በፈረንሳይ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ 500 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ተዘጉ
ባለፉት ቀናት በፈረንሳይ የአድማ ብተና ፖሊሶች እና ተቃዋሚ ተማሪዎች መካከል ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ፣ እስከ 500 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች በዛሬው ዕለት [ሰኞ] በሙሉ ወይም በከፊል እንደሚዘጉ የፈረንሳይ የትምህርት ሚኒስትር ገለጹ።
ኤዱዋር ጄፍሬይ እንዳሉት፣ በ“400 እስከ 500” የሚደርሱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ “የደኅንነት ሁኔታዎች ስላልተሟሉ” ትምህርት በሙሉ ወይም በከፊል ይቋረጣል። እንዲሁም ከተቃውሞዎቹ መጀመር በኋላ 24 ትምህርት ቤቶች “ተቃጥለዋል ወይም ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በትምህርት ጥራት ላይ ተቃውሞ ያደረጉ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በፓሪስ የጀመረው እንቅስቃሴ ወደ ሞንፔሊየ፣ ናንትስ እና ማርሴይን ጨምሮ ወደ ሌሎች ከተሞችም ተስፋፍቷል።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና ሌሎች ተቃዋሚዎች የመምህራን እጥረት፣ የተጨናነቁ ክፍሎች እና ያረጁ እና የተበላሹ የትምህርት ቤት ሕንፃዎችን ሁኔታ በመቃወም ወደ አደባባይ ወጥተዋል።
የፈረንሳይ የፍትሕ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒን አርብ ዕለት እንደተናገሩት፣ ከፈረንሳይ 3,700 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 735 የሚሆኑት “በአንድ ወይም በሌላ መልኩ” ኃይል በተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎች ተፅእኖ ደርሶባቸዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዛሬ ሰኞ ችግር የሚገጥማቸው ትምህርት ቤቶች ቁጥር ካለፈው ሳምንት አሃዝ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀው፣ ቢሆንም “ትምህርት በከፊል እና በደረጃ በደረጃ” እንደሚጀመር ቃል ገብተዋል።
ጨምረውም ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ 78 የትምህርት ዘርፍ ሠራተኞች መቁሰላቸውን ገልጸው፣ ይህንንም “ከዚህ በፊት አይተነው የማናውቀው ነገር ነው” ሲሉ ገልጸውታል።
የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሎራን ኑኔዝ እንዳሉት፣ ዓርብ ዕለት ብቻ 1,747 ሰዎች ታስረዋል።
ነገር ግን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደዘገበው፣ እንቅስቃሴው ከተጀመረ ወዲህ በአጠቃላይ ከ5,000 በላይ ሰዎች ታስረዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች እና ወጣቶች ናቸው።
እሁድ እለት የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲያን ሌኮርኑ መንግሥታቸው “የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና የትምህርት ዘርፉ ሠራተኞች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት” ተጨማሪ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።