ወደ ዱባይ የሚሄዱ ሴቶችን "ለሚያዋርድ የወሲብ ንግድ" የሚያቀርበው ግለሰብ በፖሊስ ተያዘ

ቻርልስ ምዌሲግዋ
የምስሉ መግለጫ, ቻርልስ ምዌሲግዋ

ማስጠንቀቂያ፡ የሚረብሽ እና ዝርዝር የወሲብ ተግባራት አገላለጾችን ይዟል

ወደ ዱባይ የሚሄዱ ሴቶችን "ለሚያዋርድ የወሲብ ንግድ" እንደሚያቀርብ በቢቢሲ ምርመራ የተጋለጠው ግለሰብ በፖሊስ ተያዘ።

በዱባይ ቅንጡ መኖሪያ አካባቢዎች ሴቶችን ለወሲብ ንግድ ሲያቀርብ የነበረው ግለሰብ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፖሊስ መያዙ ተገልጿል።

ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ ቻርልስ ምዌሲግዋ ሴቶችን "በወሲብ ድግሶች ላይ እንደሚያቀርብ" ሲናገር ይደመጣል።

አቤይ በሚል ስም የሚታወቀው ይህ ግለሰብ ለቢቢሲ ምሥጢራዊ የምርመራ ጋዜጠኛ እንዳለው ሴቶችን ከ1,000 ዶላር ጀምሮ ያቀርባል። ደንበኞቹ የሚፈልጉትን "ማንኛውንም ነገር" እነዚህ ሴቶች እንደሚፈጽሙም ተናግሯል።

ቀድሞ በለንደን የአውቶብስ ሾፌር የነበረው ግለሰቡ ምን ዓይነት ክስ እንደሚቀርብበት እስካሁን በግልጽ አልታወቀም። ስለ ጉዳዩም በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።

ዱባይ በሚገኘው አል አዊር ከተማ ባለ ማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

በኢንተርፖል ኡጋንዳ አማካይነት ግለሰቡ የእስር ማዘዣ እንደወጣበት ተገልጿል።

ለሌላ አገር ተላልፈው የሚሰጡ ተጠርጣሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲፈለጉና በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የሚያደርገው ማዘዣ (red notice) እንደተላለፈት ታውቋል።

በአቡ ዳቢ ያለው የኡጋንዳ ኤምባሲ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ "ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ እያደረግን ያለው ምርመራ እንደቀጠለ ነው። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እርምጃ ወስደዋል" ብሏል።

ይህ መግለጫ የወጣው ቻርልስ ሙሲግዋን በተመለከተ መሆኑ ይታመናል።

ቢቢሲ በሠራው የምርመራ ዘገባ ላይ የወጣት ኡጋንዳውያን ምስክርነት ተካቷል። ወደ ዱባይ ያቀኑት የተሻለ ሥራ እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸው ቢሆንም የገንዘብ እዳቸውን ለመክፈል በወሲብ ንግድ ለመሰማራት መገደዳቸውን እማኝነት ሰጥተዋል።

በዱባይ በመደብር ወይም በሆቴል እንደሚሠሩ በማመን ነበር እነዚህ ሴቶች የተጓዙት። በዱባይ የወሲብ ንግድ በሕግ የተከለከለ ነው።

በግለሰቡ ብዝበዛ ከደረሰባቸው አንዷ ሞኒክ

የፎቶው ባለመብት, Family handout

የምስሉ መግለጫ, ግለሰቡ ከፈጠረው የወሲብ ንግድ ሰንሰለት ጋር በተያያዘ ሞኒክ ካሩንጊ ከሕንጻ ላይ ወድቃ መሞቷን ቢቢሲ በምርመራው ደርሶበታል።

ሁለቱ ሴቶች ራሳቸውን አጥፍተው ነው ቢባልም ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ግን ሞታቸውን በተመለከተ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ እንዳለበት ይገልጻሉ።

ቻርልስ ምዌሲግዋ ጉዳዩ የሚመለከተው የሴቶቹን ሞት የመረመረው የዱባይ ፖሊስ ነው ሲል ተናግሯል። ቢቢሲ ከዱባይ ፖሊስ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም።

የቢቢሲን ዘገባ ተከትሎ በኡጋንዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይቶች ተካሂዷል። የሕዝብ እንደራሴዎች ድርጊቱን "የሚረብሽ" ሲሉ ገልጸው፣ ፍትሕ እንዲሰፍን ከኢንተርፖል ጋር በጥምረት ለመሥራት ቃል ገብተዋል።