በአሜሪካ ስደትን አሸንፈው ስደተኞችን የሚረዳ ተቋም የገነቡት ኢትዮጵያዊ ዶ/ር ፀሐየ ተፈራ

የፎቶው ባለመብት, ECDC
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ለስደተኞች ባደረጉት እገዛ 'ሻምፕዮንስ ኦፍ ቼንጅ' ከሚል ሽልማት ጀምሮ ለግማሽ ምዕተ ዓመት እስከ በኖሩባት የቨርጂኒያዋ አርሊግንተን ካውንቲ የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።
ትግራይ ውስጥ ከምትገኘው ድምባዛ የገጠር ቀበሌ ተነስተው በአሜሪካዋ ቨርጂንያ ግዛት የስደት ኑሯቸውን የጀመሩት ዶ/ር ፀሐየ ተፈራ፣ ዛሬ በአሜሪካን አገር ስደተኞችን በማቋቋም እና ከማኅበረሰቡ ጋር በቀላሉ እንዲዋሀዱ ከሚሠሩ ትላልቅ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነውን "ኢትዮጵያን ኮሙኒቲ ዴቨሎፕመንት ካውንስልን" (ECDC) አቋቁመው በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ይመራሉ።
"አሁን ላለሁበት የትምህርት እና የሕይወት ደረጃ ለመድረስ ወላጅ አባቴን ትልቅ ሚና ነበራቸው" ይላሉ ልጅነታቸውን ሲያስታውሱ።
ልጅነታቸውን በድምባዛ ያሳለፉት ዶ/ር ፀሐየ ተፈራ፣ 25 ሳንቲም (ስሙኒ) እያስከፈሉ ማመልከቻ በመጻፍ ገቢ ያገኙ ነበር።
ወላጅ አባታቸው ፊታውራሪ ተፈራ አሉላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የአካባቢው ማኅበረሰብ አስተዳዳሪ ስለነበሩ፣ ልጆቻቸው ተምረው ተመራማሪዎች እንዲሆኑ በማሰብ የቤተ ክህነት ቀሳውስትን ሳይቀር ቤታቸው በመቅጠር ፊደል ያስቆጥሯቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
"አባታችን 15 ልጆች ነው የወለደው። ወደ ትምህርት ቤት ገብተን የትምህርት ዕድል ያገኘነው ግን እኔን ጨምሮ ከእኔ በታች ያሉት ናቸው። ቄሶቹ ፊደል እና ማንበብ ብቻ ነበር የሚያስተምሩን" ይላሉ ዶ/ር ፀሐየ።
ከዚያም ከትውልድ መንደራቸው 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ጥንታዊቷ አክሱም ከተማ ተጉዘው የመንግሥት ትምህርት ቤት ገቡ።
ከትምህርት መልስ ደግሞ በመሬት ይገባኛል የሚካሰሱትን አርሶ አደሮች 25 ሳንቲም እያስከፈሉ ማመልከቻ ይጽፉላቸው እንደነበር የሚናገሩት ዶ/ሩ፣ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው በአክሱም እና መቀለ አጠናቅቀው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል።
በኢትዮጵያ መምህር ሆነው ለጥቂት ዓመታት ካስተማሩ በኋላ እአአ በ1972 ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ አሜሪካን አቀኑ።
በጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ጨርሰው በዚያው ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ፣ በሐዋርድ ዩኒቨርስቲ ደግሞ መምህር ሆነው ሠርተዋል።
ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወደ አገር ቤት የመመለስ ዕቅድ ቢኖራቸውም የአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት በደርግ የተተካበት ጊዜ ስለነበር የመመለስ ሐሳባቸው ሰርዘው እዚያው አሜሪካን አገር የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው መኖር ጀመሩ።
