ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታዋቂዋ የሶማሊኛ ድምጻዊት በስደተኞች ጀልባ ላይ በደረሰ አደጋ ከልጇ ጋር ሕይወቷ አለፈ
ታዋቂዋ የሶማሊኛ ድምጻዊ ሆዳን አደንን እና በርካታ የሶማሌ ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ በፈረንሳይ ሥር በምትተዳደረው ማዮቴ የባሕር ዳርቻ አካባቢ ተገልብጣ የበርካቶች ሕይወት ማለፉ ተሰማ።
ድምጻዊት ሆዳን አደን በመድረክ ስሟ ሆዳን አፍሪካ በሚል የምትታወቅ ሲሆን በጀልባው ውስጥ ከሴት ልጇ ጋር እንደነበረች እና የሁለቱም ሕይወት ማለፉ ተገልጿል።
የድምጻዊቷ የቅርብ የሥራ አጋር እና ጓደኛ ሆነው አብዱልቃድር ፊልፊል በጀልባው ውስጥ 15 ሰዎች እንደነበሩ እና አንድ ሰው ብቻ በሕይወት መትረፍ መቻሉን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሌሎች የመረጃ ምንጮች እንዲሁ በጀልባዋ ላይ የነበሩት ስደተኞች ቁጥር 20 ይጠጋል ብለዋል።
የድምጻዊቷ ሞት ታዋቂ ግለሰቦች ጭምር የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ አውሮፓ በሕገ ወጥ መንገድ በባሕር ለመሄድ ሕይወታቸውን እንዴት ለአደጋ እንደሚያጋልጡ ያሳየ ነው ተብሏል።
የቅርብ ጓደኛዋ አብዱልቃዲር ፊልፊል "ሆዳን ጠንካራ እና ሥራዋን የምትወድ ነበረች፤ ከአባቷ የወረሰችውን የጥበብ ፍቅር ለማሳካት በጥልቅ የምትተጋ ነበረች።" ብሏል።
"ፈጣሪ ነፍሷን ይቀበላት" ሲል የተናገረው ጓደኛዋ ለአድናቂዎቿ እና ለቤተሰቦቿ መጽናናትን ተመኝቷል።
ሆዳን ድምጻዊነትን የጀመረችው ከዓመታት በፊት በስደት በምትኖርበት የኬንያ መዲና ናይሮቢ ነበር።
ሶማሊያ ውስጥ ሙዚቀኞች እና ድምጻውያን ተቀባይነት ስለሌላቸው ከአገራቸው ውጭ ሰርተው ስም እና ዝና ካተረፉ በርካታ የአገሪቱ የጥበብ ባለሙያዎች መካከልም አንዷ ነበረች።
የሙዚቃ ሥራዎቿ በሶማሊያ እንዲሁም በባሕር ማዶ በሚኖሩ የአገሪቱ ተወላጆች እና የቋንቋው ተናጋሪዎች ዘንድ አድናቆትን ያገኙ ነበሩ።
በተለይ ሥራዎቿ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተጋርተዋል።
ሆዳን ወደ ሶማሊያ ተመልሳ የሙዚቃ ሥራዋን ለመቀጠል ሞክራ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን በሞቃዲሾ ባጋጠማት ተግዳሮት ዳግም ስደትን መከተል መርጣለች።
እአአ በ2018 ከአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ላይ "እዚያ ባሕሉን ለመከተል ሞክሬያለሁ፤ ፀጉሬን መሸፈን እንኳን ለመጀመርያ ጊዜ የጀመርኩት እዚያ ነው" ብላ ነበር።
በሞቃዲሾ ከገጠሟት አስቸጋሪ ጊዜዎች መካከል አንዱን ስታስታውስም "በመድረክ ላይ ሥራዬን ሳቀርብ አንገቴን ከፕሬዚዳንቱ መደበቅ እንዳለብኝ ተነገረኝ" ብላለች።
"የመንግሥት ባለሥልጣናት በሙሉ የተገኙበት ክብረ በዓል ነበር" ያለችው ሆዳን፣ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሹ የነበራት ቆይታ ፈተናዎች እንደ ነበሩት ተናግራ ነበር።
ከልጇ ጋር ሕይወቷ ያለፈበት ማዮቴ ደሴት ከከፕሞሮስ ደሴቶች 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት።
300 ሺህ ነዋሪዎች እንዳሏት የምትገመተው ይህች ደሴት ኮሞሮስ ከቅኝ ግዛት እአአ በ1975 ነጻ ስትወጣ ደሴቲቱ ግን በፈረንሳይ አስተዳደር ሥር ቆይታለች።
የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከጥር እስከ ነሐሴ 2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ብቻ 5,435 ሶማሊያውያን በባሕር እና በየብስ አቋርጠው አውሮፓ ደርሰዋል።
ይህ ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 3.3 በመቶ ጭማሬ አሳይቷልም ብሏል።