ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሳይተዋወቁ አንዳቸው የሌላኛውን ሕይወት የታደጉት ሁለት ግለሰቦች
ሁለት የማይተዋወቁ ሰዎች አንዳቸው የሌላኛውን ሕይወት ታድገዋል።
በዜግነት የማይገናኙት ሁለቱ ሰዎች አንደኛው የዩናይትድ ኪንግደም ዜጋ ሲሆን፣ ሌላኛው ጀርመናዊ ነው።
እንዴት? ታሪኩ እንዲህ ነው።
ማሪየስ ቨርነር የተባለው ጀርመናዊ ወጣት የአጥንት መቅኒ በመለገስ የብሪታንያዊውን ዶክተር ሕይወት ታድጎል።
ለበርካታ ዓመታት ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ራሱን ለማጥፋት ሲያሰላስል የነበረው ይህ ወጣት፣ የመኖር ተስፋው እንደለመለመ እና በሕይወቱም ዓላማ እንዳለው ተረዳ። በዚህም የዶክተሩ ሕይወትም ለማሪየስ መኖር ምክንያት ሆኗል።
ባልተለመደ ዓይነት የደም ካንሰር ተጠቅቶ የነበረው ዶክተር ኒክ ኢምብልተን ብቸኛ ተስፋው የነበረው የአጥንት መቅኒ ንቅለ ተከላ (ቦንማሮው ትራንስፕላንት) ነበር።
በአገሩ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከእሱ ጋር የሚመሳሰል ለጋሽ ባለማግኘቱም ፍለጋው በዓለም ዙሪያ እንዲሆን ተደረገ።
ልገሳው ከተካሄደ ከሁለት ዓመታት በኋላ ቢቢሲ እና አንቶኒ ኖላን የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት “በደም የተሳሰሩትን” እነዚህን ግለሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲገናኙ አድርገዋቸዋል።
‘ልሞት እችል ነበር’
የ60 ዓመቱ የህክምና ባለሙያ ኒክ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በኒውካስል ያለጊዜያቸው የተወለዱ ጨቅላዎች ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ ነው ያገለገለው።
በሺዎች የሚቆጠሩ የዓለማችን ትንንሽ ታካሚዎችን ሕይወት የታደገው ይህ ዶክተር እሱም በአንድ ወቅት ህክምና አስፈለገው።
በአውሮፓውያኑ 2021 በደም ካንሰር እንደተጠቃ ታወቀ።
ከምርመራው በኋላ በሆስፒታሉ መተላለፊያዎች ሲረማመድም ዶክተር ኒክ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ ነበር።
“እንደምሞት ስለተረዳሁም ተናዘዝኩኝ” ይላል።
“መርዶውንም ለባለቤቴ እና ለልጆቼ ነገርኳቸው።”
“ለልጆቼ በጣም አዘንኩላቸው። ቀሪ ሕይወታቸውን ያለ አባት እንዲያድጉ አልፈልግም ነበር።”
የአጥንት መቅኒ ንቅለ ተከተላ ጤናማ ያልሆኑ የደም ህዋሳትን በጤናማ ይተካቸዋል። ነገር ግን ተመሳሳይ ካልሆነ ሰውነታችን ወዲያውኑ ነው ውድቅ የሚያደርገው።
የአንቶኒ ኖላን የበጎ አድራጎት ድርጅት ሠራተኛ ሻርለት ሂዩዝ እንደተናገሩት መጀመሪያ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ተመሳሳይ ለጋሾችን ከፈለጉ በኋላ ካልተገኘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍለጋቸውን እንደሚቀጥሉ ያስረዳሉ።
ለጋሾች ከየትኛውም ቦታ ሊመጣ እንደሚችልም ነው የሚገልጹት።
‘ደስታዬ ከቃላት በላይ ነው’
የንቅለ ተከላው ቀዶ ህክምና እስኪጠናቀቅ ድረስ የለጋሽ እና የህመምተኛው ማንነት ለሁለቱም ግለሰቦች ሳይገለጽ መቆየት አለበት።
የቀዶ ህክምናው በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ ከህመሙም ከተፈወሰ ከሁለት ዓመት በኋላ ዶክተር ኒክ ለጋሹን ማወቅ እንደሚፈልግ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ቢቢሲ ከአንቶኒ ኖላን ጋር በመጣመርም ለዶክተሩ ልገሳውን ያበረከተው ግለሰብ ማሪየስ የተባለ የ24 ዓመት ወጣት መሆኑን አወቀ። በጀርመን ቼምኒትዝ በምትባል ስፍራ የሚኖረው ወጣት ከአስራዎቹ ዕድሜ ጀምሮም በለጋሽነት የተመዘገበ ነው።
ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተጉዞ ዶክተር ኒክን ለማግኘት ተስማማ።
ሁለቱም ዶክተር ኒክ ንቅለ ተከላውን ባደረገበት በሜጊ ኒውካስትል የካንሰር ድጋፍ ማዕከል፣ ፍሪማን ሆስፒታል ተገናኙ። ሁለቱ ሰዎች ሲገናኙ ተቃቀፉ። ማሪየስም “የተሰማኝን ስሜት መግለጽ ከምችለው በላይ ነው፣ እየተንቀጠቀጥኩ ነው” ሲል ተናገረ።
‘በጣም አመሰግናለሁ’
ዶክተር ኒክ የካንሰር ህዋሳቱ በሙሉ እንደተወገዱ ለማሪየስ ነገረው።
“ደሜን ሲመረምሩ ህመምተኛ የነበሩት ህዋሳት በሙሉ ተወግደው በአንተ የደም ህዋሳት ተተክተዋል። ሁሉም የአንተ ናቸው።”
“አንተ ባትኖር ኖሮ ሞቼ ነበር።”
“አራት ልጆቼም አባት አይኖራቸውም ነበር።”
“ምን ማለት እችላለሁ፣ አመሰግናለሁ ብቻ።”
ቃላት የጠፋበት ማሪያስም “ምንም አይደል!” ሲል መለሰ።
ሁለቱም ፊታቸው በእንባ ታጠበ። ኒክም በሳግ በተቆራረጠ ድምጽ “በጣም አመሰግናለሁ!” ሲል መለሰ።
‘እንባዬ ይቀድመኛል’
ማሪየስ ንቅለ ተከላው በስኬት ተጠናቆ የዶክተር ኒክን ሕይወት እንደታደገም ከተረዳ በኋላ “እንባዬ ይቀድመኛል” ይላል።
“ወደ ሥራ ለመሄን መንገድ ላይ ነበርኩ፣ እናም መኪናዬን አቁሜ መውጣት ነበረብኝ። እንባዬም እየፈሰሰ ነበር።”
ማሪየስ ከዚህ ቀደም ራሱን ለማጥፋት ሞክሮ በሆነ መንገድ ዶክተር ኒክ እንደረዳው ገልጿል።
“ከ13 ዓመቴ ጀምሮ ሙሉ ሕይወቴን ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ እየታገልኩ ነበር” ይላል።
“የሕይወቴን መንገድ መፈለግ ለእኔ ፈታኝ ነበር። በሕይወቴ ውስጥ ምን አላማ አለኝ? የሚለውም የዘወትር ጥያቄዬ ነበር።”
“በአሁኑ ወቅት አንድ ነገር በትክክል አከናውኛለሁ ማለት እችላለሁ።”
ሁለቱ የማይተዋወቁ ሰዎች በልገሳ ምክንያት ተሳስረው ግንኙነታቸውንም ለማጥበቅም አቅደዋል።