ሐማስን በመቃወም የሚንቀሳቀሰው የሚሊሻ ቡድን መሪ፣ ያሲር አቡ ሻባብ በጋዛ ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Yasser Abu Shabab/Facebook
በጋዛ ሐማስን በመቃወም የሚታወቀው የፍልስጤም ሚሊሻ ቡድን መሪ ተገደለ።
ያሲር አቡ ሻባብ በርካታ ተዋጊዎችን የያዘውን እና በደቡብ በራፋህ ከተማ አቅራቢያ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለው ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የፖፑላር ፎርስ ቡድንን መርቷል።
ፖፑላር ፎርስ ባወጣው መግለጫ አቡ ሻባብ የተገደለው በአቡ ሴኔይማ አባላት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት እየሞከረ በነበረበት ወቅት ነው ብሏል። ከእስራኤል ጋር በመተባበር በሚከስሰው በሐማስ እንደተገደለ የሚገልጹ "አሳሳች" ዘገባዎችንም ውድቅ አድርጓል።
ከአቡ ሻባብ የቤዱዊን ጎሳ አካል የሆነው ታራቢን ቀደም ሲል በሰጠው መግለጫ "በተቃዋሚ እጅ" እንደተገደለ እና የፍልስጤምን ሕዝብ ከድቷል ሲል ከሷል።
ሌሎች ምንጮች እንደሚሉት ደግሞ ሕይወቱ ያለፈው በስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ነው።
ሐማስ በግድያው ውስጥ የነበረውን ተሳትፎ ሳይጠይቅ ባወጣው መግለጫ የአቡ ሻባብ "ዕጣ ፈንታ ሕዝባቸውን እና የትውልድ አገራቸውን የሚክዱ እና ለወራሪዋ እስራኤል መሳሪያ ለመሆን የሚሞክሩ በሙሉ የማይቀር ዕጣ ፈንታቸው ነው" ሲል ገልጿል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ አቡ ሻባብ በደቡብ እስራኤል ቢርሼባ ወደሚገኘው ሶሮካ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ በደረሰበት ጉዳት መሞቱን የደህንነት ምንጭ ጠቅሶ ገልጿል። ሆስፒታሉ ግን ሕክምና እያገኘ ሕይወቱ ማለፉን አስተባብሏል።
ፖፑላር ፎርስ በመግለጫው "የመጨረሻው አሸባሪ ከጋዛ እስኪወገድ እና በሰላም ለሚያምኑ ሕዝቦቻችን ብሩህ እና አስተማማኝ ዕጣ ፈንታ እስኪገነባ ድረስ" በአቡ ሻባብ መንገድ እንደሚቀጥል ቃል ገብቷል።

የፎቶው ባለመብት, Yasser Abu Shabab/Facebook
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እስራኤል በጋዛ የሚገኙ እና ሐማስን የሚቃወሙ የፍልስጤም ጎሳዎችን እያስታጠቀች መሆኑን ባለፈው ሰኔ አረጋግጠዋል።
ይህንን የገለጹት የእስራኤል ሚዲያዎች ለፖፑላር ፎርስ የጦር መሳሪያ አቅርቦት እንደፈቀዱ ከዘገቡ በኋላ ነው። ሚሊሻዎቹ ግን እስራኤል እያስታጠቀቻቸው ነው መባሉን ክደዋል።
ፖፑላር ፎርስ በጦርነቱ ወቅት ወደ ጋዛ የተላኩ የሰብዓዊ እርዳታ መኪናዎችን በመዝረፍ ቢከሰሱም ሚሊሻዎቹም ክደዋል። ከእስራኤል በተገኙ ዘገባዎች መሠረት ሁለት አባሎቻቸው ከዚህ በፊት ከእስላማዊ መንግሥት ቡድን (አይኤስ) ጋር ግንኙነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረ ከስምንት ሳምንታት ገደማ በፊት አንስቶ በሁለተኛው ምዕራፍ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛ የሰላም ዕቅድ ውስጥ ቦታ ለማግኘት ከሚፎካከሩት በርካታ ፀረ-ሐማስ ሚሊሻ መሪዎች አንዱ አቡ ሻባብ እንደሆነ ተዘግቧል።
ይህም ጊዜያዊ መንግሥት ማቋቋም፤ ዓለም አቀፍ የሠላም አስከባሪ ኃይል ማሰማራት፤ የእስራኤል ወታደሮችን ማስወጣት እና ሐማስን ትጥቅ ማስፈታትን ያካትታል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሐማስ አሁንም በእስር ላይ የነበሩትን 48 በሕይወት ያሉ እና ሌሉ ታጋቾችን በሙሉ ሲለቅ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፍልስጤም እስረኞችን እንዲፈቱ ተደርጓል። እስራኤል በከፊል ከጋዛ መውጣት እና የሰብአዊ እርዳታ መጨመርንም የስምምነቱ አካል ነው።
የአንድ የሞተ የእስራኤል ታጋች አስከሬን እስካሁን አልተመለሰም።
የእስራኤል መንግሥት ሐማስ ሁሉንም ታጋቾች እስኪመልስ ድረስ በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ውይይት እንደማይሳተፍ ቀደም ሲል አስታውቋል። ሆኖም ትራምፕ ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት ሁለተኛው ምዕራፍ "በቅርቡ እንደሚጀመር" ተናግረዋል።
በጋዛ የተከሰተው ጦርነት የተቀሰቀሰው መስከረም 26 ቀን 2016 በደቡባዊ እስራኤል ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሲሆን 1,200 የሚያህሉ ሰዎች ሲገደሉ 251 ደግሞ ታግተው ተወስደዋል።
ከዚያን ወዲህ እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃቶች ከ70 ሺህ 120 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ሲል በሐማስ የሚመራው የአካባቢው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።















