ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አቶ ጌታቸው ረዳ የጊዜያዊ መስተዳደራቸውን ካቢኔ ይፋ አደረጉ
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ያካተተ አዲስ ካቢኔያቸውን ይፋ አደረጉ።
በአቶ ጌታቸው ካቢኔ ውስጥ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በተደገው ጦርነት የትግራይ ኃይሎችን ሲመሩ የነበሩት ሌተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና ቀድሞው የአገሪቱ ሠራዊት ኤታማዦር ሌተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።
ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 27/2015 ዓ.ም. ሥነ ሥርዓት ላይ በደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ይመራ የነበረው የክልሉ አስተዳደር በአቶ ጌታቸው ረዳ ለሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ሥልጣን አስረክቧል።
የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በደረሱት የሰላም ስምምነት መሠረት ነው ጊዘያዊ አስተዳደሩ የተመሰረተው።
በዚህም ምርጫ ተደርጎ አዲስ የክልል መስተዳደር እስኪመሰረት ድረስ ትግራይን የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።
የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተክሎ አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕስ መስተዳድር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተሾሙት ከሳምንት በፊት ነበር።
ይህንንም ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳ ኃላፊነቱን መረከባቸው ይፋ በሆነበት በዛሬው ዕለት 27 አባላት ያሉት ካቢኔያቸውን አሳውቀዋል።
በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ሌተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የሰላም እና ፀጥታ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን፤ ሌተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ ደግሞ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።
ከሁለቱ ከፍተኛ የጦር አመራሮች በተጨማሪ የባይቶና ትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በአቶ ጌታቸው ካቢኔ ውስጥ ሁለት ኃላፊነቶችን ይዘው መካተታቸው ተገልጿል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት እነማን ናቸው ?
ሌተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ - ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሰላምና ጸጥታ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ
ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገ/ተንሳኤ - በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታዜይሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ
ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት - የማህበራዊ ልማት ሽግግር ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ
አቶ በየነ ምክሩ - የኢኮኖሚ ልማት ሽግግር ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ
ሐጎስ ጎደፋይ (ዶ/ር) - የእቅድ፣ ገቢና የሀብት አስተዳደር ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ
አቶ ሐድሽ ተስፋ - የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ እና
ሌተናንት ጄነራል ፍስሃ ኪዳኑ ፋንታ – የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ይገኙበታል።