በሱዳን በመዋዕለ ሕጻናት ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት 33 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በሱዳን፣ ደቡብ ኮርዶፋን ግዛት በምትገኘው ካሎጊ ከተማ በመዋዕለ ሕጻናት ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት 33 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ጥቃቱን መፈጸሙን የሱዳን ሐኪሞች ማኅበር እና የሱዳን ጦር ገልጸዋል። አርኤስኤፍ እስካሁን ስለ ጥቃቱ ምንም አላለም።
ያሳለፍነው ሳምንት አርብ በዳርፉር ግዛት በሚገኝ ገበያ ላይ የሱዳን ጦር የድሮን ጥቃት ፈጽሟል ሲል አርኤስኤፍ ከስሷል።
በገበያው አቅራቢያ ማለትም በአድሬ የቻድ ድንበር ላይ የነዳጅ ማከማቻ ይገኛል።
ስለ ሁለቱ ጥቃቶች የወጡ ሪፖርቶችን በገለልተኛ ወገን ማጣራት አልተቻለም።
ላለፉት ሁለት ዓመታት በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የቀጠለው ጦርነት አገሪቱን ለከፋ ቀውስ ዳርጓታል።
ለሱዳን ጦር ቅርበት ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው፤ መዋዕለ ሕጻናቱ በድሮን እና በሚሳዔል ሁለት ጊዜ ጥቃት ተፈጽሞበታል።
እርዳታ ለመስጠት ወደ መዋዕለ ሕጻናቱ ያቀኑ የሕክምና ባለሙያዎች እና ንጹኃን ዜጎች ላይም ጥቃት በድረሱን አስታውቋል።
የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ሸልደን ዩት "ሕጻናት በትምህርት ቤት ሳሉ መግደል ከፍተኛ የልጆች መብት ጥሰት ነው። ሕጻናት በግጭት ወቅት ዒላማ መደረግ የለባቸውም" ሲሉ ጥቃቱን አውግዘዋል።
"ሁሉም ወገኖች ይሄን መሰል ጥቃት እንዲያቆሙ ዩኒሴፍ ያሳስባል። ሰብአዊ እርዳታ ባልተገደበ እና ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲገባም መፈቀድ አለበት" በማለት አክለዋል።
አርኤስኤፍ እንዳለው የሱዳን ጦር በአድሬ የድንበር መተላለፊያ ላይ ጥቃት የፈጸመው አካባቢው "የሰብአዊ እርዳታ እና የሸቀጥ መተላለፊያ" ስለሆነ ነው።
የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት እየሰነደ የሚገኘው 'ሱዳን ዋር ሞኒተር' እንደገለጸው፤ በዚህ ጥቃት ሳቢያ ንጹኃን ከመጎዳታቸው በተጨማሪ ገበያ ላይም ውድመት ደርሷል።
በዳርፉር ስለተፈጸመው ጥቃት የሱዳን ጦር እስካሁን ድረስ ምንም አላለም።
የሱዳን መዲና ካርቱም እና ዳርፉር የሚገኙበት ሰሜን ኮርዶፋን፣ ደቡብ ኮርዶፋን እና ምዕራብ ኮርዶፋን ዋነኛ የጦርነት አውድማ ሆነዋል።
በአጠቃላይ በኮርዶፋን ግዛቶች ስምንት ሚሊዮን ሰዎች ይኖራሉ።















