ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በሱዳን ታጣቂ ኃይል በተፈፀመ የድሮን ጥቃት 41 ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከኢትዮጵያ ድንበር ጋር በሚዋሰነው የአገሪቱ ብሉ ናይል ክልል በፈፀመው የድሮን ጥቃት 41 ሰዎች መገደላቸውን አንድ የመብት ተሟጋች ቡድን አስታወቀ።
ከአገሪቱ የመንግሥት ኃይሎች ጋር በመዋጋት ላይ የሚገኘው እና አስቀድሞ የአገሪቱ ጦር ድጋፍ ሰጭ የነበረው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዓርብ ዕለት የፈፀመው ጥቃት፣ በክልሉ አቡ ሻንዲ አካባቢ የሚገኘው የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር 'ኢመርጀንሲ ሎውየርስ' የተባለው ቡድን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) በበኩሉ "እጅግ አስደንጋጭ" ባለው በዚህ ክስተት "ደንግጫለሁ" ብሏል። የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች፣ አብዛኞቹ ተጎጂዎች ሴቶችና ሕጻናት መሆናቸውን እንደሚያመለክቱም ኦቻ ገልጿል።
የሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሚመሩ አማፂያን ከአውሮፓውያኑ 2023 ጀምሮ የአገሪቱን ሥልጣን ለመቆጣጠር በመዋጋት ላይ ይገኛሉ።
ይህ ውጊያ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው አፈናቅሏል።
ግጭቱ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ የከፉ የሰብዓዊ ቀውሶች አንዱ እንዲፈጠር ሲያደርግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም የሕክምና ድጋፍ ይፈልጋሉ።
የሱዳን ጦር አብዛኛውን የአገሪቱን መካከለኛና ምሥራቃዊ ክፍሎች የሚቆጣጠር ሲሆን፣ ዋና መሠረቱን ምዕራባዊው የዳርፉር ክልል ያደረገው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ደግሞ በደቡብ ሱዳን የሚገኙ አካባቢዎችንም ተቆጣጥሯል።
በጦርነቱ ሁለቱም ወገኖች የድሮን ጥቃቶችን በመፈፀም ክሶች ይቀርቡባቸዋል።
ኦቻ ባወጣው መግለጫ፣ ዓርብ ዕለት የድሮን ጥቃት ተፈፀመበት የተባለው አካባቢ "ባለፉት ሳምንታት ተደጋጋሚ ጥቃት ሲደርስበት የነበረ ሲሆን፣ በዚህም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ሲፈናቀሉ ብዙዎች ለከባድ አደጋ ተጋልጠዋል" ብሏል።