ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፍቅር እና እገታ: ከታሊባን እስር ቤት የወጣው ምሥጢራዊ የስልክ ጥሪ
ነሐሴ 2013 ዓ. የአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል መልሳ በታሊባን እጅ ስትወድቅ መላው ዓለም ከአገር ለመውጣት የሚመርመሰመሱ አፍጋናውያን አየር ማረፊያውን ሲያጨናንቁ የሚያሳዩ ምሥሎችን ተመልክቷል።
በአሜሪካዋ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ ደግሞ አንድ ሰው የራሱን ተልዕኮ ይዞ መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር። ይህ ሰው የባሕር ኃይል ሐኪም የነበረው ሳፊ ራውፍ ነው።
የሳፊ ዓላማ አፍጋኒስታን ውስጥ መውጫ ያጡ ወዳጅ እና ባልደረቦቹን መርዳት ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ግን የሰዎችን ሕይወት አድናለሁ እንጂ ፍቅር ይይዘኛል ብሎ አልጠበቀም ነበር።
ከዚያም በላይ ሙስሊሙ ሳፊ በአይሁዳዊት ሴት ፍቅር እወድቃለሁ ብሎ እንዴት ይገምታል?
"እያንገራገርኩ ነበር አንድ ሰውን መርዳት የጀመርኩት" ይላል እዚህ ተግባር ውስጥ የገባበትን አጋጣሚ ሲያስታውስ።
"እርሱ ተሳካ። ከዚያ አንድ አንድ እያልኩ ሌሎችንም ረዳሁ። በድንገት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አፍጋኒስታን ውስጥ፣ በርካቶች ደግሞ ዋሽንግተን ውስጥ ሆነው የሚያንቀሳቅሱት ግዙፍ ተልዕኮ ሆነ" ይላል።
የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ የተወለደው ሳፊ፤ ወደ አሜሪካ የተሰደደው ታዳጊ እያለ ነበር። ከዚያ ደግሞ ራሱን ውጥረት በተሞላበት የነፍስ አድን ተልዕኮ ውስጥ አገኘው።
እዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር ሳሚ ካኖልድን የተዋወቃት። ኒው ዮርክ ውስጥ የቴያትር አዘጋጅ የሆነችው ሳሚ፤ የጓደኛዋን ቤሰቦች ከካቡል ለማስወጣት እየሞከረች ነበር።
"ምንም የማውቀው ሰው አልነበረኝም። ከዚያ ስለ ሳፊ ቡድን የተዘጋጀ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተመለከትኩ። ሊያግዘን ከቻለ በሚል ጻፍኩለት። ማድረግ የምችለው የተሻለው ነገር ወደ ዋሽንግተን መጓዝ እና ከእርሱ ቡድን ጋር በበጎ ፈቃድ ሥራ መሳተፍ እንደሆነ ነገረኝ" በማለት ታስታውሳለች።
አላንገራገረችም ልብሷን ሸክፋ፣ ባቡር ተሳፍራ ወደ ዋሽንግተን አመራች። ደርሳም በወንድ ቀድሞ ወታደሮች የተሞላውን የተልዕኮ ማዕከል ተቀላቀለች።
"የምኖረው በቴያትር ሰዎች ተከብቤ ነበር" ስትል ያጋጠማት ሁኔታ ከለመደችው ተቃራኒ መሆኑን እየሳቀች ትናገራለች።
ሳሚ ስለ አፍጋኒስታን የምታውቀው ምንም ነገር አልነበረም። ለዚህ ተልዕኮ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘ ክህሎት እንዳላት የታወቀው ኋላ ላይ ነው።
"ከኮሚዩኒኬሽ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ድሮም የለመድኳቸው ነገሮች ናቸው። ስለዚህ የኮሚዩኒኬሽን ሰው ሆንኩ። ማን ይሄንን ይገምታል?" በግርምት ትጠይቃለች።
