አይቮሪ ኮስት፡ ከእርስ በርስ ጦርነት በቢሊዮን ዶላር የአፍሪካ ዋንጫን ወደ ማዘጋጀት

አይቮሪ ኮስት

አይቮሪ ኮስት የ2023ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅቷን አጠናቃ እና ተወዳዳሪዎቹን ተቀብላ ቅዳሜ ምሽት ውድድሩን ጀምራለች።

የአይቮሪ ኮስት መንግሥት ይህ ውድድር በአገሪቱ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት በ2011 ካበቃ በኋላ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ያስመዘገበችውን አስደናቂ ለውጥ እንደሚያፋጥነው ተስፋ ሰንቋል።

ውድድሩን ለማዘጋጀት የአገሪቱ መንግሥት ቢያንስ 1 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ አድርጓል። አራት አዳዲስ ስታዲየሞች ተገንብተዋል። ሁለቱ ደግሞ ትልቅ እድሳት ተደርጎላቸዋል።

ጨዋታዎቹን የሚያስተናግዱት አምስት ከተሞች አቢጃን፣ ቡዋኬ፣ ኮርሆጎ፣ ሳን ፔድሮ እና ዋና ከተማዋ ያሙሶክሮ ናቸው።

አይቮሪ ኮስት በእነዚህ ከተሞች የአየር ማረፊያዎች፣ መንገዶች፣ ሆስፒታሎችና ሆቴሎች ገንብታለች አልያም ማሻሻያ አድርጋለች።

ይህም ከ2002 እስከ 2007 እንዲሁም ከ2010 እስከ 2011 የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ትልቁ የመልሶ ግንባታ ሥራ ሆኗል። የተወሰኑት መልሶ ግንባታዎች የተከናወኑት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ባለፈው ሚያዝያ በተገኘው 3.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ነው።

እንደአይኤምኤፍ ከሆነ አይቮሪ ኮስት ከ190 አገራት 138ኛዋ ሃብታም ሀገር ሆና ተቀምጣለች። ምንም እንኳን የቀድሞ የአይኤምኤፍ ተቀጣሪ የነበሩት ፕሬዚዳንት አላሳን ኦታራ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በዓመት በአማካይ 8 በመቶ ዕድገት ብታስመዘግብም የአገሪቱ ወጪ ለአንዳንዶች አሳሳቢ ሆኗል።

"አይቮሪ ኮስት ድሃ ሀገር ናት" ሲሉ አይቮሪ ኮስታዊው የምጣኔ ሃቭት ፕሮፌሰር ፕራኦ ያኦ ሴራፊን ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግረዋል።

"በዚህም ምክንያት ፕሬዝዳንት ኦታራ ይህንን ፕሮጀክት ለመደገፍ ብድር መውሰድ ነበረባቸው። የተወሰደው ብድር ለአይቮሪ ኮስት በትክክል እንደሚጠቅሙ ማረጋገጥ አለብን። አገሪቱ መሠረተ ልማቶቹን መጠበቅ አለባት።”

"በጥንቃቄ ካልያዝነው እና ከስታዲየሞቻችን የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ ዝግጅቶችን ካላዘጋጀን የዝሆኖቹ አገር ነጭ ዝሆኖችን እንዳታፈራ እሰጋለሁ።"

'ነጭ ዝሆኖች' የሚለው ቃል ቀደም ሲል ከነበረ ውድ እንስሳትን ለንጉሣዊው ከሚሰጥበት የታይላንድ ልማድ የተገኘ ነው። ወጪያቸው ከጥቅማቸው በላይ ናቸው የሚባሉ የመሠረተ ልማት ፕሮጄክቶችን ለመገልለጽ 'ነጭ ዝሆኖች' ጥቅም ላይ ላይ ይውላል።

ታዲያ በአንድ ወቅት በአፍሪካ የትልልቅ ዝሆኖች አገር የነበረችው አይቮሪ ኮስት ይህን መሰሉ ችግር ይደርስባት ይሆን?

