ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያዊቷን ተመራማሪ የገደለው አደገኛ ተላላፊ በሽታ ምን ያህል ዓለምን ያሰጋል?
በሩሲያዋ ሳይቤሪያ ግዛት በሚገኝ የቸነፈር (አደገኛ ተላላፊ በሽታ) ምርምር ማዕከል ውስጥ የቤተ ሙከራ ባለሙያ የሆነች ሩሲያዊት መሞቷን ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስጋቱን እየገለጸ ነው።
ለተመራማሪዋ ሞት ምክንያቱ ከቤተ ሙከራ ሾልኮ የወጣ ተላላፊ በሽታ ሊኖር ይችላል የሚለው አስጊ ሆኗል።
የሩሲያ ባለሥልጣናት መጀመሪያ ላይ ባለሙያዋ የሞተችው ከቸነፈር ጋር በተያያዘ ነው የሚል መረጃ አውጥተው ነበር። አሁን ግን ሞቷ ከቸነፈር ጋር የሚያያዝ አይደለም ብለዋል።
ከህሙማን ለይቶ ማቆያ ጋር ግንኙነት ያላቸው ገለልተኛ የመገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ የተመራማሪዋ ሞት ከቸነፈር ጋር የሚገናኝ ነው።
በከፍተኛ መጠን ተላላፊ የሆነ በሽታ ወይም ቸነፈር በእንግሊዘኛው ፕሌግ (plague) ይባላል።
ለመሆኑ ባለሙያዋ የገጠማት ምንድን ነው? ክስተቱስ ምን ያህል ያሰጋል?
እስካሁን ምን እናውቃለን?
የ28 ዓመቷ ዳሪያ ሺፒሎቪያ በሳይቤሪያ በፀረ ቸነፈር ማዕከል ውስጥ ትሠራ ነበር። ወደ ሆስፒታል የተወሰደቸው መስከረም መጨረሻ ላይ ሲሆን፣ ከሦስት ቀናት በኋላ ሕይወቷ አልፏል።
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2 መሞቷ ቢገለጽም ቢቢሲ መረጃውን ማረጋገጥ አልቻለም።
ሆስፒታሉ ሥራውን እንዲያቋርጥ ተደርጎ የነበረ ሲሆን የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልም ቀርቧል።
ባለፈው ሳምንት የሳይቤሪያ ቀጣና አገረ ገዢ ኢጎር ኮብዜቭ እንደተናገሩት የሩሲያ ዋነኛ የሕክምና ባለሙያ ወደ አካባቢው ሄደዋል።
"አደገኛ የሆነ ኢንፌክሽንን ለመመርመር" ወደ አካባቢው መጓዛቸው ተገልጿል።
ከሟቿ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ላይ ቅርብ ክትትል እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።
ወደ 197 የሚጠጉ ሰዎች በሕክምና ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነ ኢዝቬስቲያ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።
አገረ ገዢው ይሄንን በተናገሩበት ዕለት በአጎራባች ከተማዋ ቡርያታ አንድ የቤተ ሙከራ ባለሙያ ከቸነፈር ጋር በተያያዘ መሞታቸው ተሰምቷል።
ከአደገኛ በሽታዎች ምርምር ተቋሙ ሾልኮ የወጣ ሊሆን ይችላል የሚል ጭምጭምታ የተሰማውም ከዚህ በኋላ ነበር።
አንድ የሩሲያ ጋዜጠኛ ተመራማሪዋ የሞተችው ጥናት የሚደረግበትን ብልቃጥ ከሰበረች በኋላ ነው የሚል ያልተረጋገጠ መረጃ አውጥቷል።
የሚወጣው መረጃ ለምን ተለዋዋጭ ሆነ?
