ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአንጎላ “የሰላም መሃንዲስ” በ79 ዓመታቸው አረፉ
በማዕድን የበለጸገችውን አንጎላን ለአራት አስርት ዓመታት ያህል የገዙት ሁለተኛው የአንጎላ ፕሬዝዳንት ሆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።
ዶሳንቶስ ስፔን ውስጥ የልብ ህመም በሽታ ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ሕይወታቸው አልፏል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶስ ሳንቶስ በአውሮፓውያኑ 2000 መጀመሪያ ላይ በአንጎላ ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነት በመቋጨት ታሪክ ይዘክራቸዋል።
ለዚያም ነው ደጋፊዎቻቸው “የሰላም መሃንዲስ” እያሉ የሚጠሯቸው።
ነገር ግን በሥልጣን ዘመናቸው በተፈጸሙ መጠነ ሰፊ ሙስና እና የሰብዓዊ መብት ረገጣ ምክንያት በርካቶችም የሚተቿቸው አልጠፉም።
ዶስ ሳንቶስ በቀድሞዋ የሶቭየት ኅብረት በፔትሮሊየም ምህንድስና ዲግሪያቸውን ያገኙት በአውሮፓውያኑ 1969 ነበር።
የመጀመሪያው የአንጎላ ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ አጎስቲንሆ ኔቶ ከሞቱ ከአስር ዓመታት በኋላ ሁለተኛው ፕሬዚዳንት በመሆንም አንጎላን መርተዋል። ሥልጣን ሲቆናጠጡ ገና የ37 ዓመት ወጣት ነበሩ።
ከቅኝ ግዛት ነጻነቷን በአውሮፓውያኑ 1975 የተጎናጸፈችው አንጎላ ከአራት ዓመታት በኋላ የፖርቹጋል ቅኝ ግዛትን የተዋጉት የዶስ ሳንቶስ ኤምፒኤልኤ እና ዩኒታ በሚባሉ ቡድኖች በተፈጠረው ቁርሶ አገሪቷ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገባች።
ለ27 ዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነትም አገሪቷን አፈራረሳት። በጦርነቱ ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል ተብሎ ይታመናል።
በተጨማሪም በዚህ ጦርነት የውጭ አገራት ኃይሎች ተሳታፊ ሆነዋል። በአፓርታይድ የነጮች አገዛዝ ስር የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ወታደሮች አማጺው ዩኒታ የተሰኘውን ቡድን እንዲደግፉ ስትልክ፣ የኩባ ኃይሎች ደግሞ ለመንግሥት ወግነው ጣልቃ ገብተዋል።
ዶስ ሳንቶስ ሶቭየት ኅብረት እስትክትፈርስ እንዲሁም የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተሚያ ድረስ በማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም ላይ ያተኮረ የአንድ ፓርቲ መንግሥትን መርተዋል።
ኤምፒኤልኤ እና ዩኒታ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ግን ሁኔታዎች መቀየር ጀመሩ።