እስራኤል እና ሐማስ የጋዛን ጦርነት ለማቆም ከስምምነት ደረሱ

ለአስራ አምስት ወራት የተካሄደውን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተዋል።

በኳታር እና በአሜሪካ አሸማጋይነት በተደረሰው ስምምነት መሠረት በሐማስ የታገቱ እስራኤላውያን የሚለቀቁ ሲሆን እስራኤልም ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼኽ መሐመድ ቢን አብዱል ራሕማን አል ታሕኒ እንዳሉት ስምምነቱ በእስራኤል ካቢኔ ከፀደቀ የፊታችን እሑድ ይተገበራል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስምምነቱ "በጋዛ ግጭት ያስቆማል፣ የሰብአዊ እርዳታ ለንጹሃን ፍልስጤማውያን ዜጎች ያደርሳል፣ ታጋቾችን አስለቅቆ ከቤተሰባቸው እንዲቀላቀሉ ያስችላል" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የስምምነቱ የመጨረሻ ዝርዝሮች አሁንም እየታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ባይደን ስምምነቱን ወደፊት በማምጣታቸው ኔታንያሁ አመስግነዋል።

የሐማስ መሪ ካሕሊል አል-ሐያ ስምምነቱ የፍልስጤም አይበገሬነት ውጤት ነው ብለዋል።

ፍልስጤማውያን እና የታጋቾች ቤተሰቦች በዜናው ተደስተዋል።

ሐማስ እንዳለው በኳታር የስምምነቱ መገባደድ ከተገለጸ በኋላ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። 12ቱ በጋዛ በሼኽ ራድዋን ሰፈር የሚኖሩ ናቸው።

የእስራኤል ጦር ስለ ጉዳዩ ምላሽ አልሰጠም።

እስካሁን እስራኤል በጋዛ ውስጥ ባካሄደችው ጦርነት ከ46,700 በላይ ሰዎች መገደላቸው ሪፖርት ተደርጓል። ከጋዛ 2.3 ሚሊዮን ነዋሪዎች መካከል አብዛኞቹም ተፈናቅለዋል።

በእስራኤል መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በጋዛ ከፍተኛ ውድመት ከመድረሱ ባሻገር የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የነዳጅ አና የመጠለያ እጥረት ተከስቷል።

እስራኤል 94 ታጋቾች በሐማስ ቁጥጥር ሥር እንዳሉ የምትገልጽ ሲሆን፣ ከመካከላቸው 34ቱ ሞተዋል ተብሎ ይታመናል።

ከጦርነቱ በፊት ከታገቱ አራት ሰዎች ሁለቱ ሞተዋል።

የካታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሁለቱም ወገኖች "ሰከን እንዲሉ" አሳስበዋል።

ስድስት ደረጃ ባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ሴቶች፣ ሕጻናት እና አዛውንቶችን ጨምሮ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ።

እስራኤል በምላሹ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች።

የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ሰዎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።

በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገቡ ይፈቀዳል።

በሁለተኛው የስምምነቱ ዙር ተጨማሪ ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን፣ ይህም የመጀመሪያው ዙር ስምምነት የሚተገበረው 16 ቀን ሲሞላው ነው።

ሦስተኛ እና የመጨረሻው ደረጃ ጋዛን መልሶ መገንባት ሲሆን፣ ይህም ዓመታት ይወስዳል።

በዚህ ምዕራፍ የታጋቾች አስክሬንም ይመለሳል።

ሼኸ መሐመድ እንዳሉት ሁለተኛ እና ሦስተኛውን ምዕራፍ ለመደራደር ግልጽ አሠራር ተቀምጧል።

ዝርዝር መረጃው በቀጣይ ቀናት ይፋ ይሆናል።

ኳታር፣ አሜሪካ እና ግብፅ ስምምነቱ እንዲደረስ አግዘዋል። እስራኤል እና ሐማስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚከታተሉም ይሆናል።

"ይህ የጦርነቱ ማብቂያ ነው ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ሁሉም ወገኖች ስምምነቱን ያከብራሉ ብለን እናምናለን" ብለዋል ሦስቱ አገራት።

ባይደን እንዳሉት ከስምንት ወራት በፊት የታቀደው ስምምነት "ሐማስ ካለበት ከፍተኛ ጫና እና በሊባኖስ ያለው የተኩስ አቁም ኢራንን በማዳከም የቀጠናውን አሰላለፍ ከመለወጡ አንጻር" እውን የሆነ ነው።

