በሦስት የትግራይ ከተሞች የባንክ አገልግሎት መጀመሩ ተገለጸ

በትግራይ ክልል የሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ
የምስሉ መግለጫ, በትግራይ ክልል የሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሦስት የትግራይ ክልል ከተሞች ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረውን የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።

ባንኩ ሥራውን የጀመረው በፌደራሉ መንግሥት ቁጥጥር ስር በሚገኙት ሽረ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞች ነው።

የባንክ አገልግሎት ከተቋረጠ ከዓመት በላይ በሆነባቸው በእነዚህ ከተሞች የሚገኙ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች እንደገና አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም ያስታወቀው ታኅሣሥ 10/2015 ዓ.ም. ዕለት ባወጣው መግለጫ ነው።

በነዚህ ከተሞች የሚሰጠው አገልግሎት ከውጭ ሃገር እና ከሃገር ውስጥ የሚላኩ ገንዘቦችን የመቀበል እንዲሁም የማስቀመጥ መሆኑንም ባንኩ በመግለጫው ጠቅሷል።

ለሁለት ዓመት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የባንክ አገልግሎት ጨምሮ መሠረታዊ የሚባሉት የኤሌክትሪክ፣የ ስልክ እና ሌሎች አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል።

የፕሪቶሪያውንም የሰላም ስምምነት ተከትሎ አንዳንድ አገልግሎቶች እንደገና እየተመለሱ ይገኛሉ። አንበሳ የተሰኘው የግል ባንክም በሽረ ከተማ ሥራ መጀመሩን እንዲሁ አስታውቋል።

በቅርቡ የትግራይ ርዕሰ መዲና መቀለ ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል [ግሪድ] ጋር በመገናኘቷ ለረዥም ጊዜያት በጨለማ ተውጣ የነበረችው ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አግኝታለች።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን አስከፊ ጦርነት ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ የምግብ ዕጦት የተዳረጉ ሲሆን፣ በፌደራሉ መንግሥትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለሕዝቡ ሰቆቃ ፋታ ሊሰጠው ይችላል የሚል ተስፋን ሰንቋል።

ሆኖም ስምምነቱ ከተፈረመ ከስድስት ሳምንታት በላይ ቢሆነውም የኤርትራ ወታደሮች እና የፌደራሉ መንግሥት አጋር የሆኑት የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል የመውጣት አዝማሚያ ባለማሳየታቸው ስጋት እንደጫሩ ነው። እንዲሁም የትግራይ ኃይሎችም ትጥቅ አልፈቱም።

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እና በናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሣሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ተጠቅሷል።

የህወሓት ሊቀመንበር እና የክልሉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ድብረጽዮን ገብረሚካኤል ወታደሮቻቸው በአራት የጦር ግንባሮች ከነበሩባቸው አካባቢዎች ለቀው መውጣታቸውን ገልጸው፣ የፌደራል መንግሥቱ ከስምምነቱ የተወሰኑትን ተግባራዊ ለማድረግ አልቻለም ሲሉ ከሰዋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ መንግሥት በትጋት ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረገ ነው ብሏል።