ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትንታኔ፡ ትራምፕ ጋዛን 'ይጠቀልሏታል'? ይህ ሃሳባቸው ምን ጦስ ይዞ ይመጣ ይሆን?
- ፀሐፊ, ጄሬሚ ቦዌን
- የሥራ ድርሻ, የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አርታዒ
ትራምፕ፣ ግሪንላንድን እና የፓናማ ቦይን "የእኛ እናደርጋለን" ሲሉ ብዙዎች ከቁም ነገር አልጻፏቸው ይሆናል።
አሁን ደግሞ ስለ ጋዛ የሰጡት አስተያየት ምናልባት አጠገባቸው ቆመው የነበሩትን ቤኒያሚኒ ኔታንያሆን ጭምር ፈገግ አሰኝቷል፤ ፈገግታቸው የደስታ ይሁን ግራ የመጋባት ባይታወቅም።
አረብ አገራት ውሳኔው "በመቃብራችን ላይ'' ካልሆነ አይፈጸምም ብለዋል። ይህ ተቃውሞ የአሜሪካ ጥበቅ አጋር የተባሉት ዮርዳኖስ እና ግብፅን ይጨምራል።
ለመሆኑ የትራምፕ 'ጋዛን እንጨብጣታለን' ህልም መሬት ላይ ይወርዳል? የቢቢሲው የዓለም አቀፍ ፖለቲካ አርታኢ ጄሬሚ ባዌን ነገሩን 'የቀን ቅዠት' ብሎታል።
ሐሳቡን የአሜሪካ አጋር የሚባሉት ዩናይትድ ኪንግደም አና የአውሮፓ አገራትም አልወደዱትም።
እርግጥ ነው የተወሰኑ ፍልስጤማውያን ዕድሉን ቢያገኙ ከጋዛ የመውጣቱን ነገር ሊያደርጉት ይችላል።
ብዙ መቶ ሺዎች በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከጋዛ ለመውጣት ይፈቅዳሉ ቢባል እንኳ 1.2 ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች ከመሬታቸው ፈቀቅ ለማለት ይፈቅዳሉ ተብሎ አይታመንም።
ትራምፕ "የመካከለኛው ምሥራቅ አፀደ ገነት'' አደርጋታለሁ የሚሏት ጋዛ ነዋሪዎቿ "ወደየትም ንቅንቅ አንልም" ካሉ የግድ ጉልበት መጠቀም ሊኖርባቸው ነው።
ጉልበት ለመጠቀም ደግሞ ወታደር መላክ ያሻቸዋል።
ይህ ደግሞ ትራምፕ ለመራጮቻቸው ከገቡት ቃል የሚያፈነግጥ ነው።
አሜሪካውያን ወታደሮቻቸው ወደ ሌሎች አገራት እንዲሰማሩ አይወዱም፤ አይፈቅዱም።
ጣጣውን በኢራቅ እና በአፍጋኒሰታን አይተውታል።
መካከኛው ምሥራቅን በተመለከተ አሜሪካ ከ90ዎቹ ጀምሮ 'የሁለት ሕዝቦች ነጻ አገር" ዕቅድ ደጋፊ ነበረች። በመካከለኛው ምሥራቅ የውጭ ፖሊሲዋ የተመራውም በዚህ የእስራኤል እና የፍልስጤም 'የሁለት ነጻ አገር' ፖለቲካዊ መፍትሄ ነበር።
እስራኤል ይህን ሐሳብ አሁን ገሸሽ አድርጋዋለች።
"የሁለት ነጻ አገር ዕቅድ" ሐሳብ አሁን- አሁን ባዶ መፈክር ሆኗል።
በዚህ ወቅት ነው ትራምፕ "ጋዛን እንጠቀልላታለን" እያሉ ያሉት።
ትራምፕ በሐሳባቸው ከገፉበት ዓለም አቀፍ ሕግን መጣስ ይሆንባቸዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን፣ ቻይና ታይዋንን መጠቅለል መሻታቸውንም ልክ ያደርገዋል። የጋዛ ሐሳብ ልክ የማይሆነውም ለዚያ ነው።
ምን ጦስ ይዞ ይመጣል?
