“ሳልታመም ለ50 ዓመት ሆስፒታል ውስጥ ኖርኩኝ”

የፎቶው ባለመብት, Margo McKeever
ቻርልስ ኤስለር ከ50 ዓመታት በላይ ሳይታመም ሆስፒታል አልጋ ይዞ ኖሯል።
መጠነኛ የመማር ውስንነትና የሚጥል ሕመም አለበት። መጀመሪያ ሆስፒታል የተወሰደው በ10 ዓመቱ ነበር።
ነጻነቱን አጥቶ በሆስፒታል መቀመጥን በጣም ይጠላዋል።
እህቱ ማርጎ በነጻነት የሚኖርበት ቦታ ላይ እንዲሆን ለማስቻል ለዓመታት ታግላለች።
ቻርልስ 62 ዓመት ሲሆነው ነው የሱና የእህቱ ጥያቄ የተመለሰው።
በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚኖርበት ቤት ቁልፍ ተሰጥቶታል።
‘ዘ ሪችመንድ ፌሎሺፕ ስኮትላንድ’ የተባለው በጎ አድራጎት ድርጅት ሠራተኛ ዴቪድ ፍሌሚንግ እንደሚለው፣ የቻርልስ ቤተሰቦች ለዓመታት ነው የታገሉት።
“ቋሚ ቦታ እንዲኖር ብለው ቤተሰቦቹ ለዓመታት ታግለዋል። የሚያሳዝነው ነገር ሰዎች በሥርዓቱ ውስጥ ተውጠው መቅረታቸው ነው” ይላል።
ቢቢሲ ስኮትላንድ ባደረገው ምርመራ እንዳገኘው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመማር ውስንነት ያለባቸው ሰዎች ለዓመታት በሆስፒታል ወይም ከቤተሰቦቻቸው በራቀ ስፍራ ይኖራሉ።
የመንግሥት ፖሊሲ ለረዥም ጊዜ በሕክምና ተቋም የቆዩ ሰዎች ወደ ቤታቸው መግባት አለባቸው ቢልም ብዙዎች ግን ከሆስፒታል መውጣት ሳይችሉ ቆይተዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት የስኮትላንድ መንግሥት ሰዎችን ከሆስፒታሎች አስወጥቶ ቤታቸው እንደሚያስገባ አስታውቆ ነበር።
ይህም ይጠናቀቃል የተባለው እአአ በ2024 ነበር።
ቢቢሲ በቅርቡ ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ግን በሆስፒታል ያሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው የመጣው።
በብሔራዊ ደረጃ የተመዘገበው ቁጥር እንደሚያሳየው ከቤታቸው ርቀው የሚገኙ ሰዎች ከ1,243 ወደ 1,398 (12%) ጨምሯል።

የፎቶው ባለመብት, Margo McKeever
በአውሮፓውያኑ 2024 በጋ ላይ ‘ፍሪደም ኦፍ ኢንፎርሜሽን’ ባወጣው መረጃ መሠረት የመማር ውስንነት ያለባቸው በሆስፒታል የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ173 ወደ 191 ጨምሯል።
ማንኛውም ሰው በአካባቢው በሚደረግለት ድጋፍ መኖር እንደሚችል ቻርልስ ማሳያ ነው።
“ባደረግኩት የመኖሪያ ቦታ ለውጥ ተደንቄያለሁ። አሁን በነጻነት፣ በጥሩ ሁኔታ እየኖርኩ ነው” ይላል ቻርልስ።
ያደገው ግላስጎው ነው።
ከሆስፒታል ከ50 ዓመታት በኋላ መውጣቱን ተከትሎ “አሁን ያሻኝ ቦታ እሄዳለሁ። መጠጥ ቤት እሄዳለሁ። ምሳ እበላለሁ። ዓሣና ድንች ጥብስ ነው የምወደው። በጣም ነው ደስ የሚለው። በስተመጨረሻ ነጻ ወጣሁ” ሲል ሕይወቱን ይገልጻል።

የፎቶው ባለመብት, Margo McKeever
ቤቱ የጄምስ ቦንድ ፊልሞችን መመልከት እንደሚያስደስተው ተናግሯል።
ምግብ ማብሰል፣ አትክልት መትከልና ማጽዳት እየተማረ ነው።
እህቱ ማርጎ መክቪር እንደምትለው ወንድሟ ልጅ ሳለ ጀምሮ ባሕሪው አስቸጋሪ ስለነበር ሆስፒታል እንዲያስገቡት ቤተሰቦቹ ምክር ተሰጥቷቸዋል።
ሐኪሞች የቻርልስን የሚጥል ሕመም መድኃኒት በተገቢው መንገድ መስጠት አልቻሉም።
“በአንድ ቀን አይደለም ከሆስፒታል እንዲወጣ የተወሰነው። ጊዜ የወሰደ ሂደት ነበር። የራሱን ቤት እንዲያገኝ ለማስቻል 14 ዓመታት ወስዷል” ትላለች።
“ሁሉም ሰው የሚንከባከበውና ቁጥር ሆኖ እንዳይቀር የሚረዳው ሰው ይፈልጋል” ስትልም ታክላለች።

