ታጣቂዎች በሙገር ሲሚንቶ የሠራተኞች አውቶቡስ ላይ ተኩስ ከፍተው ሰዎች ተገደሉ

መገር ሲሚንቶ ፋብሪካ

የፎቶው ባለመብት, Mugher Cement Factory/fb

የምስሉ መግለጫ, ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ይገኛል

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ታጣቂዎች በሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ የሠራተኞች ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ተኩስ ከፍተው በፈጸሙጥ ጥቃት ቢያንስ ሁለት ሰዎችን ሲገደሉ በርካቶች ቆሰሉ።

ቢቢሲ ከሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች እና ከአካባቢው ነዋሪዎች እንዳረጋገጠው ጥቃቱ የተፈጸመው ዛሬ ሰኞ መስከረም 23/2015 ዓ.ም. ንጋት 12 ሰዓት አካባቢ ነው።

ነዋሪዎችና ሠራተኞች እንዳሉት ጥቃቱን የፈጸመው መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀውና በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም ሸኔ ነው።

በሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች ላይ ጥቃት የተፈጸመው የሠራተኞች ማመላለሻ አውቶቡስ የሲሚንቶ ግብዓት ወደሚወጣበት አካባቢ እየተጓዘ ሳለ በታጣቂዎች በተከፈተባቸው ተኩስ ነው።

በዚህ ጥቃት ቢያንስ ሁለት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ12 ያላነሱ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል። በአውቶብሱ ምን ያክል ሰዎች ተሳፍረው እንደነበረ ግን ግልጽ አይደለም።

ቢቢሲ ጥቃቱን በማስመልከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኦሮሚያ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ከፍያለው ተፈራን ቢጠይቅም መረጃ እንደሌላቸው ሲገልጹ፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ እና የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ እና አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ መልሰን እንድንደውል ነግረውናል።

በተጨማሪም ስለደረሰው ጉዳት ለመጠየቅ ተሽከርካሪው ላይ ጥቃት የተፈጸመበትን የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

አድፍጠው ሲጠብቁ የነበሩት ታጣቂዎች

ቢቢሲ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንደተረዳው ከሆነ ሠራተኞቹ በአውቶቡሱ እየተጓዙ ሳለ አድፍጠው ይጠብቁ የነበሩት ታጣቂዎች የተሸካርካሪውን ጎማ ጨምሮ የተለያየ የመኪናውን አካል በጥይት መትተዋል።

ተሳፋሪዎች እና ተሸከርካሪው በጥይት ይደብደቡ እንጂ የአውቶብሱ አሸከርካሪ መኪናውን ሳያቆም የፊት ጎማው በጥይት የተመታ መኪናውን እያሸከረከረ የሲሚንቶ ግብዓት ከሚወጣበት ቦታ ላይ ደርሷል።

ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ከወገባቸው በታች ያለ የሰውነት ክፍላቸው በጥይት ተመትቶ መቁሰላቸውን እማኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ከሲሚንቶ ፋብሪካው ሠራተኞች እንደተረዳው በአካባቢው ያሉ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለምርታቸው ግብዓት የሚሆናቸውን ላይምስቶን የተሰኘ የድንጋይ አይነት ከፋብሪካው በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኝ አካባቢ ይወስዳሉ።

ለሲሚንቶ ምርት ግብዓት የሚወጣበት አካባቢ በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጥበቃ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፤ ከታጣቂዎች ተኩስ ያመለጠው የሠራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ ከጥቃቱ በኋላ የፀጥታ አስከባሪዎች እስካሉበት ቦታ ድረስ በቸርኬ ተጉዞ መድረሱን ቢቢሲ ከፋብሪካው ሠራተኛ እና ከነዋሪዎች ለማውቅ ችሏል።

ያልተለመደ ጥቃት

መንግሥት ሸኔ የሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚገኙበት ምዕራብ ሸዋ አድአ በርጋ ወረዳ እና ዙሪያው ነው።

በዚህ አካባቢ ታጣቂ ቡድኑ የፋብሪካ ሠራተኞች እና ነዋሪዎችን በማገት የማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቅ የተለመደ ይሁን እንጂ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ መክፈት የተለመደ አይደለም።

ይሁን እንጂ በዚህ አካባቢ ሰላማዊ ሰዎች ከመንግሥት ወይም ከታጣቂዎች ጋር ተባብራችኋላ በሚል ምክንያት በታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በዚሁ አደአ በርጋ ወረዳ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በታጣቂዎች ከተገደሉ በኋላ አርብ ሚያዚያ 21/2014 ዓ.ም. የፖሊስ አባላቱ በወሰዱት እርምጃ በርካታ ንጹሃን ሰዎችን መግደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። ነዋሪዎች በዚህ ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ቁጥርን ከ21 እስከ 40 አድርሰውት ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ለመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላት ወደውም ሆነ ተገደው የትራንስፖርት አገልግሎት የሰጡ ሰላማዊ ሰዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸው ያውቃል።

ከምዕራብ ሸዋ ባሻገር በሌሎች የወለጋ ዞኖች ባለፉት ወራት ውስጥ ተፈጽመው በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑ ጥቃቶችን ፈጽሟል ተብሎ ታጣቂው ቡድን ይከሰሳል።

ቡድኑ ግን እነዚህ ጥቃቶች አልፈጸምኩል በማለት ሲያስተባብል ቆይቷል። ዛሬ ስለተፈጸመው ጥቃት ግን አስካሁን በቡድኑ በኩል የተባለ ነገር የለም።