በምስቅልቅል ውስጥ የጎመራው ፍቅር
የአደጋ ጊዜ እና የቀውስ ድባብ በሰፈነበት ተልዕኮ ማዕከል ውስጥ እየተካሄደ የነበረው ሰዎች የማዳን ዘመቻ ብቻ አልነበረም።
"መፈላለግ ነበረ ወይ? መልሱ አዎ የሚል ይመስለኛል" ስትል ሳሚ እውነታውን ታምናለች። ሳፊ ስንት ዓመቱ እንደሆነ ለማወቅ ጎግል ስታደርግ እንደነበር ታስታውሳለች። ዓላማዋ "ፍቅር ለመጀመር ዕድሜው አለመሄዱን" ማረጋጥ ነበር።
"የሳፊን ስም እና ዕድሜ ጉግል አድርጌ ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ በጣም ተጨናንቆ ለስነበር አሁን ከሚታየው የበለጠ ዕድሜው ከፍ ያለ ይመስል ነበር" ትላለች።
የመጀመሪያውን ረጅም የእግር ጉዟቸውን ያደረጉት ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ፤ የሚያስወጧቸው ሰዎች የታሊባንን የፍተሻ ጣቢያዎች እስከሚያልፉ እየጠበቁ በነበረበት ድቅድቅ ጨለማ ነው።
የአብርሃም ሊንከን መታሰቢያ ጋር እስከሚደርሱ ድረስ በዋሽንግተን ሃውልቶች መካከል ለረጅም ጊዜ ተጉዘዋል።
"ፊልም ነበር የሚመስለው። 'ይሄንን ሰውዬ ላገባው ነው?' ብዬ አሰብኩ" ትላለች ሳሚ።
ቀጥሎ ደግሞ በተልዕኮ ማዕከሉ በረንዳ ላይ ተሳሳሙ። በሁኔታው የተርበተበተው ሳፊ ራሱን ያገኘው ስለ መኪናዎች እያወራ ነበር።
ትስስራቸው ያደገው በፍጥነት ነው። የባህል ልዩነቶችን የሚፈቱበትን መንገድ ማበጀትም አልቀረላቸውም ነበር።
ሳፊ "ከቤተቦቼ ጋር እንድትተዋወቅ እጠይቃት ነበር፤ ሁሌም ሊሆን እንደማይችል ነበር የምትናገረው" በማለት ይናገራል።
የእስልምና እምነታቸው ላይ አጥባቂ የሆኑት የሳፊ ቤተሰቦች የሚጠብቁት ራሳቸው መርጠው ከሚያመጡለት የአፍጋን ሴት ትዳር እንደሚመሠርት ነበር። ሳሚ ደግሞ አይሁዳዊ ነች።
ይህም ቢሆን ግን ቀጠሉበት። ሳሚ እርሷ ሕይወቷን ከሰጠችለት የሙዚቃዊ ቲያትር ሥራ ጋር ሳፊን ማስተዋወቅ አልከበዳትም። 'ሌስ ሚዝረብልስ' የተሰኘውን ሙዚቃዊ ቲያትር ለመመልከት በሄዱበት ወቅት ከጠበቀችው በላይ ወድዶት እንደነበር ትናገራለች።
እገታ በአፍጋኒስታን
ታኃሣሥ 2014 ዓ.ም. ለሰብአዊ እርዳታ ሥራ ከወንድሙ ጋር ወደ ካቡል ተመለሰ። ሳፊ ወደ አፍጋኒስታን እንዳይጓዝ ተመክሮ ነበር። እርሱ ግን በታሊባን የተሰጠውን የምህረት እና ጥበቃ ቃል ተማምኖ እንደነበር ይገልጻል።
ከአፍጋኒስታን ሊወጡ በተዘጋጁበት በመጨረሻው ቀን ግን ሳፊ እና ወንድሙን ጨምሮ ሰባት የውጭ ዜጎች በታሊባን የስለላ አካል ታገቱ።
የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ቀናት ያሳለፈው ቀዝቃዛ ምድር ቤት ውስጥ ብቻውን ታስሮ ነበር። የታሰረበት ስድስት ጫማ በስድስት ጫማ የሆነ ክፍል መስኮትም ሆነ አልጋ እንዳልነበረው ያስታውሳል።
ኒው ዮርክ እጅጉን ተደናግጣ ነበር። ጎግል ማፕን በመጠቀም ያለበትን አድራሻ ስትመለከት የታሊባን የስለላ ዋና መሥሪያ ቤት እንደሆነ ተረዳች።
ሳፊ ከታሰረበት ክፍል ጠባቂ ጋር እስከሚግባባ ድረስ በነበሩት ጥቂት ሳምንታት ማንም ድምጹን አልሰማም ነበር። ለሰርጉ ገንዘብ ከሚፈልገው ጠበቃ ጋር ተደራድሮ አንድ የቅርብ ዘመዱ ገንዘብ እና ሞባይል ስልክ እንዲያስገባለት አደረገ።
