በአሜሪካ ሚዙሪ ሁለት የቤተሰብ አባላቱን የገደለው በሞት ተቀጣ

ብሪያን ዶርሲ

የፎቶው ባለመብት, Jeremy Weiss

እአአ በ2006 የአጎቱን ልጅ እና ባለቤቷን የገደለው የሚዙሪ ነዋሪ በእስር ቤት የጥበቃ አባላት ምህረት ቢጠየቅለትም በሞት ተቀጥቷል።

የ52 ዓመቱ ብሪያን ዶርሲ ከአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች ጋር በተያየዘ የነበረበትን ዕዳ ለመክፈል የተስማሙትን ሳራ ቦኒ እና ቤን ቦኒ በጥይት ተኩሶ ገድሏቸዋል።

ግድያው በተፈጸመበት ወቀት የጥንዶቹ የአራት ዓመት ሴት ልጅ ቤት ውስጥ ነበረች።

ማክሰኞ የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ እንደተደረገበት የሚዙሪ ማረሚያ ቤት አስተዳር አስታውቋል።

ዶርሲ በእስር ቤት ቆይታው አዎንታዊ የባሕሪ ለውጥ ማምጣቱን እና በችሎት ውሎው በቂ የሕግ ከለላ እንዳላገኘ በማንሳት ሞት ፍርዱ እንዲቀየር ብዙዎች ተሟግተዋል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን የሞት ፍርድ ውሳኔው እንዲዘገይ የቀረቡለትን ሁለት ይግባኞች ውድቅ አድርጓል። የሚዙሪ ገዢ በሰጡት መግለጫ ዶርሲ “በችግር ጊዜ የረዱትን ቤተሰቦቹን ቀጥቷል” ሲሉ የምህረት ጥያቄን ውድቅ አደርገዋል።

የአጎቱን ልጅ ከገደለ በኋላም የጾታ ጥቃት ፈጽሟል የሚለውን የአቃቤ ህግ ክስ የሚዙሪ ገዥ ማይክል ፓርሰንስ አንስተዋል። የዶርሲ ጠበቆች ግን ይህንን ክስ በችሎት የተረጋገጠ አይደለም በማለት ውድቅ አድርገዋል።

ዶርሲ ከጥቃቱ ከሦስት ቀናት በኋላ ራሱን ለፖሊስ አሳልፎ ሰጥቷል። ጥፋተኛ ነኝ ብሎም አምኗል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እአአ በ2023 በሚዙሪ ግዛት አራት ሰዎች የሞት ፍርድ ተፈጸሞባቸዋል። ዶርሲ በዘንድሮው የፈረንጆች ዓመት በሚዙሪ የሞት ቅጣት የተፈጸመበት የመጀመሪያው እስረኛ ሆኗል።

ባለፉት 17 ዓመታት አርአያ የሆነ እስረኛ ነበር ሲሉ የዶርሲ ጠበቆች ገልጸዋል። በእስር ቤቱ ፀጉር አስተካካይነት ከመሥራቱም በላይ በሠራው ወንጀል ተጸጽቷል ሲሉ ተከራክረዋል።

ከገና በዓል ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅት በአደንዛዥ እፅ ምክንያት የአእምሮ ህመም እየተሰቃየ ነበር ያሉ ሲሆን በፍርድ ሂደቱ ወቅት ጠበቆቹ የጥቅም ግጭት እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።

ጠበቆቹ የሞት ፍርድ ሊፈረድበት እንደማይችል ሳያረጋግጡ ጥፋተኛ ነኝ እንዲል አቻኩለውታልም ብለዋል።

ከ70 በላይ የሚሆኑ የማረሚያ ፖሊሶች በመልካም ስነ ምግባሩ ምክንያት ቅጣቱ ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀየር በፊርማቸው ጠይቀዋል።

"ለዓመታት የማውቀው ብሪያን ማንንም ሊጎዳ አይችልም። እኔ የማውቀው ብሪያን ሊገደል አይገባም" ሲል አንድ ማረሚያ ቤቱ ፖሊስ ማመልከቻው ላይ ጽፏል።

ዶርሲ ከመሞቱ በፊት በሰጠው የመጨረሻ ቃል ለተጎጂዎቹ እና ለዘመዶቻቸው በድጋሚ ይቅርታ ጠይቋል።

"ለሳራ እና ለሁሉም ለምወዳቸው ቤተሰቦቻችን እና የቤን ወዳጆች በሙሉ በጣም በጥልቅ አዝኛለሁ" ብሏል።

"ጥፋቴን እና የእፍረቴን መጠን ቃላቶች ሊገልጹት አይችሉም። አሁንም እወዳችኋለሁ። ማንንም መጉዳት ፈጽሞ አልፈለግኩም። እነሱንም እና አንተንም ስለጎዳሁ ይቅርታ።"

የሞት ቅጣቱ ከመፈጸሙ በፊት ጥቃት የደረሰባቸው ዘመዶች ውሳኔውን "በመጨረሻም ብርሃን አየን" ብለውታል።

ዶርሲን "ከመጥፎ ሁኔታ ለመውጣት እጃቸውን የዘረጉለት የቅርብ የቤተሰብ አባላት ነበሩ። ይህንን የእርዳታ ወደ ክህደት ቀይሮታል" ሲል የሳራ ቦኒ ቤተሰቦች መግለጫቸው አስታውቀዋል።