ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል ዛሬ አርብ ከኢራን ሊቃጣባት ለሚችል ጥቃት በተጠንቀቅ ላይ መሆኗ ተገለጸ
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ዛሬ አርብ መጋቢት 27/2016 ዓ.ም. ከኢራን በኩል ሊቃጣበት የሚችለውን ጥቃት ለመመከት በጠንቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ።
የእስራኤል ባለሥልጣናት ኢራን በመጨረሻው የረመዳን ሳምንት አርብ በሆነው ቁድስ (የኢየሩሳሌም ቀን) ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል ያምናሉ።
እስራኤል ከጥቂት ቀናት በፊት በሶሪያ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ጽህፈት ቤት ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማ ከፍተኛ ጄኔራልን ጨምሮ 13 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት ቆይታለች።
የእስራኤል መከላከያ ኃይሉ ሊቃጣ የሚችል የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃትን ለማክሸፍ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የአቅጣጫ መጠቆሚያ ሥርዓት (ጂፒኤስ) እንዲቋረጥ እያደረገ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የእስራኤል መከላከያ ኃይል ለሠራዊት አባላት የእረፍት ጊዜ እንደማይፈቅድ ያስታቀ ሲሆን፣ አየር ኃይሉም ተጠባባቂ አባላቱን ለግዳጅ ጠርቷል።
በረመዳን የመጨረሻው አርብ በተለይ በኢራን ፀረ እስራኤል የሆኑ እና ፍልስጤማውያንን የሚደግፍ ሰልፍ ማዘጋጀት የተለመደ ነው።
ከትናንት ሐሙስ መጋቢት 26/2016 ዓ.ም. ጀምሮ በመካከለኛው የእስራኤል ግዛት ውስጥ ጦር መሳሪያዎች ዒላማቸውን ለመምታት የሚጠቀሙበት የጂፒኤስ አገልግሎት እንዲቋረጥ ተደርጓል።
በዚህም ምክንያት እንደ ቴል አቪቭ ባሉ ከተሞች የሚገኙ በርካታ እስራኤላውያን መገኛ ቦታን በመጠቀም የሚሠሩ መተግበሪያዎችን መጠቀም አለመቻላቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
የአገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ አገሪቱ ጂፒኤስ መዝጋቷን አረጋግጠዋል።
ዜጎችም መገኛቸውን በስልካቸው እራሳቸው እንዲሞሉ የታዘዙ ሲሆን፣ ይህም በአካባቢያቸው የሮኬት ጥቃት የሚኖር ከሆነ ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ይደርሳቸዋል ተብሏል።
አንዳንድ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ የሚገኙ ኤምባሲዎች ከኢራን ሊፈጸም ስለሚችለው ጥቃት ቀድሞ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ዘግበዋል።
በዚህ መካከል የጦርነት ስጋት የገባቸው እስራኤላውያን ጥሬ ገንዘብ ከገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤቲኤም) እያወጡ እና ምግብ እየገዙ እያከማቹ መሆኑ ተገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ግን ሕዝቡ እንዲረጋጋ ማሳሰቢያ አውጥቷል። መከላከያው በኤክስ ገጹ “ጄኔሬተር መግዛት እና ምግብ የምታከማቹበት ወይም ገንዘብ ከኤቲኤም ማሽኖች የምታወጡት ምንም ምክንያት የለም” ብሏል።
“እስከዛሬ እንዳደረግነው ሁሉ ማንኛውም ለውጥ ሲኖር ሥርዓት ባለው መንገድ በይፋ እናሳውቃለን” ብሏል።