''የትራምፕ 'የአፍ ወለምታ' መሬት ላይ የማይተገበር ከሆነ ለምን ያሳስበና?'" ብሎ ይንደረደራል የቢቢሲው የፖለቲካ ተንታኝ።
ትራምፕ ባሉት መንገድ ነገሩ ሊፈጸም አይችልም። ነገር ግን የራሱን ጦስ ያስከትላል ብሎ ያምናል ጄሬሚ ቦዌን።
አንደኛ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ናቸው።
በዓለም ላይ እጅግ ኃያሉ ሰው እርሳቸው ናቸው።
መርሳት የሌለብን ትራምፕ የቀድሞው የቴሌቪዥን መርሐ ግብር አሰናጁ ትራምፕ አይደሉም።
ሥልጣናቸው የትየለሌ ነው። ክንደ ብርቱ ናቸው።
ከአንደበታቸው የሚወጣ ቃል ፖለቲካን ሊገድልም ሊያሽርም ይችላል። ተጽእኗቸው ወደር የለውም።
ጋዛን በተመለከተ የሰነዘሩት አስተያየታቸው ብቻውን በቋፍ ላይ የሚገኘውን የተኩስ አቁም ስምምነት ከናካቴው ሊያፈርሰው ይችላል።
የሰላም ስምምነቱ አንዱ ፈተና የጋዛ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በግልጽ አለመቀመጡ ነው።
አሁን ትራምፕ አንድ አማራጭ አቅርበዋል።
ምንም እንኳ ያሉት ነገር መሬት ላይ የማይወርድ ነው ብንልም በፍልስጤማውያን ዘንድ ጠባሳን፣ በአክራሪ እስራኤላውያን ዘንድ ደግሞ ሐሴትን አኑሮ ያልፋል።
ለምሳሌ በአክራሪ አይሁዶች ዘንድ ''ምኞታችን ተሳካ'' እንዲሉ ያስችላቸዋል። ከዚህ ወዲያ ፍልስጤማውያን ላይ የሚወስዱት የማፈናቀል እርምጃ ''ትክክል" ሆኖ እንዲሰማቸው የልብ ልብ ይሰጣቸዋል።
ዌስት ባንክ ላይ ይህ በቅርብ ጊዜ ሊታይ ይችላል።
ጽንፈኛ አይሁዶች በሜዲትራኒያን እና በዮርዳኖስ ወንዝ መሀል ያለው መሬት በሙሉ ከአምላክ ለእስራኤል የተሰጠ ፀጋ ተደርጎ ይታመናል።
ስለዚህ በዚያ ያለ ነዋሪ ሁሉ ተጠራርጎ መሸኘት አለበት፤ ወደየትም ይሁን ወዴት።
የእነዚህ ጽንፈኞች ተወካዮች ከኔታንያሁ ፓርቲ ጋር በጥምረት መንግሥት መሥርተዋል።
በትራምፕ ንግግር ደግሞ ፈንጥዘዋል።
የጋዛ ጦርነት እንዲቀጥል ይሻሉ። ቀስ በቀስ ፍልስጤማውያን ተሸኝተው በአካባቢው አይሁዶች ብቻ እንዲኖሩበት ይፈልጋሉ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ቤዛለል ስሞትሪች ዶናልድ ትራምፕ የጋዛን ትክክለኛ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አሁን ገና አፈረጡት ዓይነት አስተያየት ሰጥተዋል።
"እኛን የነካ ሁሉ ይቀበራል፤ ከመሬቱም ከርስቱም ይነቀላል። አሁን በፈጣሪ እርዳታ 'የፍልስጤም አገር' የሚባለውን ቅዠት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የምንቀብርበት ጊዜ ላይ ነን" ብለዋል።
ሐማስን የመሰሉ ኃይሎች ደግሞ ጋዛን በተመለከተ ትራምፕ በይፋ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ ጉልበታቸውን ለማሳየት አጋጣሚ ሊጠብቁ ይችላሉ።
ለተራ ፍልስጤማውያን ደግሞ ሌላ አስፈሪ እና አስጨናቂ ነገን አመላክቷቸዋል። ሌላ ምስቅልቅል፤ ሌላ ጥፋት፣ ሌላ "አል-ናቅባ'' [መፈናቀል እና ስቃይ]።
የእስራኤል እንደ አገር መመሥረትን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 1948 'አል-ናቅባ'፣ 700 ሺህ ፍልስጤማውያን ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ አልተመለሱም።
ትራምፕ ምን ያተርፋሉ?
