የቱርክ የዋጋ ግሽበት በ24 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቱርክ ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ነው የተባለለት የዋጋ ግሽበት አጋጠመ።
በአገሪቱ ያለው የዋጋ ግሸበት 83 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
ትራንስፖርት፣ ምግብ እና የቤት ዘርፎች ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል።
ኢንፍሌሽን ሪሰርች ግሩፕ የሚባለው ገለልተኛ የአጥኚዎች ቡድን ዓመታዊውን የዋጋ ግሽበት 186.7 በመቶ ያደርሰዋል።
ባለፈው ዓመት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት በሚል ባልተለመደ ሁኔታ የወለድ ምጣኔውን ቀንሰው ነበር። በርካታ ባንኮች ደግሞ የዋጋ ግሽበቱን ለመከላከል የወለድ መጠናቸውን ከፍ አድርገው ነበር።
የትራንስፖርት ዘርፉ 117.66 በመቶ የዋጋ ግሽበት በማስመዝገብ ቀዳሚ ነው። ምግብ እና ከአልኮል ነጻ የሆኑ መጠጦች በ93 በመቶ ይከተላሉ።
የምጣኔ ሃብት ፖሊሲያቸው በውጭ ምንዛሪ ገበያ ውስጥ ጣልቃ መግባትን የሚያካትተው ኤርዶሃን፤ የወለድ ምጣኔን “የሁሉም ሴጣኖች እናት እና አባት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት የወለድ ምጣኔ ከ19 በመቶ ወደ 14 በመቶ መቀነሱ የአገሪቱን መገበያያ ገንዘብ ሊራን ዋጋ ቀንሶታል። ይህም አገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸው ዕቃዎችን በከፍተኛ ዋጋ እንድትገዛ ያስገድዳታል።
ሊራ ከዶላር አንጻር ያለው ልዩነት ክብረወሰን በሆነ ደረጃ ቀንሶ 1 የኤሜሪካ ዶላር በ18.56 ሊራ እየተመነዘረ ነው።
የአሜሪካው ባንክ ጂፒ ሞርጋን እንዳለው የቱርክ የዋጋ ግሽበት “የፖሊሲ ለውጥ ካልተደረገ ባልተለመደ መልኩ ከፍተኛ ይሆናል።”
ሰኞ ምሽት ቴሌቭዥን ፊት የቀረቡት ፕሬዝዳንት አርዶሃን “ይህንን የዋጋ ግሽበት ችግር አራግፈን በጋራ ጠንካራዋን ቱርክ እንገነባለን” ብለዋል።
ይህ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ጭማሪ የተከሰተው ከሁለተኛው የዓለም ጦርንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሲሉ የቀድሞው የቱርክ ማዕከላዊ ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት ሃካን ካራ ተናግረዋል።
ከሚቀጥለው ሃገራዊ ምርጫ በፊት የዋጋ ግሽበት እና የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የኤርዶሃንን ፓርቲ ፈተና ይሆናል ተብሏል።
ከኮቪድ-19 ስርጭት ጋር በተያያዘ በተከሰተ የአቅርቦት መስተጓጎል በመፈጠሩ እና የነዳጅ እና የምግብ ዋጋን ካናረው የዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ጭማሪ እየተከሰተ ነው።












