እስራኤል በጋዛ ጥቃት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከ70 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል- የጋዛ የጤና ሚኒስቴር

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ ከ70,000 በላይ ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የሐማስ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በጥቅምት 10 የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ሲል ሚኒስቴሩ ተናግሯል።
አክሎም እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ የአየር ድብደባ ማካሄዷን እና አስከሬኖች ከፍርስራሹ ስር እየተገኙ መሆኑን ገልጿል።
ቅዳሜ ዕለት በእስራኤል ድሮን ጥቃት ከተገደሉት መካከል ፋዲ እና ጁማ አቡ አሲ የተባሉ ሁለት ሕጻናት ወንድማማቾች ይገኙበታል።
ሕጻናቱ በተገደሉበት ወቅት እንጨት እየሰበሰቡ እንደነበር ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ጉዳዩን አስመልክቶ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ቢጫ መስመሩን አቋርጠው የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎችን መትቷል።
ይህ ቢጫ መስመር የእስራኤል ጦር ከሰባት ሳምንታት በፊት በዩናይትድ ስቴትስ አደራዳሪነት በተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ለቅቆ ለመውጣት የተስማማበትን መስመር ያመለክታል።
የሞቱት ሕጻናት ልጆች በሚዲያ ዘገባዎች የስምንት ዓመት እና የ10 ወይም የ11 ዓመት ወንድማማቾች እንደሆኑ ተገልጸዋል።
ዘመዶቻቸው እንደተናገሩት ልጆቹ ሲገደሉ በደቡባዊ የጋዛ ሰርጥ ከኻን ዩኒስ በስተምሥራቅ የማገዶ እንጨት እየፈለጉ ነበር።
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ቅዳሜ ዕለት በናስር ሆስፒታል ተካሂዷል።
ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች በእስራኤል መንግሥት በተናጥል ወደ ጋዛ እንዳይገቡ ታግደዋል፤ ስለዚህ ከሁለቱም ወገኖች የተገኙ መረጃዎችን በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻሉም።
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገደሉት የፍልስጤማውያን ቁጥር አሁን 70,100 እንደደረሰ እና 350 የሚሆኑት ፍልስጤማውያን የሞቱት ከጥቅምት 10 የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ እንደሆነ ተናግሯል።















