የኒውክሌር ፍንዳታን የሚቋቋሙት እና ጥይት የማይበሳቸው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አውሮፕላን እና መኪኖች

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ከኤር ፎርስ ዋን ወርደው አቀባበል ሲደረግላቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ከኤር ፎርስ ዋን ወርደው አቀባበል ሲደረግላቸው

ዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በጉብኘት ላይ ናቸው። በዚህ ጉዟቸው ላይም በርካታ ሰዎች እና የተለያዩ መገልገያዎቻቸው አብረዋቸው ይጓዛሉ።

ትራምፕ በዩናይትድ ኪግደም በሚያደርጉት ጉብኝት ላይ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጪ ይደረጋል።

የምሥጢራዊ ደኅነንት ጥበቃ አገልግሎት የሆነው ሴክሬት ሰርቪስ የሚባለው የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶችን በየትኘውም ቦታ የሚጠብቀው የደኅንነት ቡድን አባላትም በዙሪያቸው ያልተቋረጠ ጥበቃ ያደርጉላቸዋል።

በተጨማሪም በሺህዎች የሚቆጠሩ የዩናይትድ ኪንግደም የፖሊስ መኮንኖችም የጥበቃው አካል ናቸው።

ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2019 ባደረጉት የመጀመሪያው ኦፊሴላዊ ጉብኝት ከስድስት ሺህ በላይ የዩኬ ፖሊስ መኮንኖች ተሰማርተው ነበር። ለዚያ ጉብኝትም 3.4 ሚሊዮን ፓውንድ የሚገመት ገንዘብ ወጪ መደረጉ ተነግሯል።

አሜሪካ ውስጥ አንድ ወጣት ወግ አጥባቂውን አክቲቪስት ቻርሊ ከርክን መግደሉን ተከትሎ የፕሬዝዳንቱ ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክሯል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶችን ደኅንነት በሚጠብቀው ሴክሬት ሰርቪስ ዙሪያ የጠለቀ ዕውቀት ያላቸው ደራሲው ሮናልድ ኬስለር የፕሬዝዳንቱ ጉዞ የረጅም ጊዜ ዕቅድ መሆኑን ይናገራሉ።

ለኦፊሴላዊ ጉብኝት ዝግጅት የሚጀምረው ፕሬዝዳንቱ ከመጓዛቸው "ከብዙ ሳምንታት በፊት" መሆኑን በመግጽ፣ ዝግጅቱ ጉብኝት በሚደረግበት አካባቢ ካሉ ፖሊሶች ጋር ውይይቶችን ማድረግ እና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን መከታተልን ያካትታል ብለዋል።

ወደ 60 የሚጠጉ የሴክሬት ሰርቪስ ባለደረቦች ፕሬዝዳንቱን በቀጥታ የመጠበቅ ኃላፊነት ይጣልባቸዋል ተብሎ ይገመታል። ፖሊሶች ደግሞ እጀባ ማድረግ፣ የመኪና እና የሰዎችን እንቅስቃሴ እና የአየር ክልልን የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጉዞ በሚያደርጉበት ጊዜ በቡድናቸው ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኃላፊዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ይካተታሉ ተብሎ ይታመናል።

የኤር ፎረስ ዋን ንድፍ

ዋይት ሐውስ በሰማይ ላይ

ከባለቤታቸው ሜላኒያ ጋር ጋር ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የገቡት ትራምፕ በልዩ መልኩ በተሠራው ቦይንግ 747-200ቢ አይሮፕላን ተጉዘዋል። ይህ አውሮፕላን ኤር ፎርስ ዋን በመባል ይታወቃል።

ኤር ፎርስ ዋን አንድ አውሮፕላን ብቻ አይደለም። ከሁለት በልዩ ሁኔታ ከተመረቱት የቦይንግ 747-200ቢ አውሮፕላኖች አንዱን ነው። የእነዚህ ፕሬዝዳንታዊ አውሮፕላኖች መለያ ኮድ 28000 እና 29000 ነው።