የሩሲያ የሸማቾች ደኅንነት እና የኅብረተሰብ ጤና ቁጥጥር ተቋም የሆነው ሮስፖትሬበንዳዞር የወጣውን መረጃ አስተባብሏል።
ስም ሳይጠቅስ የቤተ ሙከራዋ ባለሙያ የሞተችው መነሻው ባልታወቀ የሳምባ ምች ምክንያት መሆኑን ገልጿል።
በተደረገው ምርመራ መሠረት "ከባለሙያዋ ጥናት ጋር የተገናኙ ረቂቅ ተሕዋሲያን (ማይክሮኦርጋኒዝምስ) አልተገኙም" ሲልም አስታውቋል።
መግለጫው ከወጣ በኋላ የመንግሥት ደጋፊ የሆነ መገናኛ ብዙኃን ክስተቱ ከቸነፈር ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚሉ አምስት ልጥፎችን ከገጹ ሰርዟል።
በቸነፈር ስጋት ምክንያት ወደ ስፍራው ጉዞዎች እንዳይከናወኑ የሚጠይቀው ባለሥልጣናት አውጥተውት የነበረው የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክት ጠፍቷል።
ባለሥልጣናት በተቀናጀ ሁኔታ ክስተቱን ለማቃለል የሚሞክሩ መረጃዎች እያወጡ ይመስላል።
ገለልተኛ የሆነው ባይካል ድረ ገጽ ምንጮችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ በአካባቢው የሚገኙ ቢያንስ አራት ሆስፒታሎች ለሦስት ሳምንታት መዘጋታቸውን ገልጿል። መረጃው ትክክለኛነቱ አልተረጋገጠም።
የበሽታው ክስተት ሪፖርት የተደረገበት አካባቢው ፀረ ወረርሽኝ ተቋም ጥቅምት ላይ ዓለም አቀፍ የቸነፈር ቁጥጥር ጉባዔ እንደሚያስተናግድ ቢቢሲ ሩሲያ ማወቅ ችሏል።
በጉባዔው የቻይና፣ የሞንጎሊያ እና የቀድሞ ሶቪየት ኅብረት አባል የነበሩ በርካታ አገራት ይሳተፋሉ።
ጉባዔው በተያዘው ዕቅድ መሠረት ስለመከናወኑ ቢቢሲ ከተቋሙ ማብራሪያ ጠይቋል።
ቸነፈር ምንድን ነው?
ቸነፈር ወይም ፕሌግ ባክቴርየም (plague bacterium ወይም Yersinia pestis) በ14ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓን ግማሽ ሕዝብ ፈጅቷል።
'ጥቁር ሞት' ወይም 'ብላክ ዴዝ' በሚል ስያሜ የሚታወቅ ቀሳፊ ተላላፊ በሽታ መሆኑ ይታወቃል።
ከኦሺንያ በስተቀር በሁሉም አህጉራት የሚገኝ ሲሆን እንሰሳት ላይ ሕመም ያስከትላል።
አይጦች እና በሩሲያ ቡርያታ ግዛት የሚገኙ ማርሞት ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው።
ሰዎች በቁንጫ ንክሻ፣ ከሰውነት በሚወጣ ፈሳሽ፣ ከተበከለ ቁስ ጋር በሚኖር ንክኪ ወይም ቅንጣቶች በመተንፈሻ አካል በኩል ወደ ሰውነት ሲገቡ ለሕመም ሊጋለጡ ይችላሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው እንደ ሳምባ ምች ያለው ቸነፈር በሰውነት ውስጥ ለመሠራጨት የሚወስድበት ወቅት (ኢንኬቤሽን ፔሬድ) 24 ሰዓታት ብቻ ነው። በቶሎ ሕክምና ካልተገኘም ለሞት ሊዳርግ ይችላል።
ትንፋሽ ማጠር፣ ማሳል እና ደም የቀላቀለ አክታ ከምልክቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
የቤተ ሙከራ ባለሙያዋ ለኅልፈት የተዳረገችው በምንም ምክንያት ቢሆን የቸነፈር ወረርሽኝ ሊነሳ የሚችልበት ዕድል ጠባብ እንደሆነ ሩሲያዊቷ የሳይንስ ዘጋቢ ኢርና ያኩቴንኮ ትናገራለች።
ለዚህም ምክንያቱ ወረርሽኝ ለማሠራጨት ምቹ የሆነ ሁኔታ ባደጉ አገራት አለመኖሩ ነው ትላለች።
"መሠረታዊ የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶች ቸነፈርን ያጠፋሉ። አሁን ላይ በሽታው በስፋት አይስተዋልም። የመስፋፋት ዕድልም አላገኘም።"
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምን አለ?
