በኡጋንዳ በርካታ ተሽከርካሪዎች ተጋጭተው 46 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Joseph Muyingo
በኡጋንዳ በርካታ ተሽከርካሪዎች ተጋጭተው 46 ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ ገለጸ።
በተቃራኒ አቅጣጫ ይጓዙ የነበሩ አውቶብሶች ከፊትለፊታቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎችን ለመቅደም ሲሞክሩ ተጋጭተዋል።
በካምፓላ በሚገኘው ካምፓላ-ጉሉ አውራ ጎዳና በደረሰው አደጋ የሞቱ ሰዎች 63 ናቸው ተብሎ ነበር።
ሆኖም ፖሊስ ራሳቸውን የሳቱ ሰዎችን እንደሞቱ በማሰብ የተሳሳተ ቆጠራ አድርጓል ተብሏል። ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር 46 መሆኑም ተገልጿል።
ፖሊስ እንዳለው፤ አንደኛው አውቶብስ ከፊትለፊቱ ሲመጣ ከነበረው አውቶብስ ጋር ላለመላተም አቅጣጫውን ሲለውጥ ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ገጭቷል።
ከአውቶብሶቹ ቀድመውና ተከትለው ይጓዙ የነበሩ ተሽከርካሪዎችም እርስ በእርሳቸው ተጋጭተዋል።
በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ፖሊስ ክስተቱን እየመረመረ ይገኛል።
የተጎዱት ሰዎች በኡጋንዳ ምዕራባዊ ከተማ ኪራይዶንጎ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ተወስደዋል።
ፖሊስ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ከጤና እና ድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎች ጋር በመጣመር ትክክለኛ የተጎጂዎችን ቁጥር ለማወቅ እየሠራ ሲሆን፤ የአደጋው መንስዔም እየተጣራ ነው።
ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በትራፊክ አደጋው የተሰማቸውን ሐዘኔታ ገልጸው ለሟቾች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።
በአደጋው ለሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው አምስት ሚሊዮን ሽልንግ እንዲሁም በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች አንድ ሚሊዮን ሽልንግ እንደሚሰጥ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
አደጋው የደረሰበት አውራ ጎዳና ከሰሜናዊ ኡጋንዳ ወደ ደቡባዊው ክፍል የሚወስድ ሲሆን፤ አብዛኛውን ጊዜ የትራፊክ መጨናነቅ ይከሰታል።
ከአደጋው በኋላ ፖሊስ "በችላ ባይነት አደገኛ በሆነ ሁኔታ መኪኖችን ለመቅደም አትሞክሩ። በአገሪቱ አብዛኞቹ የትራፊክ አደጋዎች የሚደርሱት ለመቅደም በሚደረግ ሙከራ ነው" ሲል አሳስቧል።