ኤር ፎርስ ዋን ከውጭ ሲታይ ከመደበኛው የመንገደኞች አውሮፕላን ጋር ይመሳሰላል። ባሉት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች እና በመከላከያ ዘዴዎች ምክንያት ግን ወታደራዊ አውሮፕላን ከሚባሉት መካከል ይመደባል።

አውሮፕላኑ የአየር ጥቃትን ለመቋቋም እና የጠላትን ራዳር ለማደናቀፍ ተደርጎ ነው የተገነባው።

ሙቀት ያላቸውን ዒላማዎች በመከተል የሚመቱ ሚሳዔሎችን ለመከላከል የሚያስችለው ሥርዓትም አለው።

አውሮፕላኑ በጉዞ ላይ ሳለ ነዳጅ ቢያስፈልገው ሳያርፍ አየር ላይ ሆኖ ነዳጅ መሙላት ይችላል። ይህም በአደጋ ወቅት ላልተወሰነ ጊዜ ሳያርፍ ለረጅም ሰዓታት እንዲበር ያስችለዋል።

ውስጡ ለፕሬዝዳንቱ እና አብረዋቸው ለሚጓዙ ሰዎች የሚሆን አራት ሺህ ካሬ ጫማ ስፋት የሚሆን ቦታ አለው። ይህም በሦስት እርከኖች የሚገኝ ነው።

ለፕሬዝዳንቱ የሚሆን ሰፊ ክፍል፣ የቀዶ ሕክምና ማከናወን የሚያስችል የሕክምና ክፍል እና ለጋዜጠኞች፣ ለደኅንነት ሠራተኞች እና ለፀሐፊዎች የተመደቡ ቦታዎችንም አካቷል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ባለቤታቸው ሜላኒያ ወደ ኤር ፎረስ ዋን አውሮፕላን ሲገቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ባለቤታቸው ሜላኒያ ወደ ኤር ፎረስ ዋን አውሮፕላን ሲገቡ

ፕሬዝዳንቱ በመሬት ላይ

ፕሬዝዳንቱ ከአውሮፕላን ሲወርዱ ሌላው ቅንጡ እና ደኅንነቱ የተጠበቀው መኪናቸው ካዲላክ ዋን ይጠብቃቸዋል።

ይህ በልዩ ትዕዛዝ የተሠራው ሊሙዚን "አውሬው" (The Beast) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ስያሜውን ያገኘው ያለምክንያት አይደለም።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን የሚያጅቡ መኪኖች በአውሮፕላን ተጭነው

የፎቶው ባለመብት, US Secret Service via X

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን የሚያጅቡ መኪኖች በአውሮፕላን ተጭነው

ትራምፕ ዩናይትድ ኪንግደም ከመድረሳቸው በፊት ሁለት ተመሳሳይ የሆኑት ሊሙዚኖች በወታደራዊ አውሮፕላኖች ቀድመው ወደዚያ ተወስደው ተዘጋጅተው ጠብቀዋቸዋል።

በተጨማሪም በርካታ የሴክሬት ሰርቪስ መኪኖችም አብረው ተወስደዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን የሚያጅቡ መኪኖች በአውሮፕላን ተጭነው

የፎቶው ባለመብት, US Secret Service via

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን የሚያጅቡ መኪኖች በአውሮፕላን ተጭነው

ፕሬዝዳንቱ በአንዱ ቢስት ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። ሁለተኛው መኪና ፕሬዝዳንቱ የትኛው ውስጥ እንዳሉ እንዳይታወቅ ያጅባቸዋል። ሁለቱም 800-002 የሚል የዋሽንግተን ዲሲ ሰሌዳዎችን ይጠቀማሉ።

የሴክሬት ሰርቪስ እና የተሽከርካሪው አምራች ጄነራል ሞተርስ ስለሊሙዚኖቹ ዝርዝር መረጃ ለማንም ፈጽሞ አይሰጡም። ነገር ግን መኪኖቹን የተመለከተ ያላቸው አንዳንድ የደኅንነት ገጽታዎች ይታወቃሉ።

