ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሕዳሴ ግንባታ ጋር በተያያዘ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮችን አመሰገኑ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ይመረቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ግንባታ በማስጀመራቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የጉባ ላይ ወግ" በተሰኘ እና በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሰኞ ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም. በሚኒስትር ማዕረግ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪያቸው ከሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት ነው ምስጋናቸውን ያቀረቡት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ2003 ዓ.ም. ወቅቱ በሁሉም ዘርፍ ምቹ መሆኑን ተገንዝበው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማስጀመራቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ይሄም ከአንድ አገር መሪ የሚጠበቅ ተግባር ተደርጎ መገለጽ እንዳለበት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይኹን እንጂ እርሳቸው ግድቡ በተጀመረ በዓመቱ በማለፋቸው በወቅቱ የግንባታ ዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደነበር ተናግረዋል።
"ያም ቢሆን ግን ለማስጀመራቸው ከፍተኛ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቀጣይነት ከእርሳቸው ሥልጣኑን የተረከቡትን ኃይለማርያም ደሳለኝንም አመስግነዋል።
ከ14 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ ተጠቃሽ የሆነ ግዙፍ ግድብ መገንባት መጀመሯን በማብሰር በይፋ የመሠረት ድንጋዩን በማስቀመጥ ግንባታውን ያስጀመሩት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ።
ከእርሳቸው በመቀጠል አገሪቱን ማስተዳደር የጀመሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ቢሆኑ ግድቡን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ "እየተንገዳገደ የተወሰነ ቦታ እንዲደርስ ስላደረጉት ጥረት" ምስጋና እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።
በወቅቱ የፕሮጀክት አስተዳደር ውስንነት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም የኢትዮጵያ አጠቃላይ ፖለቲካ የነበረበት ሁኔታ ያሳደረው ተጽዕኖ መሆኑን አስረድተዋል።
በፊት የነበረው ሥራ አሁን ካለው አጨራረስ ጋር ሊወዳደር አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግድቡ ሳቢያ ግጭት እና ውጊያ የበዛው በማጠናቀቂያወ ሥራ ወቅት እንደነበር አብራርተዋል።
"በዚያ ዘመን ውሃ መያዝ ስላልነበር አጨቃጫቂው ዋና ጉዳይ ውሃ መያዝ ነው። አጨቃጫቂው ዋና ጉዳይ ግድቡን መጨረስ ነው። ገንዘብ አመንጭቶ ማሽኖቹን ማምጣት ነው" በማለት "ግጭት እና ውጊያ የበዛብን ከዚያ በኋላ ነው" ብለዋል።
"በርካታ ተፋላሚዎች ወጥተው ከአገር ሠልጥነው ያስቸገሩን ከዚያ በኋላ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈተና ረገድ ይወዳደራሉ ማለታቸው ሳይሆን ተገቢው ምስጋና ግን በተገቢው መንገድ ለሁሉም መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል።
ግንባታው ከተጀመረው በኋላ ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቶች ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ገብታ የቆየችው ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ሙሉ ወጪ የሸፈነችው ከሕዝብ ከተሰበሰበ ገንዘብ ነው።
በአምስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የሕዳሱ ግድብ 14 ዓመታት የፈጀ ሲሆን፣ ለግንባታውም አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማም ወጥቶበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በውይይታቸው ወቅት በግድቡ ዙሪያ የእኛም ዘመን ሆነ ከዚያ በፊት የነበረው ዘመን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሚና አይተካውም፤ ዋናው የጉዳዩ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ነገር ግን በየዘመኑ ጉዳዩን ወስነው የመሩ ሰዎች በልካቸው ሳይጋነንም፤ ሳያንስም ተገቢ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ እኛ ታሪክ የምንሻማ ሳንሆን ታሪክ የምንሠራ ትውልድ መሆናችንን ማሰብ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሕዳሴ ግድብ ላይ ለተፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ "ንጋት" የሚል ስያሜ መሰጠቱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን ባብራሩበት ንግግራቸው በግብፅ በአስዋን ግድብ ላይ የተፈጠረው ሐይቅ በወቅቱ በነበሩት መሪ ስም መሰየሙን አስታውሰው፤ ይህ የሕዳሴ ግድብ እና ሐይቅ ግን "ከአንድ ግለሰብ፣ ከአንድ ቡድን፣ ከአንድ ሰው ጋር የሚያያዝ" አለመሆኑን ጠቅሰው "ሐይቁ ንጋት፣ ግድቡ ደግሞ ሕዳሴ" መባሉን ጨምረው ገልፀዋል።