"ጥሩ ዜና ቢሆንም ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸውን ሰዎችም አንረሳም። በጦርነቱ የሞቱ ንጹሃንንም አንዘነጋም። ጦርነቱ ከዚህ ቀድሞም መቆም ነበረበት" ብለዋል ባይደን።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ለስምምነቱ ሚና እንደነበራቸው ባይደን ጠቁመዋል።

በሁለቱም ወገኖች ላይ ጫና በማሳደር ስምምነቱ እንዲፈረም ትራምፕ ማስቻላቸው ተገልጿል።

ስምምነቱ መደረጉን ከኳታር እና ጆ ባይደን ጽህፈት ቤት ቀድመው ይፋ ካደረጉት መካከል ትራምፕ አንዱ ናቸው። ስምምነቱን "ታላቅ" ሲሉም ገልጸዋል።

"በኅዳር ምርጫ አስደናቂ ድል በማግኘታችን የመጣ ስምምነት ነው" ብለዋል ትራምፕ።

ኔታንያሁም ትራምፕ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ባደረጉት ጫና አመስግነዋቸዋል።

የኔታንያሁ ጽህፈት ቤት በይፋ መግለጫ የሚሰጠው ስምምነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።

የመጨረሻው የስምምነቱ ደረጃ አሁንም በሂደት ላይ እንዳለ እስራኤል አስታውቃለች።

የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ "ስምምነቱ በጣም የሚያሙ ወቅቶችን ያስታውሳል። ፈታኝም ይሆናል። ግን ትክክለኛው ውሳኔ ነው" ብለዋል።

የኔታንያሁ ቀኝ ዘመም የፓርቲ አባላት ስምምነቱን ቢነቅፉም፣ ዛሬ ካቢኔው ያፀድቀዋል ተብሎ ይታመናል።

'በስተመጨረሻ ሳልሰጋ ልተኛ ነው'

በስምምነቱ መሠረት፣ የሚለቀቁ ፍልስጤማውያን እስረኞች ስም ዝርዝር ይፋ ይሆናል። አንዳንዶቹ የታሰሩት በግድያ እና በሽብር ተከሰው ነው። ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች ይግባኝ ለማለት 48 ሰዓት ይሰጣቸዋል።

የሐማስ ዋነኛ ተደራዳሪ እና የጋዛ አስተዳዳሪ ካሕሊል አል-ሐያ ስምምነቱ "ከጠላት ጋር የምናደርገው ውጊያ ዋነኛ ክፍል ነው። በምላሹ ሕዝባችንን ነጻ የማውጣት ግብ አለን" ብለዋል።

በጋዛ ፍልስጤማውያን የደረሰባቸውን ስቃይ ግን "አንረሳም፣ ይቅርም አንልም" ሲሉ አክለዋል።

በጋዛ ዴር አል-ባላህ እና በኻሀን ዩኒስ ከተሞች ነዋሪዎች ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

የ17 ዓመቷ የሰሜን ጋዛ ነዋሪ ሳናባል "ሁላችንም ደስ ብሎናል። ለረዥም ጊዜ ስንጠብቀው ነበር። በስተመጨረሻ ሳልሰጋ ልተኛ ነው። አሁን ማገገሚያ ጊዜ ነው" ብላለች።

የእስራኤል ወታደሮች ታጋቾችን ለማስለቀቅ በፈጸሙት ጥቃት ከተገደሉ ከ70 በላይ ሰዎች መካከል አንዱ ባለቤቷ የሆነው ናዋራ አል-ናጃር "ከተኩስ አቁሙ በኋላ ለልጆቼ ጥሩ ሕይወት መስጠት እፈልጋለሁ። ስንኖረው ከነበረበት ፍርሃት እንዲወጡ እፈልጋለሁ" ብላለች።

የ84 ዓመት አባቷ የታገተባት ሻሮን ሊፍቺትዝ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ደስተኛ እንዳደረጋት ተናግራለች።

"አባቴ የመትረፍ ዕድሉ ጠባብ ነው። እናቴ አብራው ታግታ የነበረ ቢሆንም ተለቃለች። አባቴ በተዓምር ከተረፈ እኔ እና እናቴ እንንከባከበዋለን" ብላለች።

ቤተሰቡ የታገተበት ሞሼ ላቪ "ቤተሰቦቻችን እንዲመለሱ እንፈልጋለን። ግን ስምምነቱ ብዙ ምዕራፎች እንዳሉት እና አሁን የተስማሙት በመጀመሪያው ምዕራፍ መሆኑን መዘንጋት የለብንም" ብሏል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "አሁን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ግጭቱ የፈጠረውን የከፋ ስቃይ ማቆም ነው" ብለዋል።