ዶ/ር ፀሐየ ከዚያም በፊት በሥራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ስለነበር፣ የስደት ኑሮ እንደ ሌላው ስደተኛ አልከበዳቸውም።
አገር ቤት አስተማሪ የነበረን ሰው አሜሪካን አገር ከሄደ በኋላ መምህር ሆኖ የመሥራት ዕድል አለው፤ ሆኖም ግን የአገሪቱ ሥርዓት፣ ሥርዓተ ትምህርት እና የሥራ ልምድ ከሌለ ስለማይቀበሉ አብዛኛው ዝቅ ብሎ እንዲጀምር ይገዳዳል ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, ECDC
ባለፉት አሥርት ዓመታት የነበሩ በተለይ ደግሞ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በስደተኞች ላይ በራቸውን ከመዝጋት በተጨማሪ ጠንካራ እርምጃዎችን በመውሰዳቸው ሁኔታዎች እንደተለወጡ እየታየ ነው።
በዚህም ምክንያት ቀደም ባለው ዘመን በአሜሪካ ውስጥ ለስደተኞች የነበሩት ዕድሎች እየጠበቡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው።
ከ53 ዓመታት በፊት ወደ አሜሪካ ያቀኑት ዶ/ሩ ፀሐየ "እኔ ወደ አሜሪካ በገባሁነት ጊዜ የሚሰደድ የሐበሻ ቁጥር ጥቂት ስለነበር የሥራ ዕድል ከማግኘት አንጻር ሲታይ ከዛሬው የተሻለ ነበር።
"ቢሆንም ግን የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር ጥቂት ከመሆኑ የተነሳ ፍላጎቶቹ በቀላሉ የሚገኙባቸው የሐበሻ ሱቆች እና አብያተ ክርስቲያን ስላልነበሩ ሰው በናፍቆት ይሰቃይ ነበር" ይላሉ።
በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ብቸኝነት የሚያጠቃቸው ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ያጠፉ እንደነበር የሚያስታውሱ ዶ/ር ፀሐየ በአሁኑ ጊዜ ግን ሌላው ቀርቶ እንግሊዘኛ ቋንቋ የማይነገርባቸው የአሜሪካ አካባቢዎች እንዳሉ ይናገራሉ።
"ለምሳሌ ዲሲን እንደ ምሳሌ በመውሰድ በየቦታው ቤተ ክርስቲያን አለ፤ በየሄድክበት የአገርህን ሰው ታገኛለህ ያማረህን ገዝተህ የምትበላበት የሐበሻ ምግቤ ቤቶች ሞልተዋል። አንዳንድ የአሜሪካ ሰፈሮች የሐበሻው ብዛት ኢትዮጵያ ያለን እስኪመስል ድረስ ነው" ይላሉ።
የትራምፕ አስተዳደር ከስደተኞች ጋር በተያያዘ በያዘው አቋም ምክንያት አሜሪካ ለስደተኞች የማትመች አገር እንደሆነች የተናገሩት ዶ/ር ፀሐየ በዚህም ሳቢያ ብዙ ስደተኛ ሽብር ውስጥ ገብቷል ይላሉ።
እሳቸው ወደ አሜሪካ ባቀኑበት ጊዜ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ገቢ ቢኖራቸውም በብቸኝነት ስሜት ይጠቁ ስለነበር 'እገሌ ሐኪም ቤት ነው። እገሌ ደግሞ እስር ቤት ነው' የሚል መረጃ በየጊዜው ይደርሳቸው ነበር።
በዚህም ምክንያት በተለያዩ ችግሮች እየተፈተኑ የነበሩትን ስደተኛ የአገራቸውን ሰዎች ለመደገፍ በአውሮፓውያኑ 1983 የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ዴቨሎፕመንት ካውንስል (ECDC) የተባለውን ድርጅት አቋቋሙ።
ይህ ለትርፍ ያልተቋቋመው ድርጅት የኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአሜሪካ ውስጥ መልሰው እንዲቋቋሙ ለማድረግ የሚያስችል ድጋፍ በመስጠት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ድልድይ ሆኖ የሚያገልግል ነው።