የፎቶው ባለመብት, Margo McKeever
ፍራሰር ማልኮም ከሆስፒታል ለመውጣት ዝግጁ ነው ቢባልም ለሦስት ዓመታት ከሆስፒታል አልወጣም።
ፍራሰር 20 ዓመቱ ነው። በዌስት ኪልብራይድ ነው ያደገው።
የንግግር ውስንነት አለበት። ሆስፒታል ከመግባቱ በፊት የተሻለ ሕይወት እንደነበርው ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።
ልዩ ትምህርት ቤት ነበር የሚማረው። ባሕር ላይ መጓዝ ይወድ ነበር። ክረምት መርከብ በማደስ ያሳልፋል።
ቤተሰቦቹ “እርዳታ መጠየቃችን ትልቁ ስህተታችን ነበር” ይላሉ።
እናቱ ካረን እንደምትለው ሆስፒታል መኖሩ ልጇን እየጎዳው ነው።
“ሆስፒታሉ፣ አንድ ወቅት ላይ የነበረውን ማንነት እየነጠቀው ነው” ትላለች ካረን።
የመማር ውስንነት ያላቸውና ሆስፒታል እንዲኖሩ የተደረጉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ በጣም እንደሚያሳዝን ትናገራለች።
“ከቤተሰቦች ጋር ስንነጋገር ምን ያህል ሁኔታው እንደጎዳን እናወራለን” ትላለች።
የፍራሰር ቤተሰቦች ልጃቸው ቤት ውስጥ የሚያስፈልገውን ነገር አመቻችተው ከሆስፒታል እንዲወጣ እየጠየቁ ነው።
እንደ ሌሎች ቤተሰቦች ሁሉ ለልጆቻቸው ከሆስፒታል ወደ ቤት የሚደረግ ሽግግር ላይ የሚያግዙ ባለሙያዎች ለማግኘት ይቸገራሉ።
የ ‘ኖርዝ አይሸር ኸልዝ ኤንድ ሶሻል ኬር ፓርትነርሺፕ’ ቃል አቀባይ ወጣቱን ከሆስፒታል ለማስወጣት የሚደረገውን ጥረት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የ ‘ግላስጎስ ኸልዝ ኤንድ ኤንድ ሶሻል ኬር ፓርትነርሺፕ’ ቃል አቀባይ እንደ ቻርልስ ሌሎችንም ከሆስፒታል ለማስወጣት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ባገኘው መረጃ መሠረት በስኮትላንድ 120 ሰዎች ከዓመት በላይ ሆስፒታል መቆየት ሳያስፈልጋቸው ሆስፒታል ቆይተዋል።
ከእነዚህ መካከል 28 የሚሆኑት ከ20 ዓመት በላይ የቆዩ ናቸው።
የመማር ውስንነት ያለባቸው ሰዎች ከሆስፒታል መውጣት ሳይችሉ መቅረታቸውን ቢቢሲ ለማወቅ ችሏል።
ሆስፒታል ውስጥ ተዘግቶባቸው እንዲኖሩ ተገደዋል።

የፎቶው ባለመብት, Margo McKeever
የ37 ዓመቱ ካይል ጊቦን ካርስቴርስ ሆስፒታል ውስጥ ለ15 ዓመታት ኖሯል።
የ26 ዓመቱ ጄሚ ከ19 ዓመቱ ጀምሮ በውድላንድስ ቪው ሆስፒታል ኖሯል።
እአአ በ1990ዎቹ የመማር ውስንነት ያለባቸው ሰዎች በሆስፒታል ለመኖር መገደዳቸው ኢሰብአዊ ነው ተብሏል።
እንደማንኛውም ሰው በቤታቸው የመኖራቸው መብት እንዲጠበቅ መመሪያ ወጥቷል።
ዶ/ር ሳም ስሚዝ የ ‘ሲ ቼንጅ ስኮትላንድ’ ኃላፊ ናቸው።
“ሰዎች ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል እየቻሉ፣ ረዥም ጊዜ የሚያቆዩ ሆስፒታሎችን ዘግተን ነበር” ይላሉ።
የስኮትላንድ መንግሥት ከቤተሰቦቻቸው ርቀው የሚኖሩ ሰዎችን በመመዝገብ 20 ሚሊዮን ፓውንድ መድቦ ወደ ቤታቸው የመመለስ ፕሮጀክት ነድፏል።
የማኅበራዊ እንክብካቤ ሚኒስትር ማሪ ቶድ “ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኛ ነን። ችግሩን ለመቅረፍ ግን ቀላል አይደለም። መፍትሄ መስጠት ከሚችሉ የየአካባቢው አመራሮች ጋር በመሆን እየሠራን ነው” ይላሉ።












