ዶናልድ ትራምፕ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የቡድን 20 ስብሰባ ላይ አገራቸው እንደማትሳተፍ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዶናልድ ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ መድልዎ ታደርሳለች በማለት አገሪቱ በምታዘጋጀው የቡድን 20 አገራት ስብሰባ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ እንደማትሳተፍ ተናገሩ።
ትራፕም ደቡብ አፍሪካ የዓለም ትልልቅ ምጣኔ ሃብት ያላቸው አገራት በጆሃንስበርግ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ የሚሳተፉበትን ስብሰባ በማዘጋጀቷ "ትልቅ ውርደት ነው' ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዋይት ሐውስን ውሳኔ "የሚያጸጽት" ሲል ገልፆት፣ "የስብሰባው ውጤታማነት በአንድ አባል አገር ላይ የተመሰረተ" እንደማይሆን የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ክሪስፒን ፊሪ ለቢቢሲ ኒውስ አዎር ተናግረዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አፍሪካናዎችን እና ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን የሚወክሉትን ጨምሮ፣ አንዳቸውም በአገሪቱ ውስጥ የዘር ማጥፋት ስለመፈጸሙ ያሉት ነገር የለም።
ፊሪ ለቢቢሲ ኒውስ አዎር ፕሮግራም በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ትራምፕ "የደቡብ አፍሪካን የቀደመ የሚረብሽ የቅኝ ግዛት ታሪክ በመጠቀም. . . በአዕምሯቸው የሚስሉትን ቀውስ እያቀነባበሩ ነው" ብለዋል።
አክለውም "በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ መድልዎ እየደረሰ ነው ለሚለው ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም" በማለት አስተባብለዋል።
"ደቡብ አፍሪካ የራሷ ችግሮች አሉባት እና እነርሱን ለመቅረፍ እየሰራን ነው። ወንጀል ምንም ዘር ሳይለይ ሁሉንም የሚጎዳ ይመስለኛል" ሲሉ ተናግረዋል።
"ያለ ዩናይትድ ስቴትስ ስብሰባችንን እንቀጥላለን" ሲሉም አክለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ "የቡድን 20 አገራት ስብሰባ በደቡብ አፍሪካ መካሄዱ ትልቅ ውርደት ነው" በማለት ለጥፈዋል።
"አፍሪካና (በብዛት የደች፣ የፈረንሳይ እና ጀርመን ዝርያ ያላቸው የደቡብ አፍሪካ ነጮች) እየተገደሉ እና እየታረዱ ነው፤ መሬታቸው እና እርሻቸውም ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ እየተወረሰባቸው ነው" ሲሉ ጽፈዋል።
"ይህ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እስከቀጠለ ድረስ ማንም የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን ስብሰባው ላይ አይገኝም።"
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ የዘር ማጥፋት ተካሄዷል የሚለው ውንጀላ "እውነት አለመሆኑ በብዙኃን የተረጋገጠ እና አሳማኝ በሆነ መረጃ ያልተደገፈ ነው" ብሏል።
የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ "የፈጠራ ታሪክ" በማለት ውድቅ አድርጎታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ብሎ ደቡብ አፍሪካ ከቡድን 20 መውጣት አለባት ብለው እንደሚያምኑ ተናግረው ነበር።
ደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ መድልዎ ታደርሳለች ብለው በተደጋጋሚ የከሰሱት ትራምፕ፤ በጉባዔው እንደማይገኙና በምትካቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስን እንደሚልኩ ገልጸው ነበር።
አሁን ግን ዋይት ሐውስ የትኛውም የአሜሪካ ባለሥልጣን በጉባዔው ላይ እንደማይሳተፍ ይፋ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በየዓመቱ አንድ የተለየ አባል አገር የቡድን 20 ጉባዔን በማስተናገድ የመሪዎችን አጀንዳ ያዘጋጃል።
ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ጉባዔውን የማዘገጀት ኃላፊነት የአሜሪካ ነው።
የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው "የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አፍሪካናስ በብቸኝነት የነጮች ቡድን መደረጉ ታሪካዊ መሆኑን ለማሳወቅ ይፈልጋል። በተጨማሪም ይህ ማኅበረሰብ መድልዎ ይደርስበታል የሚለው በእውነታ ላይ የተመሠረተ አይደለም።" ብሏል
ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት በጥር ወር ዳግም ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ በተደጋጋሚ ደቡብ አፍሪካ የነጭ ህዳጣንንታገላለች ሲሉ ይሰማሉ።
በግንቦት ወር ሲሪል ራማፎሳ ጋር በዋይት ሐውስ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅትም ነጮች ላይ መድልዎ ይፈጸማል ሲሉ ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር በሚቀጥለው ዓመት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ወደ 7 ሺህ 500 እንደሚገድብ ሲወስን ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ ለነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
ጂ20 የተመሠረተው እአአ በ1999 ከእስያ የፋይናንስ ቀውስ በኋላ ነው። በምስረታው ላይ የተሳተፉት አገራት ከ85 በመቶ በላይ የዓለም ሃብት ያላቸው ሲሆን ዓላማውም የኢኮኖሚ መረጋጋትን ወደ ነበረበት መመለስ ነበር።
የመጀመርያው የመሪዎች ጉባኤ እአአ በ2008 የተካሄደው የዚያን ዓመት የተከሰተውን የዓለም የገንዘብ ቀውስ ተከትሎ አለም አቀፍ ትብብርን ለማበረታታት ነው።
አሁን መሪዎቹ በየዓመቱ ከአውሮፓ ኅብረት እና ከአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች ጋር በመሆን ስለዓለም ኢኮኖሚ እና አገራት እያጋጠሟቸው ስላሉ ጉዳዮች ይወያያሉ።