እንደዚያ አይሆንም ይላሉ የአገሪቱ ፖለቲከኞች።

ወደፊቱን መገንባት

ስታዲየም

አይቮሪ ኮስት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ መሠረተ ልማቶችን የገነባችው ከወጪዋ ትርፍ ልታገኝ እንደምትችል በማሰብ እንደሆነ አንዳንዶች ይገመታሉ።

የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴን የሚመሩት ፍራንሷ አሚቺያ ግን ይህ የአይቮሪ ኮስት ዓላማ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

"አይቮሪ ኮስት ይህን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ስትወስን ገንዘብ ለማግኘት አልማ ሳይሆን እራሷን ለመለወጥ ነው” ብለዋል የአይቮሪ ኮስት የፓርላማ አባል የሆኑት እና የቀድሞ የስፖርት ሚኒስትሩ አሚቺያ።

"የስፖርት መሠረተ ልማቶችን መገንባት የሚያስችል ዕድል ተፈጥራል። ለዓመታት ምንም ዓይነት የስፖርት መሠረተ ልማት አልተገነባም ነበር። የአፍሪካው ዋንጫ አራት አዳዲስ እንዲሰሩ እና ሁለት ስታዲየሞች በአንድ ጊዜ እንድናድስ አስችሎናል።”

የያሙሱኩክሮ ስታዲየም ለመገንባት 79 ሚሊዮን ዶላር፣ ለኮርሆጎ ስታዲየም 84 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የአቢጃን ኦሊምፒክ ስታዲየምን ለመገንባት ደግሞ 113 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎባቸዋል።

ለስታዲየም እድሳት ደግሞ 109 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል።

በአምስቱ አስተናጋጅ ከተሞች 24 ማሰልጠኛ ማዕከላት ተገንብተዋል ወይም ታድሰዋል።

አይቮሪ ኮስት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኮርሆጎ እና ሳን ፔድሮ ያሉ ሆስፒታሎች የማሻሻያ ግንባታ ተደረገላቸው። የሁለቱ ከተሞች አየር ማረፊያዎች እንዲሁ ታድሰዋል። ከአቢጃን እስከ የባህር ዳርቻዋ ሳን ፔድሮ እና ከሰሜን እስከ ኮርሆጎ ያሉት አውራ ጎዳናዎች ማሻሻያ ተድርጎላቸዋል።

"ውድድሩን ማዘጋጀታችን የትራንስፖርት መስመሮችን እንድናሻሽል አስችሎናል" ሲሉ አሚቺያ አክለዋል።

"አይቮሪ ኮስት አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ እንዳለፈች እናውቃለን። ይህም በኢኮኖሚ ረገድ ቀላል አልነበረም። ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ግን አይቮሪ ኮስት ለታዳጊ አገር ብቁ የሆኑ የስፖርት እና ስፖርታዊ ያልሆኑ መሠረተ ልማቶችን እንዲኖራት አስችሏታል።"

መሠረተ ልማቶችን ጥቅም ላይ ማዋል

የአይቮሪ ኮስት የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ትልቅ ወጪ የወጣባቸውን የስፖርት መሠረተ ልማቶች ከአፍሪካ ዋንጫ በኋላም ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሁኔታ እያሰበ ነው።

በቅርቡ የአሴቶች የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድርን ያስተናገዱት አዳዲሶቹ ስታዲየሞች ወደፊትም በቀጠናው ለሚካሄዱ ውድድሮች የአስተናጋጅ ሚናን ለመውሰድ እንደሚጥር ይጠበቃል።

“አገራችን የምዕራብ አፍሪካ ውድድሮች ዋነኛ መዳረሻ እና የውድድር ማዕከል መሆኗን እናረጋግጣለን” ብሏል የአይቮሪ ኮስት እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዲዓሎ።

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ያፈናቀለው የአይቮሪ ኮስት የእርስ በእርስ ጦርነት አገሪቱን ከፍተኛ የፋይናንስ ኪሳራ ውስጥ ከትቷት ነበር።

ይሁን እንጂ የአገሪቱ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ከቡና እና ካካዎ ምርት ውጤት ጋር ተደማምሮ አይቮሪ ኮስት የምዕራብ አፍሪካ ሁለተኛዋ ትልቅ የኦኮኖሚ ባለቤት ለመሆን ከጫፍ ደርሳለች።