በእስራኤል አየር ጥቃት 25 ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስትር ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በፈፀመችው ጥቃት በትንሹ 25 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሕይወት አድን ሠራተኞች በጋዛ ከተማ ምሥራቃዊ ዘይቱን አካባቢ የሚገኝ ሕንጻ በእስራኤል ጦር ጥቃት በደረሰበት ወቅት አንዲት አዋቂ ሴት እና አንዲት ታዳጊ ልጅን ጨምሮ 10 ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር ታጣቂዎች ለአምስት ሳምንታት የቆየውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ በደቡባዊ ኻን ዩኒስ በሚንቀሳቀሱ ወታደሮቹ ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ገልጾ "የአሸባሪው ሐማስ ዒላማዎችን" መትቻለሁ ብሏል።
ከሐማስ የተሰጠ ምላሽ የለም።
በአካባቢው ዳግም ውጥረት የተቀሰቀሰው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ ለሁለት ዓመት የዘለቀውን አውዳሚ ጦርነት ለማስቆም ያቀረቡትን ባለ 20 ነጥብ ዕቅድ ካፀደቀ በኋላ ነው።
በጋዛ ሐማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ረቡዕ ምሽት የእስራኤል የአየር፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የመድፍ ጥቃቶች በጋዛ ከተማ እና በኻን ዩኒስ በርካታ ቦታዎች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል።
ጥቃቶቹ ከበርካታ ቀናት አንጻራዊ መረጋጋት በኋላ ከፍተኛ ውጥረት ፈጥረዋል ብለዋል።
የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲው በዘይቱን በደረሰው ድብደባ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሕንጻ እና በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጿል። የሕይወት አድን ሠራተኞች በፍርስራሽ ስር የተቀበሩ ሁለት ሰዎች ሲያወጡ የሚያሳይ ቪዲዮም ለጥፏል።
በአናዶሉ የዜና ወኪል የተለቀቁ ፎቶዎች የሦስት ትንንሽ ሕጻናት አስከሬን ከስፍራው መገኘቱን ያሳያሉ።
በጋዛ ከተማ በሰው አልባ አውሮፕላን በተፈጸመ ሌላ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል በርካቶች ቆስለዋል ሲሉ ባሳል ተናግረዋል።
በምሥራቅ ጋዛ ከተማ በሼጃያ ሙሽታሃ ጎዳና የሚገኙት የባልቦል ቤተሰብ ንብረት ላይ በታንክ በተፈጸመ ድብደባ ደግሞ ሌላ ሰው መገደሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በኻን ዩኒስ በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ (ኡንዋዋ) በሚተዳደረው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ "በርካታ አሸባሪዎች የመከላከያ ሠራዊቱ ወታደሮች በኻን ዩኒስ በሚንቀሳቀሱበት ቦታ ላይ ተኩስ ከፍተዋል" ብሏል።
"ይህ እርምጃ የተኩስ አቁም ስምምነቱን መጣስ ነው፤ የእስራኤል ወታደሮች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም" ሲል አክሏል።
"በምላሹም የመከላከያ ኃይሉ በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ የአሸባሪው ሐማስ ዒላማዎችን መደብደብ ጀምሯል" ብሏል።
የእስራኤሉ መገናኛ ብዙኃን ካን የደህንነት ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የጥቃቶቹ ዒላማዎች የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የዘይቱን ሻለቃ አዛዥ የኢዝ አል-ዲን እና የባህር ኃይሉ አዛዥ ናቸው።
ሰኞ እለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እአአ ጥቅምት 10 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማጠናከር የሚያስችል ውሳኔ አሳልፏል።
የምክር ቤቱ አባል አገራት፤ በፕሬዚዳንት ትራምፕ የሚመራ የሰላም ቦርድ እና ጊዜያዊ ዓለም አቀፍ የሚያረጋጋ ኃይል (አይኤስኤፍ) የተባለ የሽግግር አስተዳደር እንዲቋቋም ፈቅደዋል።
ትራምፕ ውሳኔውን ሲያወድሱ ሐማስ በበኩሉ ያለ ፍልስጤም መንግሥት ምስረታ መሣሪያዎቹን አሳልፎ እንደማይሰጥ ደጋግሞ ገልጿል። ከእስራኤል ጋር የሚያደርገው ውጊያም ትክክለኛ እና "ትግል" እንደሆነ ተከራክሯል።















