ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ የአሜሪካ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ተባለች

የፎቶው ባለመብት, AP
ከትውልደ ኢትዮጵያውያን የተገኘችው ናኦሚ ግርማ የአሜሪካ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ተባለች።
ናኦሚ ለአሜሪካ ሴት ብሔራዊ ቡድን እና ለሳን ዲያጎ ዌቭ ክለብ እየተጫወተች ትገኛለች።
አሶሽየትድ ፕረስ እንደዘገበው ናኦሚ ይህንን ሽልማት ስታገኝ በአሜሪካ የሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ሁለተኛዋ ጥቁር እግር ኳስ ተጫዋችና የመጀመሪያዋ ተከላካይ ናት።
የአሜሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ2023 ባደረጋቸው የሴቶች የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ የቡድኑን የተከላካይ ክፍል በብቃት መምራቷ ተገልጿል።
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ የተወለደችው የ23 ዓመቷ ናኦሚ ግርማ የምትመራው የብሔራዊ ቡድኑ የተከላከይ መስመር አውስራሊያ እና ኒው ዚላንድ ባዘጋጁት የሴቶች የዓለም ዋንጫ በአራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ነበር የተቆጠረበት።
ከሽልማቱ በኋላ እግር ኳስ ተጫዋቿ “ሽልማቱን በማሸነፌ ደስ ብሎኛል” ማለቷ ተዘግቧል።
“ከዚህ ሽልማት ጀርባ ሌሎች የቡድን አጋሮቼ ቁልፍ ሚና ነበራቸው። ያለፈው ዓመት ለኔ እና ለብሔራዊ ቡድኑ ታሪካዊ ዓመት ነበር” ማለቷም ተገልጿል።
የዓመቱ ምርጥ ወጣት እግር ኳስ ተጫዋች እና የዓመቱ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማት ስታገኝ ስድስተኛዋ ተጫዋች መሆኗን የኤፒ ዘገባ ይጠቁማል።
በ2020ም የዓመቱ ምርጥ ወጣት እግር ኳስ ተጫዋች ተብላ ነበር።
“በማሸነፌ ክብር ይሰማኛል። የመጀመሪያዋ ተከላካይና ሁለተኛዋ ጥቁር አሸናፊ በመሆኔ ተደስቻለሁ። የግብ ጠባቂዎቻችን እና የመላው ቡድናችንም የልፋት ውጤት ነው” ብላለች።
“ሁላችንም የተሳሰርን ነን። ሜዳ ላይ ብዙ ደክመናል። የተሻለ ውጤት ለማምጣትና ተቀናቃኝ ቡድን እንዳያገባብን ብዙ ቪድዮዎች ስንመለከት ነበር” ስትልም አክላለች።
የአሜሪካ ምርጥ ተጫዋች ምርጫ የሚከናወነው ከአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ ከእግር ኳስ ዳይሬክተሮች የቦርድ አባላት፣ ከብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ሊግ ዋና አሠልጣኞች፣ ከሚዲያ አባላት እና ከአስተዳዳሪዎች በተሰጠ ድምጽ ነው።
የኤፒ ዘገባ ዘገባ እንደሚያሳየው ናኦሚ ግርማ 61.6% ድምጽ እግኝታለች።
ናኦሚ ከ2021 ጀምሮ በአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን በተካላከይነት እየተጫወተች ትገኛለች።












