ጋናዊው ጋዜጠኛ ጎድዊን አሴዲባ የ2025 የቢቢሲ ኮምላ ዱሞር ውድድርን አሸነፈ

ጋናዊው የምርመራ ጋዜጠኛ እና የዜና አንባቢ ጎድዊን አሴዲባ የቢቢሲ ኒውስ የ2025 ኩምላ ዱሞር ውድድር አሸናፊ ሆነ።

ውድድሩን ያሸነፈው የምርመራ ጋዜጠኛ፣ የፊልም ባለሙያ እና የዜና አንባቢ የሆነው ጎድዊን አሴዲባ በጋና ቲቪ 3 እና 3ኤፍኤም ይሰራል።

የጋዜጠኛው ስራዎች በበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ላይም ተላልፈዋል።

የ29 ዓመቱ ጋዜጠኛ ስራዎቹ የሚያተኩሩት ኢፍትሃዊነትን በማጋለጥ እና የተገለሉ ማኅበረሰቦችን ድምጽ በማጉላት በሚያልሙ የሰው ልጅ ታሪኮች ላይ ነው።

ይህ ሽልማት የተጀመረው ከአስር ዓመት በፊት በ41 ዓመቱ በድንገት ሕይወቱ ያለፈውን ባለድንቅ ችሎታው ጋናዊ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ኮምላ ዱሞርን ለማስታወስ ነው።

ከአፍሪካ አዲስ የሚወጡ ባለሙያዎችን ለማግኘትና ለማስተዋወቅ ዓላማን ላነገበው ለዚህ ሽልማት አህጉሪቱ ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች እንዲወዳደሩ ተጋብዘው ነበር።

የዘንድሮው አሸናፊ ጋናዊው ጎድዊን አሴዲባ ሽልማቱ ከተጀመረ አስረኛው አሸናፊ ሲሆን ከዚህ በፊት ከኬንያ፣ ከናይጄሪያ፣ ከኡጋንዳ የተወዳደሩ ጋዜጠኞች አሸንፈዋል።

ኩምላ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ አስተዋይ እና የሥራ ፈጣሪዎችን የሚወክሉ የአፍሪካ ድምጾችን በይበልጥ ለዓለም ለማሰማት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሰርቷል።

አሰዲባ "የኮምላ ትሩፋት የአፍሪካ ታሪኮችን በጥልቀት፣ በክብር እና ለእውነት ያለ ፍርሃት በቁርጠኝነት ሊነገሩ እንደሚገባ ያስታውሰናል" ብሏል።

ሽልማቱን ማግኘቱ ለጋናዊው "የግል ስኬቱ" ብቻ ሳይሆን "የጋዜጠኝነት መንፈስን የሚያነቃቃ፣ የሚያሳውቅ እና የሚለውጥ መንፈስ እንዲቀጥል የሚያደርግ" ነው።

የሽልማቱ ዳኞች በአሲዲባ የምርመራ ስራ እና ጋዜጠኝነት ላይ ያለው የማይናወጥ እምነት እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል።

በተለይ ከሚኮራባቸው ስራዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ችላ ተብሎ በነበረው እና የኅብረተሰብ ጤና ላይ ስጋት ፈጥሮ የነበረው የጋና ትልቁ የሬሳ ማቆያ ላይ ያደረገው የምርመራ ዘገባ ነው።

አሰዲባ አሁን ወደ ለንደን ተጉዞ ለሦስት ወራት ያህል ከቢቢሲ የዜና ቡድኖች ጋር በቴሌቭዥን ፣ በራዲዮ እና በኦንላየን ላይ ይሰራል።

በዋና ዋና የቢቢሲ ጋዜጠኞች ስልጠና ይወስዳል።

"ባለፉት አስርት ዓመታት የኮምላ ዱሞር ሽልማት የአፍሪካ ጋዜጠኞችን ለማሳደግ ረድቷል። እነዚህ ጋዜጠኞች በቢቢሲም ሆነ ከዚያ ውጭ ዘላቂ ተፅእኖ ሲፈጥሩ ማየት ትልቅ ዕድል ነው" ሲሉ የቢቢሲ የአፍሪካ ክልላዊ ዳይሬክተር ጁልየት ኒጄሪ ተናግረዋል።

"ይህ 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ለኮምላ ዱሞር ዘላቂ ውርስ ጠንካራ ምስክር ሆኖ ይቆማል። ለድፍረት፣ ለትክክለኛ ታሪክ እና ለአፍሪካ ድምጾች ያለው ፍቅር አሁንም አብሮን ይኖራል።"

አሴዲባ በአፍሪካ ውስጥ ወደሚገኝ አገር በመጓዝም ለቢቢሲ ዓለም አቀፍ ተመልካቾች የሚተላለፍ አንድ ዘገባ ያቀርባል።

ከዚህ ቀደም የተሸለሙት ሩኪያ ቡሌ፣ ፓአ ክዌሲ አሳሬ፣ ዲንጊንዳባ ጆናህ ቡዮያ፣ ቪክቶሪያ ሩባዲሪ፣ ሰለሞን ሰርዋንጃ፣ ዋሂጋ ምዋውራ፣ አሚና ዩጉዳ፣ ዲዲ አኪኒሉሬ እና የመጀመርያዋ አሸናፊ ናንሲ ካኩንጊራ ናቸው።

ባለፈው ዓመት ቡሌ ስለ ባዬ ፏፏቴ ለመዘገብ ወደ ሴኔጋል ተጉዟል።