የፎቶው ባለመብት, ECDC
የተቋሙ ስም በኢትዮጵያ ቢጠራም ዩክሬን እና አፍጋኒስታንን ጨምሮ ከ18 የአፍሪካ አገራት የመጡ ስደተኞችን እንደሚረዳ የሚናገሩት መሥስራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፀሐየ በ2024 ብቻ ከአስር ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች እንዳቋቋሙ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
ድርጅታቸው በዚህ ዓመትም ከ12 ሺ የሚበልጡ ስደተኞችን ለማቋቋም እና ከማኅበረሰቡ ጋር ለማዋሃድ ዕቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ከስደተኞች ጋር በተያያዘ በወሰዳቸው እርምጃዎች ምክንያት ዕቅዳቸው ሳያሳካ ቀርቷል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገር ቤት ላሉ የቅርብ ዘመዶቻቸው እና ጓደኞቻቸው እያለፉበት ስላሉት ትክክለኛ የስደት ሕይወት ስለማይነግሯቸው ብዙ ሐበሾች ወደ ውጭ መውጣትን እንደ ትልቅ ስኬት እንዲያስቡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
በተለይም አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞች የተረጋጋ ሕይወት እንዳይራቸው እያደረገ እንደሚገኝ እና "የመኖሪያ ፈቃድ (ግሪን ካርድ) የነበራቸውን እና ዜጋ ለመሆን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ጭምር ግሪን ካርዱን እንዴት እንዳገኙት እናጣራለን እንደሚሉ፤ በትናንሽ ጥፋቶች ከአገር እንዲባረሩ እስከማድረግ እንደደረሱ እየታዘብን ነው ያለነው" ብለዋል።
ጥገኝነት ጠይቀው ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያገኙ ስደተኞችም 'እንዴት እና በማን ጊዜ እንዳገኛችሁት እናጣራለን' እያሉ የሚያስፈራሩበት ጊዜ ስለሆነ ወደ አሜሪካ የሚደረግ ስደት የሚመከር አይደለም ይላሉ።
አንዳንድ ሰዎች ይህን መሰል ምክር በሚሰጡበት ጊዜ 'ታድያ አንተ ለምንድን ነው እዚያ ለመኖር የመረጥከው?' የሚል ጥያቄ እንደሚያነሱላቸው የሚናገሩት ዶ/ሩ "እኛ ወደ ስደት የወጣንበት እና አሁን ያለው ሁኔታ የተለያየ ነው" ይላሉ።
ድሮ ምዕራባውያን መንግሥታት ከአፍሪካ ስደተኞች ለመውሰድ በይፋ የሚጋብዙበት ጊዜ እንደነበር በመጥቀስም አሁን ግን ሁሉም በሚባል ደረጃ ለስደተኞች በራቸውን እየዘጉ በመሆናቸው ስደት ሲነሳ ደጋግሞ ማሰብ ያስፈልጋል ይላሉ።
በዶ/ር ፀሐየ ተፈራ የሚመራው የኢትዮጵያ ኮሚውኒቲ ዴቨሎፕመንት ካውንስል ስደተኞችን ከመርዳት ባለፈ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ እገዛ የሚያደርግ ሲሆን፣ ከጋምቤላ እና ከሶማሌ ክልሎች ውጪ በመላው አገሪቱ ከአምስት መቶ ሺህ እስከ 1.5 ሚሊዮን በላይ መጽሐፍቶችን እንደረዳ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በዚያች 25 ሳንቲም አስከፍለው ለገበሬዎች ማመልከቻ ይጽፉባት በነበረችው የትውልድ ቀያቸው ድምባዛ፣ ለአካባቢው ልጆች እርሳቸውን በአቅራቢያቸው ያላገኙትን የትምህርት ዕድል ለሟሟላት ትምህርት ቤት አስገንብተዋል።
በተጨማሪም በታሪካዊቷ የአክሱም ከተማ ደረጃውን የጠበቀ ቤተ መጽሐፍት አስገንብተው ለአካባቢው ተማሪዎች አገልግሎት ማብቃታቸውን ገልጸዋል።















