የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የሊቨርፑል እና የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎችን ይቅርታ ጠየቀ

የሊቨርፑል ደጋፊዎች ከሪያል ማድሪድ ጋር ከነበረው የሻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ በፊት ከስታድ ዲ ፍራንስ ስታዲየም ውጪ ተሰባስበው

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, የሊቨርፑል ደጋፊዎች ከሪያል ማድሪድ ጋር ከነበረው የሻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ በፊት ከስታድ ዲ ፍራንስ ስታዲየም ውጪ ተሰባስበው ታይተዋል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ሕብረት በሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ለመታደም የመጡ የሪያል ማድሪድ እና የሊቨርፑል ደጋፊዎች ላይ መስተጓጎል መፈጠር ያልነበረበት ነው ሲል ይቅርታ ጠየቀ።

ባለፈው ቅዳሜ የተካሄደው ጨዋታ የሊቨርፑል ደጋፊዎች የነበረውን ሁኔታ ከልክ በላይ የሆነ የፖሊስ ቁጥር የነበረበት፣ በአዘጋጆቹ በኩል መናበብ ያልነበረበት እና የተጨናነቀ ነበር ሲሉ ገልጸውታል።

ሪያል ማድሪድ በበኩሉ ለተፈጠረው ከፍተኛ ችግር ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ኅብረቱ ባወጣው መግለጫም “የእግር ኳስ ደጋፊዎች በዚያ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መውደቅ አይገባቸውም ነበር። እንዲህ ዓይነት ክስተት ዳግም መፈጠር የለበትም” ሲል ገልጿል።

“በስታዴ ዲ ፍራንስ የአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበራት ኅብረት ባዘጋጀው እና የአውሮፓ ክለቦች ሊደሰቱበት ይገባ በነበረው ሁነት ላይ የተፈጠረውን ክስተት ለተጋፈጡ ወይም በዛ አስፈሪ እና አስጨናቂ ሁኔታ ላለፉ ደጋፊዎች ከአክብሮት የመነጨ ይቅርታውን ይጠይቃል” ብሏል ሕብረቱ።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ትኬት ገዝተው ወደ ስታዲየም እንዳይገቡ የተከለከሉ ደጋፊዎች ገንዘባቸው “በተቻለ ፍጥነት” ሊመለስላቸው ይገባል ብለዋል።

“ከፍለው ጨዋታውን መታደም ላልቻሉ እና ከአካባቢው ለተገፉ ቤተሰቦች ሳስብ ነበር” ያሉት ማክሮን “ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ እና ኃላፊነቱ የማን እንደሆነ ለመለየት እንዲሁም ለተወዳዳሪዎቹ ማብራሪያ ለመስጠት ስለ ክስተቱ ጠይቄያለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።

የአውሮፓን እግር ኳስ የሚያስተዳድረው ሕብረቱ ቀደም ብሎ ስለተፈጠረው ችግር ለማወቅ እና ለቀጣይ ጊዜ ትምህርት በሚል በገለልተኛ አካል የተደረገውን ምልከታ ይፋ አድርጎ ነበር።

የእግር ኳስ ማኅበራቱ ሕብረት እና የፈረንሳይ መንግሥት ጨዋታው ከግማሽ ሰዓት በላይ እንዲዘገይ ምክንያት ለሆነው ችግር መፈጠር ዘግይተው ስፍራው ላይ የተገኙ ደጋፊዎች እና ሃሰተኛ ትኬቶች መኖርን በምክንያትነት አስቀምጠዋል።

ፖሊስ በተወሰኑ ደጋፊዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ እና የሚቃጥል መበተኛን ረጭቷል። ደጋፊዎች በወሮበሎች ኢላማ ተደርገው እንደነበርም ተደርሶበታል።

የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒን፣ በፍጻሜው ጨዋታ ላይ ችግር የፈጠሩት የእንግሊዝ ደጋፊዎች ብቻ ናቸው ብለዋል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ሕብረት ባወጣው መግለጫ “ምልከታው በዚያ ቀን በስታዲየም ውስጥም ይሁን በአካባቢው ምን እንደተፈጠረ የተሟላ መረጃ የሚያሳይ ይሆናል” ብሏል።

የሊቨርፑሉ የቀድሞ ዝነኛ ተጫዋች እና አመራር ሰር ኬኔ ዳግሊሽ በበኩላቸው "ይቅርታ ጅማሮ ነው፤ ነገር ግን መሄድ የሚጠበቅብን ብዙ ርቀት አለ" ብለዋል።

“ይህ ይቅርታ ጨዋታው ዘግይቶ መጀመሩ የሚያስተላልፈውን መልዕክት እና በደጋፊዎች ላይ የተፈጠረውን ነገር አይሸፍነውም” ሲሉም አክለዋል።