እስራኤል በጋዛ በመጠለያ ድንኳኖች ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል፤ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በተጠለሉባቸው ድንኳኖች ላይ በፈጸመችው አየር ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ አምስት ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 32 ገደማ ሰዎች መቁሰላቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ተናገሩ።
ጥቃቱ የተፈጸመው ከኻን ዩኒስ ከተማ በስተምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው የጋዛ የባሕር ዳርቻ አል ማዋሲ አካባቢ ነው።
በኩዌር ፊልድ ሆስፒታል የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ ከተገደሉት መካከል የስምንት እና የ10 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት ወንድ ሕጻናት ይገኙበታል። የ46 እና 30 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት ሴቶች እና አንድ የ36 ዓመት ወንድም ከሟቾች መካከል እንደሆኑ ተገልጿል።
በአየር ጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው 32 ገደማ ሰዎች የተጎዱት በሆስፒታል ሕክምና እየተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የነፍስ አድን ሠራተኞች፤ አልናጃት ከተባለው ካምፕ አስከሬኖችን ማውጣታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህ ካምፕ ባለፉት ጥቂት ወራት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተጠለሉባቸውን በርካታ ድንኳኖች የያዘ ነው።
የዐይን እማኞች እንደሚናገሩት የመጀመሪያው ጥቃት ዒላማ ያደረገው በአል ማዋሲ የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ የሚገኝ ድንኳንን ነው። ቀጥሎም በኩዌት ሆስፒታል አቅራቢያ ፍንዳታ መሰማቱን አስረድተዋል። ይህም በአቅራቢያ በሚገኙ መጠለያዎች ውስጥ የሰፈሩ ቤተሰቦች ላይ ድንጋጤ መፍጠሩን አክለዋል።
የእስራኤል ጦር፤ ረቡዕ ዕለት አምስት ወታደሮቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ "የሐማስ ሽብርተኞች ላይ ጥቃት መፈጸሙን" ተናግሯል።
"የሐማስ ሽብር ድርጅት በተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ግልጽ ጥሰት ፈጽሟል፤ በዚህም ሽብርተኞች በራፋህ አካባቢ የተሰማሩ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል" ሲል ባወጣው መግለጫ ከስሷል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትያናሁ "በዚሁ መሠረት ምላሽ" እንደሚሰጥ ዝተዋል።
ሐማስ በበኩሉ የእስራኤልን ጥቃት አረመኔያዊ፣ ንጹኃንን ያልለየ እና የተኩስ አቁም ስምምነቱን የጣሰ በማለት ገልጾታል።
በመስከረም 2016 ዓ. ም. 1,200 ሰዎች የተገደሉበት እና 251 ያህል ሰዎችን ታግተው የተወሰዱበትን የሐማስ ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል ሠራዊት በጋዛ በፈጸመው ወታደራዊ ዘመቻ ከ70,000 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።














