሮምኒይ ጥቃቱን አሳዛኝ ያሉት ሲሆን " ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም ቤተክርስትያናቸው የጥቃቱ ኢላማ ሆነዋል፤ የተጎዱት እንዲያገግሙ እና እንዲፅናኑ እየፀለይኩ ነው" ብለዋል።















