ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ ጦር መሳሪያ ስለማቅረቧ ምንም አይነት ማስረጃ እንደሌለ ተገለጸ
ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ ጦር መሳሪያ ስለማቅረቧ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ እንዳልተገኘ ተገለጸ።
ይህንን ለማጣራት የተቋቋመው ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ምንም አይነት ማስረጃ አላገኘም ሲሉም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ገልጸዋል።
በደቡብ አፍሪካ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉት የአሜሪካ አምባሳደር ሩበን ፕሪጌቲ በኬፕታውን ወደብ ላይ የሩሲያ መርከብ የጦር መሳሪያ ጭናለች ያሉትን ክስም ኮሚሽኑ ውድቅ አድርጓል።
የአምባሳደሩ ውንጀላ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ላይ የገለልተኛነት ሚና አለኝ በምትለው ደቡብ አፍሪካ ላይ ጥያቄ አስነስቶባታል።
ፕሬዚዳንት ራማፎሳ “ክሱ የአገሪቱን ምንዛሬ ጎድቷል፤ እንዲሁም መልካም ስም አጉድፏል” ብለዋል።
“መርከቧ ከደቡብ አፍሪካ የጦር መሳሪያ ጭና ወደ ሩሲያ አቅንታለች የሚለውን ክስ የሚያረጋግጥ ምንም አይነት መረጃ ማስረጃ ኮሚሽኑ አላገኘም” ሲሉም ፕሬዚዳንቱ እሁድ እለት በነበረው መግለጫቸው ተናግረዋል።
መርማሪው ኮሚሽን የጦር መሳሪያ የጫነች የሩሲያ የጭነት መርከብ ከሩሲያ ወደ ደቡበ አፍሪካ መድረሷንም በምርመራው ያገኘ ሲሆን የጦር መሳሪያው በአውሮፓውያኑ 2018 የታዘዘም ነው ብሏል።
አምባሳደር ሩበን ብሪጌት ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን የጫነች ሌዲ አር የተሰኘችው የሩሲያ መርከብ ኬፕታውን ነበረች ብለዋል።
አምባሳደሩ በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ በኬፕታውን በሚገኘው የባሕር ኃይል ሰፈር ቆማ የነበረችው የጭነት መርከብ በእርግጠኝነት የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን ጭና “ወደ ሩሲያ መመለሷን” ገልጸዋል።
የአምባሳደሩን አስተያየት ተከትሎም ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የሸጥኩት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ሬከርድ የለኝም ስትል ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ እንዲጣራ አዘው ነበር።
ከአንድ ቀን በኋላም አምባሳደሩ ለውንጀላቸው ይቅርታ መጠየቃቸውን የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አሜሪካዊው አምባሳደር ከደቡብ አፍሪካ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር ከተገናኙ በኋላም “በአደባባይ ላይ በሰጠሁት አስተያየት የተፈጠሩትን የተሳሳቱ አመለካከቶች ለማረም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ” ሲሉም በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር።
“የጦር መሳሪያ አቅርባችኋል ብለው የወነጀሉን በሙሉ ምንም አይነት ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም” በማለት ፕሬዚዳንት ራማፎሳ የአጣሪ ኮሚሽኑን መደምደሚያ ተናግረዋል።