የዓለም ጤና ድርጅት የሩሲያ ባለሥልጣናት ክስተቱን እንዲመረምሩ እና በዓለም አቀፍ ጤና ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ እንዲገመግሙ ማሳሰቡን የተቋሙ ቃል አቀባይ ለፖለቲኮ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ተላላፊ በሽታዎች ተቆጣጣሪ (ኢሲዲሲ) ባለሙያዎችም ጉዳዩን እየተከታተሉ እንደሆነ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
አሜሪካ ክስተቱን "እጅግ በቅርበት እየተከታተለች" እንደሆነ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገልጸዋል።
በሩሲያ ቸነፈር ተነስቶ ሊሆን ይችላል የሚለው ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ በቁጥጥጥር ሥር ለማዋል አሜሪካ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ናት ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ማርኮ ሩቢዮ "ሩሲያ ግልጽ ሆና ለዓለም መረጃውን እንድትሰጥ እንጠይቃለን፤ ከዚያ በተገቢው መንገድ ምላሽ እንሰጣለን" ሲሉ ተናግረዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፤ ትራምፕ ድጋፍ ለመስጠት ያቀረቡትን ሐሳብ በበጎ ተቀብለዋል።
"ድጋፍ እናደርጋለን ሲባል ጥሩ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በጉዳዩ ላይ ተዓማኒ የሚሆነው በሽታው ተከሰተበት ከሚባልበት ኢኩትስክ ከተባለው ስፍራ የሚወጣ ይፋዊ መረጃ ብቻ ነው ብለዋል።
በበይረ መረብ ምን መረጃ ተሠራጨ?
በሩሲያ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም በበይረ መረብ የወጡ መረጃዎች እርስ በርስ ይጣረሳሉ።
ስለ ሁለተኛው ሟች ያልተረጋገጠ መረጃ ያወጡ ቢያንስ አምስት የኢንስታግራም ገጾችን ቢቢሲ አግኝቷል።
አምስቱ ገጾች በአጠቃላይ 169,000 ተከታዮች አሏቸው።
በሩሲያኛ ተመሳሳይ መረጃ የሚለቁት ገጾች ሁለተኛው ሟች ቪክተር ናክሎኒ እንደሚባል እና የመጀመሪያዋ ሟች ዳሪያ ሺፒሎቪያ የሥራ ባልደረባ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለሩሲያ የሸማቾች ደኅንነት እና የኅብረተሰብ ጤና ቁጥጥር ተቋም ቅርብ የሆነ ምንጭ ይሄንን አላረጋገጠም።
ቢቢሲ ከተቋሙ ምላሽ ጠይቋል። በሳይቤሪያ ያለው የፀረ ቸነፈር ተቋም አስተያየት ለመስጠት አልፈቀደም።
ያልተረጋገጡትን መረጃዎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም አስተጋብተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደሙ ዴይሊ ሜል መረጃው የሩሲያ "መገናኛ ብዙኃን" ነው ሲል ዘግቧል።
በበይነ መረብ ላይ የተሰጠው ምላሽ የተለያየ ነው። አንዳንዶች ስጋታቸውን ሲገልጹ ሌሎች ሐሰተኛ መረጃ ነው ብለዋል።
ቢቢሲ በኤክስ ላይም ያልተረጋገጡ መረጃዎች አግኝቷል። እነዚህን ልጥፎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተመልክተዋል።
አንድ ጦማሪ ከጓደኛዬ አገኘሁት ባለው መረጃ የሩሲያዋ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ሴንት ፒተርስበርግ የእንቅስቃሴ ገደብ ልትጥል ነው ብሏል። ልጥፉን ስድስት ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተዋል።
ሆኖም ግን የከተማዋ ባለሥልጣናትም ሆነ መገናኛ ብዙኃን ቸነፈር መኖሩን ወይም የእንቅስቃሴ ገደብ እንደሚጣል አልገለጹም።
ሌላ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ "የሳምባ ምች ቸነፈር ከሩሲያ ቤተ ሙከራ ሾልኮ ወጥቷል፤ ከኮቪድ 100 እጥፍ የከፋ ነው" ብሏል። ይህንን ልጥፍ 11.3 ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተዋል።
በሽታው ካልታከመ ሰዎችን ሊገድል ቢችልም ፀረ ባክቴርያ በቁጥጥር ሥር ስለሚያውለው እንደ ኮቪድ ወረርሽኝ ኅልፈት ሊያስከትል የሚችልበት ዕድል የለም።