መኪኖቹ ጥይት የማይበሳቸውው አካል እና መስታወቶች ተገጥመውላቸዋል። ከዘጠኝ ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ለመመዘናቸው ደግሞ ያላቸው የደኅንነት መከላከያ አንደኛው ምክንያት ነው።

በተጨማሪም አስለቃሽ ጭስ ማስወንጨፊያዎች፣ በምሽት የሚያሳዩ ካሜራዎች እና የሳተላይት ስልክ እንደተገጠሙላቸው ይነገራል።

ዘ ቢስት

በቅርቡ የተመረቱት ዘ ቢስት ተሽከርካሪዎች ለሕክምና አገለግሎት የሚውል ኦክስጂን የተገጠመላቸው ሲሆን በተመሳሳይ ማቀዝቀዣ ያላቸው ናቸው።

ማቀዝቀዣው ለድንገተኛ የአደጋ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል ከፕሬዝዳንቱ የደም ዓይነት ጋር የሚመሳሰል ደም ለመያዝ የሚያስችል መሆኑም ተዘግቧል።

ዘ ቢስት የሚንቀሳቀስው ከፕሬዝዳንቱ አጃቢ መኪኖች አንዱ ሆኖ ነው። በዚህ ውስጥ ከአስራ ሁለት በላይ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን ይኖራሉ።

የፖሊስ አጃቢዎች፣ የመልሶ ማጥቃት አባላት እና ጥቃት ፈጻሚ ቡድኖች፣ የታጠቁ የመገናኛ ተሽከርካሪዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎች እና ተጓዳኝ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መኪኖችም አብረው ይጓዛሉ።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ሜላንያ ትራምፕ እአአ በ2019 በዩናይትድ ኪንግደም ጉብኝት አድርገው ነበር

የፎቶው ባለመብት, DANIEL LEAL/AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ሜላንያ ትራምፕ እአአ በ2019 ከዩናይትድ ኪንግደም ባኪንግሃም ቤተመንግሥት ሲወጡ

አጃቢ መኪኖች አብረው ሲንቀሳቀሱ ፕሬዝዳንቱ የሚጓዙበት ተሽከርካሪ ለተመልካቾችም ሆነ ጥቃት ለመፈጸም ለሚፈልጉ ግልጽ ላይሆን ይችላል።

አስኪ ወይም አሳሳቢ ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ የፕሬዝዳንቱ ደኅንነት ጥበቃ አባላት (ሴክሬት ሰርቪስ) "ትራምፕን ከአንድ መኪና ወደ ሌላ መኪና ማዘዋወር ይችላሉ" ብለዋል ኬስለር።

የሰማይ ላይ ጉዞ

ትራምፕ ጥቂት አጫጭር ጉዞዎችን በሊሙዚን ያደርጋሉ። አብዛኛውን ጉዞቸውን በአየር ላይ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ሐምሌ ወር ወደ ስኮትላንድ ተመሳሳይ ጉዞ አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቱ ብዙ ሄሊኮፕተሮችን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ይዘው ነው የተጓዙት። ከእነሱም መካከል ማሪን ዋን ይገኝበታል።

ይህ ሄሊኮፕተር እንደ ኤር ፎርስ ዋን የተለየ አውሮፕላን ባይሆንም ፕሬዝዳንቱን የሚያጓጉዝ የአሜሪካ ልዩ የባሕር ኃይል (ማሪን) ኮርፕ አውሮፕላን ነው።

ለዚህ ጉዞ ጥቅም ላይ የሚውለው ሞዴል ባለፈው ሳምንት በዊንድሰር ላይ ሲበር የታየውን ሲኮርስኪ ቪኤኤች-3ዲ ሲ ኪንግ ነው።

ማሪን ዋን

እነዚህ ልዩ ሄሊኮፕተሮች "ዋይት ቶፕ" በመባል ይታወቃሉ። ስያሜያቸውን ያገኙት የሚሳዔል መከላከያ እና ራዳሮችን የማፈን ሥርዓት እንዲሁም የኒውክሌር ፍንዳታ ኤሌክትሮማግኔቲክ ንዝረትን ለመቋቋም የተሠሩ በመሆናቸው ነው።