በታሰረበት ምድር ቤት ውስጥ ኔትዎርክ ለማግኘት ወንድሙ ትከሻ ላይ ወጥቶ ለሳሚ መልዕክት ላከ፤ "ሃይ፣ እንዴት ነሽ? እወድሻለሁ" የሚል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ያወራችው ከ17 ቀናት በኋላ እንደነበር ሳሚ ታስታውሳለች። "በሕይወት እንዳለ ማወቄ ብቻ በቂ ነበር። ድምጹን መስማት መቻል በጣም የሚያስደስት ነገር ነበር። ምን ሊደርስበት እንደሚችል ማሰብም ግን ትንሽ ያስፈራል" ትላለች።
ሳፊ እስር ውስጥ ሆኖ ይዘፍን የነበረው አብረው የተመለከቱትን 'ሌስ ሚዝረብልስ' ቲያትር ሙዚቃ ነበር።
"ለመጀመሪያዎቹ 70 ቀናት ፀሐይ አላየሁም ነበር። ሁሉም ጊዜ ያሳለፍነው ምድር ቤት ውስጥ ነበር። ሌሎች ሰባት የውጭ ዜጋ የሆኑ ታጋቾች ነበሩ፤ እና ከመካከላቸው አንዱ በጠና ታመመ።"
"የትግል መዝሙሬ ሆነ" የሚለውን የሙዚቃዊ ቲያትሩን ዘፈን ማንጎራጎር የጀመረው የዚህ ጊዜ ነው።
ከሳሚ ጋር ስልክ የሚያወራው ጠባቂዎች እንዳይሰሙት ብርድ ልብስ ውስጥ ተሸፍኖ ነበር። ሁለት እርምጃ አለፍ ብሎ የተቀመጠው ወንድሙ ባለበት የፍቅር ወሬ ማውራት ደግሞ የሚያሳፍር ነበር እንደነበር ያስታውሳል።
የቤተሰብ ትውውቅ
እነ ሳፊን ለማስለቀቅ ከታሊባን ጋር ይደረግ የነበረው ድርድር እጅጉን ተራዝሞ ነበር። ከ70 ቀናት በኋላ ግን ስምምነት ላይ ተደረሰ። አሜሪካ እርምጃ የማትወስድ ከሆነ ታሊባኖች እንደሚገድሉት ዝተው እንደነበር ይናገራል።
ታሊባን ላይ ጫና ለማሳደር ሲባል የሳፊ ቤተሰቦች እና ሳሚ ድርድሩ ወደሚካሄድበት ኳታር መጓዝ ነበረባቸው። ሳሚ የሳፊን ቤተሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀችው የዚያን ጊዜ ነው።
"መኖሬን እንኳን አያውቁም ነበር። ከዚያ በድንገት አንድ ህንጻ ውስጥ ለሁለት ሳምንት አንድ ላይ ኖርን" ትላለች።
የሳፊ ቤተሰቦች እንግሊዝኛ አቀላጥፈው ስለማይናገሩ ብዙ ሰዎች እሷ የቤተሰቡ ተወካይ እንደሆነች ያስቡ እንደነበር ትገልጻለች።
አጥባቂ ለሆነው የአፍጋን ሙስሊም ቤተሰብ፤ ልጃቸው የደበቃት አይሁዳዊ ፍቅረኛ እንዳለችው ማወቅ አስደንጋጭ ነበር። የነበረው ሁኔታ ግን እውነታውን እንዲቀበሉ ያስገደደ ነበር።
"የሳፊን ቤተሰቦች አመሰግናቸዋለሁ። እኔን የተቀበሉበት መንገድ ያልተለመደ ነበር" ትላለች።
ከ105 ቀናት በኋላ ሳሚ ተለቀቀ፤ ከአፍጋኒስታን ወጥቶም ከሳሚ ጋር ለመገናኘት በቃ።
የትዳር ሕይወት
ሳፊ ከተለቀቀ በኋላ አንድ ላይ መኖር ጀመሩ። ብዙም ሳይቆዩ የአፍጋን፣ የአይሁድ እና የቲያትር ልማዶችን በቀላቀለ ሰርግ ተሞሸሩ።
እንግዶች የአፍጋንን ባህላዊ ልብሰ ለበሱ። የተከፈተው ደግሞ የአይሁድ ዘፈን ነበር። ሳፊ ከጓደኞቹ ጋር የዳንስ ትርኢት አሳይቷል።
ሳፊ እስር ላይ በነበረበት ወቅት ሳሚ ስትጽፍ ነበረው ማስታወሻም ሰርጉ ላይ ተነቧል።
32ተኛው ቀን ላይ የጻፈችው እንዲህ የሚል ነበር፤ "የሆነ ቦታ በረንዳ ላይ ከአንተ አጠገብ ቁጭ ብዬ ይህንን ማስታወሻ መልሼ የማነብበትን ቀን እናፍቃለሁ። እባክህ፣ እባክህ፣ እባህክ ተመለስ።"
በሰርጋቸው ዕለት ያሰሩት ቀለበትም ባለ ታሪክ ነው። ቀበለቱ የተዘጋጀው ሳፊ ከታሰረበት ክፍል መቆለፊያ ከተገኘ አነስተኛ ብረት ነው።