"አባይን [ግድቡን] ጨርሶ የታሪክ እጥፋትን ኢትዮጵያ ውስጥ ማረጋገጥ የመጨረሻ ፀሎቴ፣ የመጨረሻ ምኞቴ ነበር" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በዚህ ወቅት በሱዳን እና በግብፅ የሚገኙ ግድቦች "ከበቂ በላይ፣ ወይም ዘወትር ከሚያውቁት በላይ ውሃ አለ። አንድም ሊትር ውሃ አልቀነሰባቸውም" በማለት የአባይ ውሃ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት አለመቀነሱን ተናግረዋል።
"ወደፊትም እንዲቀንስ አንፈልግም። እነርሱ ተስፈኛ እና ደስተኛ መሆን አለባቸው። ስጋት እንዲፈጠርባቸው አንፈልግም" ሲሉ ወደ ታችኛው የአባይ ተፋሰስ አገራት የሚፈስሰው የውሃ መጠን ወደፊትም እንደማይቀንስ ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጅምሩ እንዲሁም የተካሄዱ አምስት ውሃ ሙሌቶችን በጽኑ ሲያወግዙ የነበሩት የግብፅ ፕሬዝዳንት አልሲሲ የአገራቸው ውሃ ድርሻ እንዲነካ ፈጽሞ እንደማይፈቅዱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደመጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰኞ ምሽት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ በተላለፈው ቃለ ምልልሳቸው ላይ "ይህ ግደብ በተሟላ መልኩ አልቆ ሥራ ከጀመረበት ከዛሬ ጀምሮ የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲክስ ኩስመና ታሪክ አበቃ ማለት ነው፤ የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲክስ ቁመና ተሻሻለ ማለት ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን "የተሰመረበት ሐቅ ነው" በማለት ሲያብራሩ ኢትዮጵያ እስካሁን ባለፈችበት ዘመን ሁሉ "ትልቁ ፈተና አባይ ነው። ሌላው የአባይ ውላጅ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
በተለያዩ አካባቢ የሚታዩ ግጭቶች፣ የሚሰሙ አለመግባባቶች "የአባይ ውላጅ" ሲሉ የጠሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ዋናው የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ እናት እና ባለቤት አባይ ነበረ" ሲሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን የችግሮች ሁሉ እናት የሆነውን ከፈታች ሌሎቹ ትንንሾች ምንም ናቸው ማለት ናቸው በማለት አባይ አሁን የሚሰጠውን አገልግሎት ላላፉት 1000 ዓመታት እንዲሰጥ ማድረግ አልቻልንም ብለዋል።
ቀይ ባሕር የዛሬ 30 ዓመት በኢትዮጵያ እጅ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የተፈጠረው ስህተት የትናንትና ነው። ነገ ይታረማል። ብዙ ከባድ አይደለም" በማለት ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ መገደብ የአባይ ውሃን ይቀንሰዋል በሚል የዲፕሎማሲ እሰጥ አገባ ውስጥ የገቡ አገራት በሚቀጥሉት ጊዜያት ውሃቸው አለመቀነሱን ሲያዩ ውጥረቱን ያረግበዋል ሲሉ ያላቸውን ተስፋም አስረድተዋል።
በሚቀጥሉት አምስት፣ አስር፣ አስራ አምስት ዓመታት እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንጀምራለን ሲሉ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "አባይ ትልቁ ከተፈታ ትንንሹ ይፈታል" በማለት ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች በቀጣይ ዓመታት እንደሚኖሩ አብራርተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በ13 ተርባይኖች ከ5000 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ተነግሯል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሐምሌ እና ነሐሴ ወር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር መጨመሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዘንድሮ ጋር ሲወዳደር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩንም አብራርተዋል።
"የእኔ ምኞት ከሚቀጥለው ሳምንት ወይም 15 ቀን በኋላ የሕዳሴ ግድብ ለመላ ኢትዮጵያውያን ለጉብኝት ክፍት ይደረጋል" በማለት በቦታው ለእንግዶች ማረፊያ የሚሆን ከ100 በላይ ቪላዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ይህ ኢትዮጵያን ለዘመናት ቀፍድዶ የያዘ ችግር እንዴት እንደተፈታ ማየት እና መማር ይኖርባቸዋል ሲሉም ለኢትዮጵያውያን ጎብኚዎች ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያን ሁለት የቀድሞ መሪዎች በስም ጠርተው ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአገሪቱ ውስጥ ላለፉት ሰባት አስርታት፣ ከቆቃ ግድብ ጀምሮ በግንባታ ላይ የተሰማራው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ባለቤቶችን እና ቤተሰቦችንም አመስግነዋል።
የሕዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ በግዝፈቱ ቀዳሚ መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአፍሪካም ትልቅ ከሆኑት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት "74 ትሪሊየን ሊትር ውሃ" መያዝ መቻሉን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያለው ሐይቅ "ንጋት" በሚል መሰየሙን ተናግረዋል።
ለመላው ኢትዮጵያዊያን ግድቡን እና ሐይቁን መጥተው እንዲጎበኙ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ከዚህ ግድብ በዓመት 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይጠበቃል" በማለት በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያፈሰስነውን ሀብት ይመልስልናል ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።