የቢቢሲው ተንታኝ ጄሬሚ ቦዌን እንደሚለው ዶናልድ ትራምፕ ከሪልስቴት ቢዝነስ የመጡ ሰው ናቸው።
ሐሳባቸውን ሲናገሩ እንደመጣላቸው ነው። ወይም ደግሞ ያሉትን ይተገበራል ማለት አይደለም።
የድርድር መነሻ አድርገው ነው የሚጠቀሙበት።
ልክ ለትንሽ ነገር ትልቅ ዋጋ እንደሚጠራ ነጋዴ።
ምናልባት ትራምፕ ይህን ድንጋጤ ፈጥረው ከጀርባ ሌላ ዕቅድ እያበሰሉ ነው የሚሆነው።
ዶናልድ ትራምፕ የኖቤል ሽልማትን የሚናፍቁ ሰው መሆናቸውን ሳንዘነጋ።
በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማምጣት የሚሞክሩ ፖለቲከኞች፣ ባይሳካላቸው እንኳ የኖቤል ሽልማትን የማግኘት ዕድላቸው የሰፋ ነው።
ትራምፕ ይህ ሽልማት እንደሚገባቸው የሚያምኑ ሰው ናቸው።
ትራምፕ ይህን ቦምብ የሆነ ሐሳብ ከዋይት ሐውስ ካፈነዱት በኋላ የራሳቸው ወደሆነው 'ትሩዝ ሶሻል' የማኅበራዊ መድረክ ላይ ወጥተው የጻፉት ነገር ይህን ያሳብቃል።
ከኢራን ጋር አስተማማኝ የኑክሊየር ስምምነት ማድረግ እፈልጋለሁ ብለዋል።
ኢራን ኑክሊየር መታጠቅ አልሻም ብትልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካደረባት ስጋት የተነሳ ምኞቱ ውልብ አላለባትም አይባልም።
ኔታንያሁ ደግሞ ትልቁ ሕልማቸው በአሜሪካ እርዳታ የኢራንን የኑክሊየር ህልም ድራሹን ማጥፋት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በፍጹም ከኢራን ጋር ስምምነት እንዲደረስ አይሹም።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በኔታንያሁ ግፊት ባራክ ኦባማ ከፈረሙት የኢራን ስምምነት እንዲወጡ ሆነዋል።
ትራምፕ አገራቸው ጋዛን ተቆጣጥራ መልሳ እንደምትገናባት እና ፍልስጤማውያንንን ወደ ሌላ አገር የማስፈር ንግግር፣ ምናልባት አስፈራርቶ የሰላም ስምምነት ለመፈራረምም ያለመ ሊሆን ይችላል።
ሆኖም ግን አክራሪ አይሁዳውያንን የሚያስቦርቅ ነገር ፈልገው የተናገሩት ከሆነ ተሳክቶላቸዋል።
ፈልገውም ሆነ ሳይፈልጉት ግን በመካከለኛው ምሥራቅ አስፈሪ ድባብ ፈጥረዋል።
የትራምፕ ንግግር መሬት ላይ የሚወርድ ባይሆንም ከአንደበታቸው የወጣው ቃል ጦሱ ለዓመታት የሚዘልቅ ሊሆን ይችላል።