የሄሊኮፕተሮቹ ደኅንነታቸው ለመጠበቅ ሲባል እና ፕሬዝዳንቱ የተሳፈሩበትን ለይቶ ለማጥቃት አዳጋች ለማድረግ በሚል ተመሳሳይ የማሪን ዋን ሄሊኮፕተሮች ቡድን በአንድ ላይ እንዲበሩ ይረጋል።

በተጨማሪም በሁለት ወይም በሦስት ኦስፕሪ ኤምቪ-22 ሄሊኮፕተሮች ይታጀባል። እነዚህ አውሮፕላኖች "ግሪን ቶፕስ" እየተባሉ የሚጠሩ እና በጎን የማረፍ አቅም ያላቸው ናቸው። ያላቸው የበረራ ፍጥነት እና ብቃትም ተመራጭ ያደርጋቸዋል።

ኦስፕሬይስ የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን፣ የልዩ ኃይል አባላትን እና የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረቦችን ያጓጉዛሉ። እነዚህ ደግሞ በበረራ ወቅት የሚያጋጥምን ድንገተኛ አደጋ የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለባቸው ናቸው።

ኦስፕሬይ አውሮፕላቸች ቅኝት ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Warren Little/Getty Images

ኦስፕሬይ ሄሊኮፕተሮች ሲያኝዣብቡ እና ለማረፍ ሲቃረቡ ከፍተኛ ድምጽ ያሰማሉ። ፕሬዝዳንቱ በአውሮፓውያኑ 2019 በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ባደረጉት የመጀመሪያው ጉብኝታቸው ወቅት በለንደን ዙሪያ ሲሽከረከሩ ታይተዋል።

ሌሎች የፕሬዝዳንቱ ሠራተኞችም በአውሮፕላን ነው የሚጓዙት። ይህ ደግሞ በትራምፕ ጉዞ ወቅት በርካታ አውሮፕላኖች አብረዋቸው እንዲጓዙ የሚያስገድድ ነው።

የድሮኖች ስጋት

ንጉሥ ቻርለስ ሳልሳዊ እና ንግሥት ካሚላ ፕሬዝዳንት ትራምፕን እና ባለቤታቸውን በዊንድሶር ቤተ መንግሥት ተቀብለው ያስተናግዳሉ።

ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ አውሮፕላኖች በቤተ መንግሥቱ አካባቢ እንዲበሩ አይፈቀድላቸውም ብሏል የአካባቢው ፖሊስ። ይህንን ለማገዝ ብሔራዊ የአየር ፖሊስ አገልግሎት እገዛ ያደርጋል።

እንደኬስለር ከሆነ ድሮኖች የሚፈጥሩት ስጋት ለሴክሬት ሰርቪስ ልዩ እና አዲስ የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል።

ትራምፕ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን በሚፎካከሩበት ጊዜ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ወቅት የሴክሬት ሰርቪሱ የፀረ-ድሮን አቅም ጉድለቶች እንዳሉበት ጎልቶ ታይቷል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ኪንግደም ለሁለት ቀናት ይቆያሉ። ከሕዝብ ጋር ፊት ለፊት የሚገናኙበት መርሃ ግብር ግን አልተያዘም።

ንጉሣዊው ቤተሰብ በቀይ ምንጣፍ ለፕሬዝዳንቱ እና ለባለቤታቸው ታላቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የዩናይትድ ኪንግደም እና የአሜሪካ ወታደራዊ ጄቶች ሰማይ ላይ ታይተዋል።

በዊንድሰር እና በማዕከላዊ ለንደን በተደረጉ ፀረ-ትራምፕ ሰልፎች ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሳትፈዋል ይጠበቃል።