አሜሪካ ምንነቱ ያልታወቀ በራሪ አካልን በግዛቷ ውስጥ መትታ መጣሏን አስታወቀች

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአገሪቱ ግዛት በሆነው የአላስካ ሰማይ ላይ የታየ አንድ በራሪ አካል ተመትቶ እንዲጣል ባዘዙት መሠረት ይኸው ተፈጻሚ መሆኑ ተነገረ።

ዋይት ሐውስ እንዳለው ይህ በረራ ግኡዙ አካል የተመታው በተዋጊ ጄት ነው።

የፕሬዝዳንቱ አቀባይ ጆን ኪርቢ እንዳሉት ይህ ግኡዝ አካል መጠኑ አንድ የቤት መኪናን ያክላል።

ተመትቶ እንዲጣል የተደረገው ደግሞ በዋናነት ለአየር በረራ ስጋት ሊሆን እንደሚችል በመታመኑ ነው።

ይህ ግኡዝ ነገር ማን እንደላከው፤ በዚያ ከፍታ የተገኘበት ዓላማ ምን እንደሆነ ለጊዜው አልታወቀም። ሆኖም አሜሪካ ከሳምንት በፊት ቻይና የላከችውን የስለላ ፊኛ መትታ ከጣለች በኋላ ተመሳሳይ የደኅንነት ስጋት ሳያድርባት አልቀረም።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት አሁን ተመትቶ የወደቀው ምንነቱ ያልታወቀ ነገር በመጠኑ ሲነጻጸር ቻይና ባለፈው ሳምንት ወደ አሜሪካ ሰማይ ከላከችው የመረጃ ቃራሚ ፊኛ በእጅጉ ያነሰ ነው።

የቻይናው የስለላ ፊኛ በመጠኑ ከሦስት የከተማ አውቶቡስ ይልቃል። ይህ ግኡዝ አካል ግን አነስተኛ የቤት መኪና ቢያህል ነው።

የቻይናው መረጃ ቃራሚ ፊኛ በሳውዝ ካሮላይና ግዛት የውሃ አካል ላይ ተመትቶ ከተጣለ በኋላ ስብርባሪውን ፍለጋ ባሕር ኃይል መሠማራቱ ይታወሳል።

ይህ አርብ ዕለት የተመታው ምንነቱ ያልታወቀው ግኡዝ አካል በአላስካ ግዛት ሰማይ ላይ በ40 ሺህ ጫማ ከፍታ ሲንሳፈፍ የነበረ ነው።

ይህም ወደ 12ሺህ ሜትር ወይም 12 ኪሎ ሜትር ከፍታ መሆኑ ነው።

ብዙውን ጊዜ የመንገደኛ አውሮፕላኖች እስከ 45ሺህ ጫማ ከፍታ ደረስ ወጥተው መብረር ይችላሉ።

ግኡዝ አካሉ በሰዓት እስከ ከ20 እስከ 40 ሜትር ይጓዝ ነበር ተብሏል።

አሁን በተዋጊ ጄት ተመትቶ ከወደቀ በኋላ ስብርባሪውን በቢፎርት ባሕር አቅራቢያ ለመልቀም በሄሊኮፕተሮች ጭምር የታገዘ አሰሳ ተጀምሯል።

ቢፎርት ባሕር በዚህ ወቅት በቅዝቃዜ በረዶ ሰራ ግግር ባሕር በመሆኑ ስብርባሪውን ለማግኘት አስቸጋሪ እንደማይሆን ይጠበቃል።

ቃል አቀባዩ እንደሚሉት አሁን ይህ ግኡዝ ነገር ለጊዜው ማን እንደላከው፣ የማን ንብረት እንደነበረ፣ በባለቤትነት የሚቆጣጠረው ግለሰብ ይሁን መንግሥት የሚታወቅ ነገር የለም።

ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ደግሞ ባለፈው ሐሙስ ሌሊት ነው ተብሏል።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባዩ በራሪው ግኡዙ ነገር የተመታበትን ሁኔታ ሲያብራሩ፣ መጀመሪያ ሁለት ተዋጊ ጄቶች ከተጠጉት በኋላ ውስጡ ሰው እንደሌለ አረጋግጠው ሲያበቁ መረጃው ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከተገለጸላቸው በኋላ እርሳቸው እንዲመታ በማዘዛቸው ይኸው ተፈጻሚ ሆኗል ብለዋል።

ቻይና የስለላ ፊኛ ልካብኛለች በሚል ዋሺንግተን ከቤይጂንግ ጋር የዲፕሎማሲ ቅራኔ ውስጥ ገብታ ነበር።

ለዚህም ይመስላል ባለፈው እሑድ ቤይጂንግን ይጎበኛሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ሐሳባቸውን የቀየሩት።

ጆ ባይደን በቻይና ላይ የተለሳለሰ አቋም እየወሰዱ ነው በሚል በሪፐብሊካኖች ይተቻሉ።

ሪፐብሊካኖች እንደሚሉት ከሆነ ቻይና ከአሜሪካ ሰማይ ላይ ሆና በርካታ ወታደራዊ መረጃዎችን እየወሰደች ሳይሆን አይቀርም።

አሜሪካ ግን ተመጣጣኝ ምላሽ እየሰጠች አይደለም ሲሉ ይከሳሉ።

ቻይና በበኩሏ የአየር ንብረት መረጃ ለመቃረም የላኩት ፊኛ ነው አሜሪካ የአየር ክልል ሳልፈልግ ነው የሄደብኝ ስትል ማስተባበያ ሰጥታለች።

ከዚህ የፊኛ ውዝግብ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሎይድ ኦስቲን የቻይናው አቻቸው ጋር አደገኛ የደኅንነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብቻ በሚደዋወሉበት የስልክ መስመር ደውለላቸው ነበር።

ይሁንና የቻይናው አቻቸው ዌ ፈንጌ ስልኩን አላነሱላቸውም።